1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አካል ጉዳተኛው የቴኳውንዶ አሰልጣኝ

ዓርብ፣ መጋቢት 10 2013

የዛሬው የወጣቶች መሰናዶ በባሕር ዳር ከተማ የቴኳንዶ ስፖርት በሚያሰለጥነው ከማል ቃሲም ላይ ያተኩራል። መሰናዶውን ያጠናቀረው የባሕር ዳሩ የዶይቼ ቬለ ወኪል ዓለምነው መኮንንን ነው።

https://p.dw.com/p/3qs1X
Kemal Kassim | Taekwondo Trainer
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

አካል ጉዳተኛው የቴኳውንዶ አሰልጣኝ

ከማል ቃሲም ትውልዱ ጎንደር ከተማ ቢሆንም ያደገው ግን ከባሕር ዳር ከተማ በስተሰሜን 30 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኘው ወረታ ከተማ ነው፡፡ ከማል የ4 ዓመት ህፃን ሆኖ ነው ወደ ወረታ የመጣው፡፡ ወቅቱ በአማፂው የኢህአዴግና በመንግስት መካከል ጦርነት የተጠናቀቀበት ጊዜ ነው፡፡ በጦርነቱ በርካታ ቀላልና ከባድ የጦር መሳሪያዎች በብልሽት በየቦታው ተንጠባጥበው ይታዩ ነበር፡፡ 
 በ1985 ዓ.ም ህፃኑ ከማል የ6 ዓመት ልጅ እያለ ከሌሎች ህፃናት ጓደኞቹ ጋር ወረታ ከተማ ተበላሽቶ በቆመ ታንክ እየወጡና እየወረዱ ይጫወቱ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ አንድ ቀን ግን ለከማል ክፉ ቀን ነበረች፡፡ እንደተለመደው እየተጫወቱ ባለበት ወቅት ከታንኩ የመተኮሻ ጫፍ አካባቢ በድንገት በመውደቁ የቀኝ እግሩን ያጣበት ቀን እንደነበር ከዶይቼ ቬለ ጋር በነበረው ቆይታ አጫውቶናል፡፡ 
 የባህር ዳር ከተማ ወርልድ ቴኳውንዶ ፌደሬሽን ፕረዚደንትና የአማራ ክልል አሰልጣኞች ማሕበር ፕረዚደንት ማስተር ክንፈ እሺበል ሁለት ዓይነት የቴኳንዶ ዐይነቶች እንዳሉ ይናገራሉ፣ ወርልድ ቴኳውንዶ የደቡብ ኮሪያ ሲሆን በኦሎምፒክ ስፖርት ውስጥ የተካተተ ነው፣ ኢንተርናሽናል ቴኳውንዶ ደግሞ የሰሜን ኮሪያ ሲሆን በኦሎምፒክ ውስጥ ያልተካተተ ቢሆንም ውድድር ግን የሚደረግበት ስፖርት ነው፡፡ 
 ባለሙያው እንደሚሉት ከማል በኢንተርናሽናል ቴኳውንዶ በአካል ጉዳተኛ ደረጃ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ባለሶስተኛ ዲግሪ ነው፣ 3ኛ “ዳን” ይባላል፡፡ 
 ማስተር ክንፈ ከማልን ባለ ቢጫ ቀበቶ ሳለ እንደሚያውቁትና ጠንካራና አረአያ የሚሆን ልጅ እንደሆነ መስክረዋል፤ ወደፊትም ከፍተኛ ደረጃ ይደርሳል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡ 
 ከከማል ተማሪዎች መካከል ፍቅረተ አዝመራውና አበበ ቢሆን እንደነገሩን ከማል የማይሰለቸው፣ አካል ጉዳተኛነቱ ከመስራት የማያግደው ጠንካራና ራዕይ ያለው የቴክዋንዶ አሰልጣኝ ነው፡፡ 
 ከማል የማሰልጠኛና ሌሎች ብዙ ችግሮች እንዳሉበት የገለፀ ሲሆን፣ የባህር ዳር ከተማ ወርልድ ቴኳውንዶ ፌደሬሽንና ፕረዚደንትና የአማራ ክልል አሰልጣኞች ማሕበር ፕረዚደንት ማስተር ክንፈ እሺበል እንደሚሉት ደግሞ ችግሮቹ እንዲፈቱ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ 
 ከማል በተወዳደረባቸው ውድድሮች ከ20 በላይ ሜዳሊያዎች፣ ከ60 በላይ ሰረተፊኬቶችና ዋንጫዎችን መሸለሙን በቆይታችን አጫውቶናል፡፡ 

 ዓለምነው መኮንን (ባሕር ዳር)

እሸቴ በቀለ