አወዛጋቢው የወሎ ተርሸሪ ኬር ሆስፒታል ግንባታ
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 4 2017የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የመንግስት ወጭ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለወሎ ተርሸሪ ኬር ሆስፒታል ግንባታ ከህዝብ የተሰበሰበ ገንዘብ አሰባብ ላይ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት አስታወቀ።
የወሎ ተርሸሪ ኬር ሆስፒታል ግንባታ በ2003 አመተ ምህረት በኢትዮጵያ ያለዉን ህክምና ለማዘመን መፍትሄ ይሆናል ተብሎ ሀብት የማሰባሰብ ሂደቱ የተጀመረ ቢሆንም ባለፋት 14 ዓመታት ግንባታዉን ለመከወን የተቋቋመዊ ኮሚቴ ምንም አይነት ግንባታ ሳይከዉን ቆይቷል ነው የተባለው።
እንደ ፌደራል ኦዲት ቢሮ ሪፖርት ከሆነ በተለያዮ ምክንያቶች ለግንባታዉ ከተሸጡ ኩፖንና ሎተሪዎች ገቢ መሆን የሚገባዉ ገንዘብ በክልሎች፣ ኢምባሲዎችና ግለሰቦች ገቢ አልተደረገም።
የህዝብ አመኔታ ያጣው የሆስፒታሉ ግንባታ
ለዶቸ ቬሌ አስተያየታቸዉን የሰጡ የደሴ ከተማ ኗሪዎች እንደተናገሩት "የወሎ ተርሸሪ ኬር ሆስፒታል ግንባታ ገቢራዊ እንዲሆን በቻልነዉ መጠን አስተዋፅኦ ብናደርግም የተሰበሰበዉ ገንዘብ የት እንደደረሰ ሳናዉቅ ፕሮጀክቱ ቆሟል" ይላሉ።
ጠቅላይ ሚንስተር አብይ አህመድ በለዉጡ ማግስት ከደሴ ከተማ ማህበረሰብ ጋር በነበራቸዉ ዉይይትም "ከህብተረተሰብ የተሰበሰበዉ ብር ለአስተዋፅኦ የሚሆን ግንባታ ይሰራበት መንግስት በሪፈራል ሆስፒታል ደረጃ በራሱ ወጭ ግንባታዉን ይከዉናል" ብለዉ ነበር
ይሁን እንጂ ይህ ፕሮጀክቱን እንዲተገብር የተቋቋመዉ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ሲቨል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እዉቅና ሳይኖረዉ ስራ እየከወነ ሲሆን የሆስፒታል ግንባታዉም ከኮሚቴዉ ወደ ወሎ ዮንቨርስቲ ተሸጋግሯል።
ገንዘቡን ለማስመለስ አቅም የለንም
ባክኗል ስለተባለዉ ገንዘብም የፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ,ኃላፊ የሆኑት አቶ እሽቱ አየለ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት መሰብሰብ እንዳልቻሉ ይናገራሉ የአሜሪካና ሪያድ ኢምባሲዎች በግዜዉ የተሰጣቸዉን የገቢ ማሰባሰቢያ ኩፖን ወደገንዘብ ያልቀየሩ ሲሆን የአማራ ክልልን ጨምሮ በኦሮምያ ደቡብና አፋር ከኩፖንና ሎተሪ ሽያጭ መገኘት የሚገባዉ ብር ገቢ አልተደረገም።
ፕሮጀክት ፅህፈት ቤቱ ከ2010 ዓመተ ምህረት በኃላ ህጋዊ ሆኖ መንቀሳቀስ ስለማይችል የሰበሰበዉን ገንዘብ ለማስረከብ ተረካቢ ማጣቱን ይይገልፃል።
አሁን የሆስፒታሉ ግንባታ በወሎ ዩንቭርስቲ እየተከወነ ነው
የወሎ ዮንቨርስቲ ፕሬዝደንት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌትነት መልአክ እንደገለፁት ዩንቨርስቲዉ ለወሎ ተርሸሪ ኬር ሆስፒታል ግንባታ ተብሎ የተመደበ በጀት ባይኖርም ስራዉን ለማጠናቀቅ እየሰራን ነዉ ይላሉ። ነገር ግን ከዚህ ቀደም ከህዝብ የተሰበሰበን ገንዘብ በተመለከተ አስፈላጊዉ ህጋዊ ኦዲት ሲከወን ተጠያቂነት ባለዉ መልኩ እንረከባለን ይላሉ።
የወሎ ተርሸሪ ኬር ሆስፒታል ግንባታ 3 ቢልየን ብር ይፈጃል ተብሎ ቢጀመርም እስካሁን የዋናዉ ሆስፒታል ግንባታ አልተጀመረም።
ኢሳያስ ገላው
አዜብ ታደሰ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር