1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አትሌቲክስ ፤ እግር ኳስ እና የብስክሌት ውድድር

ሰኞ፣ ሐምሌ 1 2016

ከሀገር ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ፕሪምየር ሊግ ባደገበት ዓመት የሊጉ ሻምፒዮና ሆኗል። የኢትዮጵያ ቡና ደግሞ የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል። የአዲስ አበባ ስቴዲየምም ከአራት አመታት ዓመታት ገደማ በኋላ ዳግም በአዲስ ገጽታ ውድድር አስተናግዷል። 17ኛው የአውሮጳ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ ሃገራትን ለይቶ አሳውቋል።

https://p.dw.com/p/4i0qf
Addis Ababa Stadium
ምስል Omna Tadel

የሀምሌ 1 ቀን 2016 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት

እግር ኳስ

ከሀገር ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ፕሪምየር ሊግ ባደገበት ዓመት የሊጉ ሻምፒዮና ሆኗል። የኢትዮጵያ ቡና ደግሞ የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል። የአዲስ አበባ ስቴዲየምም ከአራት አመታት ዓመታት ገደማ በኋላ ዳግም በአዲስ ገጽታ ውድድር አስተናግዷል።

ባለፈው ሳምንት ፍጻሜውን ባገኘው እና ብርቱ ፉክክር በታየበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ንግድ ባንክ ሻምፒዮና መሆን ችሏል። ንግድ ባንክ ባለፈው ቅዳሜ  በሳላሳኛውን ሳምንት ጫወታ ኢትዮጵያ መድንን 2 ለ0 በማሸነፍ ነጥቡን 64 በማድረስ ነው ሻምፒዮናነቱን ያረጋገጠው ። መቻል ኢትዮጵያ ቡና እና ባህርዳር ከነማ በ63 ፣ 51 እና 50 ነጥቦች ከሁለት እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል። ሻሸመኔ ከተማ እና አምበሪቾ በ17 እና 9 ነጥቦች ከሊጉ ወርደዋል። የሐዋሳ ከተማው አጥቂ አሊ ሱለይማን በ20 ጎሎች የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል። የንግድ ባንኩ አሰልጣኝም ከከፍተኛ ሊግ ባደጉበት ዓመት የሊጉ ሻምፒዮን መሆን የቻሉ የእነ ገብረመድህን ኃይሌ ታሪክ መጋራት ችለዋል።

ጀርመን ሽቱትጋርት ውስጥ ደማቁ ድባብ ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት

የኢትዮጵያ ሻምፒዮና

በሌላ የሀገር ውስጥ የእግር ኳስ ውድድር በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ትናንት እሁድ ኢትዮጵያ ቡናን ከወላይታ ዲቻ ያገናኘው ግጥሚያ በኢትዮጵያ ቡና 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ከዓመታት በኋላ የአዲስ አበባ ስቴዲየምም የመጀመሪያ የሊግ ጫወታ አስተናግዷል። የጫወታውን ውጤት ተከትሎ የኢትዮጵያ ቡና ኢትዮጵያን ወክሎ የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተወዳዳሪ መሆኑን አረጋግጧል። ነገር ግን በጫወታው ወቅት በተለይ የወላይታ ተጫዋቾች  የዳኝነት በደል ደርሶብናል  በሚል ሁለተኛ ሲወጡ የሚሸለሙትን የብር ሜዳሊያ ሳይቀበሉ መቅረታቸው ተሰምቷል። ደጋፊዎችም ከፍተኛ ተቃውሞ በማሰማት የአዲስ አበባ ስቴዲየም ከዕድሳት በኋላ የመጀመሪያ ውድድር ባስተናገደበት ዕለት በርካታ ወንበሮች መሰባበራቸውን በማህበራዊ መገናኛዎች ሲንሸራሸሩ ታይተዋል።

የአዲስ አበባ ስቴዲየም
በሌላ የሀገር ውስጥ የእግር ኳስ ውድድር በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ትናንት እሁድ ኢትዮጵያ ቡናን ከወላይታ ዲቻ ያገናኘው ግጥሚያ በኢትዮጵያ ቡና 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ምስል Omna Tadel/DW

የአውሮጳ ዋንጫ

17ኛው የአውሮጳ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ ሃገራትን ለይቶ አሳውቋል። ስፔን ፣ ፈረንሳይ ፣ እንግሊዝ እና ኔዘርላንድስ ከብዙ በጥቂቱ እንደተገመቱት የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚነታቸው አረጋግጠዋል። ባለፈው ዓርብ በተለይ የአዘጋጇ ሀገር ጀርመን ከስፔን ያደረጉት ግጥሚያ እጅጉን ተጠባቂ ነበር እና ባልደረባችን ማንተጋፍቶት ስለሺ ወደ ደቡብ ምዕራባዊቷ ውብ ከተማ ሽቱትጋርት አቅንቶ ነበር ፤ ጀርመን በስፔን ከተሸነፈች በኋላ ደጋፊውጋ የነበረውን ድባብ ተመልክቷል ።

የስፔን ብሔራዊ ቡድን
17ኛው የአውሮጳ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ ሃገራትን ለይቶ አሳውቋል። ስፔን ፣ ፈረንሳይ ፣ እንግሊዝ እና ኔዘርላንድስ ከብዙ በጥቂቱ እንደተገመቱት የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚነታቸው አረጋግጠዋል።ምስል Matthias Schrader/AP Photo/picture alliance

ለአውሮጳ እግር ኳስ ጨዋታ ውድድር የጀርመን ቡዱን ዝግጅት

በቀሪ የአውሮጳ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ነገ ማክሰኞ ምሽት ስፔን ከፈረንሳይ ከዋንጫ በፊት የሚደረግ ብርቱ ፍልሚያ ይጠበቃል። ስፔን ጀርመንን 2 ለ 1 እንዲሁም ፈረንሳይ ስዊዘርላንድን በመለያ ምት 5 ለ3 በማሸነፍ ነው ግማሽ ፍጻሜውን የደረሱት ።  ሁለቱ ሃገራት እስካሁን በተገናኙባቸው 9 ዓለማቀፍ ውድድሮች ስፔን አምስቱን በማሸነፍ የበላይነት አላት ። ፈረንሳይ 3 ጊዜ አሸንፋለች ። አንድ ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። የሁለቱ ሃገራት ፍልሚያ ማክሰኞ ምሽት 4 ሰዓት የሙኒኩ አሊያንዝ አሬና ያስተናግዳል። የግማሽ ፍጻሜ ጫወታው ቀጥሎ ረቡዕ ምሽት በእንግሊዝ እና ኔዘርላንድ መካከል ይደረጋል። የብርትኳናማዎቹ የማሸነፍ ታሪክ በሚያመዝንበት የሁለቱ ሃጋራት የግማሽ ፍጻሜ ፍልሚያ እጅጉን ተጠባቂ ነው።

የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን
የግማሽ ፍጻሜ ጫወታው ቀጥሎ ረቡዕ ምሽት በእንግሊዝ እና ኔዘርላንድ መካከል ይደረጋል። የብርትኳናማዎቹ የማሸነፍ ታሪክ በሚያመዝንበት የሁለቱ ሃጋራት የግማሽ ፍጻሜ ፍልሚያ እጅጉን ተጠባቂ ነውምስል Bernadett Szabo/REUTERS

በአትሌቲክስ ዜና

ትናንት እሁድ ምሽት ፓሪስ ባስተናገደችው የዲያመንድ ሊግ ኢትዮጵያውያን ያሸነፉበት ውድድር ተደርጓል። ኢትዮጵያዊው አብረሃም ስሜ በ3 ሺ ሜትር መሰናክል አሸንፏል። በፓሪስ ዳያመንድ ሊግ የአትሌቲክስ ውድድር ኢትዮጵያውዊው አብርሃም ስሜ በ3ሺህ ሜትር መሰናክል አሸነፈ። ትናንት ምሽት የተካሄደውን ይህን ውድድር አትሌት አብርሃም የጨረሰው በ8 ደቂቃ 2 ሰከንድ ከ36 ማይክሮ ሰከንድ ነው።አብርሃም ውድድሩን በሁለተኛነት የጨረሰውን ኬንያዉውን አሞስ ሴሬምን ያሸነፈው በሽርፍራፊ ማይክሮ ሰከንዶች ቀድሞ ነው። ሩጫው ጥሩና ፈጠን እንደነበር የገለጸው አትሌት አብርሃም ውድድሩን እጅግ ስኬታማ የሆንኩበት ብሎታል፤የራሱንም ምርጥ ሰዓት አስመዝግቦበታል። ከሦስት ሳምንት በኋላ ፈረንሳይ ውስጥ ለሚጀመረው ለኦሎምፒክ ውድድር እየተዘጋጀ መሆኑን የገለጸው አብርሃም በኦሎምፒክ የሚሰለፍ ከሆነ የተሻለ ውጤት አመጣለሁ ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግ ተናግሯል። በፓሪሱ ኦሎምፒክ  በወንዶች የ3000 ሜትር መሰናክል የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት ለሜቻ ግርማን ጨምሮ ሦስት አትሌቶች ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ።እስካሁን ባለው መረጃ  አብርሃም ስሜ በተጠባባቂነት ነው የተያዘው። 

 በዓለም ከቀዳሚዎቹ በሚጠቀሰው ቱር ዲ ፍራንስ የብስክሌት ውድድር ኤርትራዊው ቢኒያም ግርማይ አዲስ ታሪክ ሰርቷል።

ብስክሌተኛ ቢኒያም ግርማይ
በዓለም ከቀዳሚዎቹ በሚጠቀሰው ቱር ዲ ፍራንስ የብስክሌት ውድድር ኤርትራዊው ቢኒያም ግርማይ አዲስ ታሪክ ሰርቷል።ምስል Daniel Cole/AP/picture alliance

ቢኒያም  ግርማይ በርካታ ዙሮች እና የአውሮጳ ሃገራትን  በሚያካልለው የቱር ዲ ፍራንስ ባለፈው ሰኔ 23 ቀን 230 ነጥብ 8 የሸፈነውን ሶስተኛውን ዙር በማሸነፍ ለራሱ ለሃገሩ ብሎም ለጥቁር አፍሪቃውያን አዲስ ታሪክ መጻፉ ይታወሳል። ብርቱ ፉክክር በሚደረግበት በዚሁ የቱር ዲ ፍራንስ የብስክሌት ውድድር ቢኒያም በድጋሚ ባለፈው ቅዳሜ 183 ኪሎ ሜትር የሸፈነውን  ስምንተኛው ዙር ማሸነፍ ችሏል። ይህም ለእርሱ ሌላ ተጨማሪ ታሪክ ሆኖለታል።

ታምራት ዲንሳ

ፀሐይ ጫኔ