1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«አንድ ባጃጅ ላይ 13 ሆነን ነው የመጣነው»የሳዑዲ ስደተኛ

ዓርብ፣ መጋቢት 22 2015

ኢትዮጵያ ውስጥ ከመቶ ሺህ በላይ ወጣቶች ለውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ሰልጥነው በህጋዊ መንገድ የሚሄዱበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑን መንግሥት ሰሞኑን አስታውቋል። በሌላ በኩል በሳዑዲ አረቢያ የተለያዩ እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አሁን ድረስ ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ነው። ሌሎች ደግሞ በህገ ወጥ መንገድ ወደዛው እየተሰደዱ ይገኛሉ።

https://p.dw.com/p/4PX6d
Tuktuk
ምስል picture alliance / Frank May

«አንድ ባጃጅ ላይ 13 ሆነን ነው የመጣነው»የሳዑዲ ስደተኛ

አረቡ እንድሮ ብላችሁ ጥሩኝ ያለን አንድ የ 19 ዓመት ወጣት ሳዑዲ ዓረቢያ ከገባ አንድ ወር ከ 15 ቀን ሆነው። የ 11ኛ ክፍል ተማሪ የነበረው ወጣት ለመሰደድ የወሰነው እንደ በርካታ ኢትዮጵያውያን በድህነት ምክንያት ነው። ህገ ወጥ ስደት ጥሩ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ሰምቶ የነበረ ቢሆንም ዛሬ «ማየት ማመን ነው» ይላል።  « እንዳንመጣባቸው፣ ለሸር ይመስለኝ ነበር ሁሉን ነገር ስደርስበት ግን አየሁት»
ወደ ሳዑዲ ሲጓዝ የመጀመሪያ ጊዜው የሆነው ይኼው ወጣት ሳዑዲ ዓረቢያ ለመድረስ 29 ቀናት ፈጅቶበታል። በጉዞው ላይ መራብ እና መጠማት ሊኖር እንደሚችል ቢጠብቅም የገጠመው ግን ካሰበው በላይ ነበር። « ሴቱ ወንዱ ላይ ወንዱ ሴቲቷ ላይ ንብርብር እያልን ነው ተጭነን የመጠናወው። አንድ ባጃጅ ላይ ለ 13 ታጭቀን ነው የተጓዝነው። ለጀልባ ቲኬት ስንቆርጥ እየተተኮሰብን ነው  የቆረጥነው።»
ወደ ሳዑዲ ለመጓዝ መኪና ስንጠባበቅ የነበርን 723 ሰዎች ነበርን የሚለው አረቡ ጉዞውን ከደቡብ ወሎ የጀመረው ከአንድ ጓደኛው ጋር ሆኖ ነው። የጉዞውን መነሻ ገንዘብ ያገኘው ያለችውን ግልገል ሸጦ ነው። « ጓደኛዬ ብር የለውም ነበር። ከዛ ያቺን ገንዘብ ከጓደኛዬ ጋር ተካፈልናት ። ኋላ ግን ለየብቻ ነው የምትሄዱት ተብለን ባቲ ላይ ለያዩን። ገንዘቡ እኔ ጋር ነበር።» ይላል።
ከዛም ሁለቱም ጓደኛሞች ጉዟቸውን ለየብቻ ቀጠሉ። መልሰው በአራት ቀን ልዩነት የመን ላይ ተገናኙ እና ጉዟቸውን ወደ ሳዑዲ ቀጠሉ። 

ኢትዮጵያውያን የሳዑዲ ተመላሾች
ኢትዮጵያውያን የሳዑዲ ተመላሾችምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

የሳዑዲ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሰይድ የሀገሪቱ መንግሥት ህገ-ወጥ ያላቸውን ዜጎች ግዛቱን ለቀው እንዲወጡ መመሪያ ሲያወጣ፣ ከዛም ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያን ሲታሰሩ ወይም ወደ ኢትዮጵያ ተመላሽ ሲደረጉ እንደነበር በቅርብ ሆነው ታዝበዋል። እንደዛም ሆኖ  አሁን ድረስ ወጣቱ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ እየገባ እንደሆነ ነው የሚናገሩት፤ « ይሔ ነገር እስከመቼ ነው የሚቀጥለው? ከአንድ ወር ገደማ በፊት የቅርብ ቤተሰብ ተቀብያለሁ። በህገ ወጥ መንገድ ነው። አሁንም የእህቴ ልጅ የመን እና ሳዑዲ ድንበር ላይ ነው ያለው። እየመጡ ነው።» ይላሉ ህገ ወጥ ስደትን የሚቃወሙት አቶ ሰይድ።  ስደተኞቹ ሳዑዲ እስኪደርሱ እስከ 10 000 ሺ ሪያል ገደማ ከደላሎች እንደሚጠየቁ ይናገራሉ። አብዛኛውን ጊዜ ኢትዮጵያ ያሉ ቤተሰቦቻቸው ይህንን ገንዘብ መክፈል አይችሉም። ስለሆነም እንደ እሳቸው ውጪ ያሉ ዘመዶች ሳይወዱ በግድ መክፈል ግድ ይላቸዋል።  « ወጣቱ ለቤተሰብ አይናገርም። ተደብቆ ነው የሚወጣው። አፋር ክልል ከደረሰ ወይም ጅቡቲ ከደረሰ በኋላ ይህን ያህል ተጠይቄያለሁ ብሎ ስልክ ይደውላል። » አረቡም ቢሆን ያደረገው ይህንን ነው። ግልገል ሸጦ ሳዑዲ መግባት እንደማይችል ያውቅ ነበር። የመን ላይ ሲደርስ ለአባቱ በመደወል ገንዘብ እንዲልኩለት መጠየቅ ነበረበት። ገንዘቡን ከየት አምጥተው እንደከፈሉለት አያውቅም። ሳዑዲ መድረሴን ለመንገር አንዴ ስልክ የደወልኩላቸው ነው» ይላል።  አረቡ ወላጆቹን እንዳሳዘናቸው ያምናል። ወላጆቹ ስለ የልጃቸው የስደት እቅድ የሰሙት ታላቅ ወንድሙ ደሴ መኪና ተራ ጠብቆ ከስደት ሊያስቆመው የሞከረ ጊዜ ነው።  « ደሴ ላይ ወንድማችን ያዘን። ብትገለኝም አልመለስም አልኩት። አለቀሰ እና ለአባቴ ደወለ። አባቴ እናትህን በህይወት አታገኛትም ተመለስ ብሎ ለመነኝ» ይላል አረቡ እሱ ግን በውሳኔው ገፍቶበት ጉዞውን ቀጠለ።
አቶ ሰይድ ለወላጅ እና ለቤተሰብ ሳይናገሩ ወጣቶች ለስደት መነሳሳታቸውን ቢቃወሙም ምክንያታቸውን ግን ይረዳሉ። «ሰላም የለም። ጦርነት አለ። የኑሮ ውድነት አለ» 
አረቡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ሳዑዲ በገባ በ 15 ቀኑ ስራ አግኝቷል። እረኛ ሆኖ ግመሎችን እና ፍየሎችን ይጠብቃል፤ እነሱን ያልባል። አብሮት የተሰደደው ጓደኛውም ይሁን መንገድ ላይ የተዋወቃቸው ጓደኞቹ የማታ ስራ አግኝተዋል። ይሁንና ሀገሪቷ ላይ ህገ ወጥ ናቸው። ደሞዝ ሊከለከሉም ሆነ ሊታሰሩ ይችላሉ። «በህጋዊ መንገድ የምሰደድበት ምንም አማራጭ በሰዓቱ አልነበረም ።» ይላል አረቡ። 

ኢትዮጵያውያን የሳዑዲ ተመላሾች
የባንግላዲሽ ስደተኞች በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤትምስል Osman Ali

ሰሞኑን የፌዴራል የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ከ163 ሺህ በላይ ወጣቶች ለውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ተመዝግበው ሥልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ። ስልጠናውን የሚወስዱ ወጣቶች ለዶይቸ ቬለ እንደተናገሩት ይህ በወጭ አገራት የሚደርስባቸውን እንግልት ሊቀንስ እንደሚችል እና በህጋዊ መንገድ እንደሚሰደዱ ተስፋ አላቸው። አቶ ሰይድ ግን ወጣቶቹ ሀገራቸው ላይ ሆነም የሚሰሩበት ሁኔታ ቢመቻች ይሻላል ይላሉ። « ይህንን እንደ አማራጭ ነው ማለት አልችልም። ምክንያቱም ከጥቅሙ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው። ወጣቱ በሀገሩ ላይ እንዲደራጅ መስራት ይገባዋል እንጂ እንዴት ወደ ውጭ! ይህ እኮ የባሪያ ግዥ ማለት ነው!»


ልደት አበበ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር