1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አረና ትግራይ ለረሐብ አደጋው ሕወሓት ትኩረት አልሰጠም ሲል ወቀሰ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 4 2016

በትግራይ ክልል ለተከሰተው ብርቱ የረሃብ አደጋ የክልሉ እና ፌደራል መንግስት ትኩረት አልሰጡትም ሲል ተቃዋሚው ዓረና ትግራይ ወቀሰ ። ዓረና ትግራይ፦ ሕዝብ በረሃብ እየሞተ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በፓርቲ «የውስጥ የስልጣን ሽኩቻ» ተጠምዷል ብሏል ።

https://p.dw.com/p/4a9n6
Äthiopien | Tigray Region Hungersnot
ምስል Million Hailesilassie/DW

ሕወሓት በፓርቲ «የውስጥ የስልጣን ሽኩቻ» ተጠምዷል ሲሉ ከሰዋል

በትግራይ ክልል ለተከሰተው ብርቱ የረሃብ አደጋ የክልሉ እና ፌደራል መንግስት ትኩረት አልሰጡትም ሲል ተቃዋሚው ዓረና ትግራይ ወቀሰ ።  ዓረና ትግራይ፦ ሕዝብ በረሃብ እየሞተ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በፓርቲ «የውስጥ የስልጣን ሽኩቻ» ተጠምዷል ብሏል ። የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ አስቸኳይ ምላሽ ለትግራይ የተባለ ሁሉን አቀፍ ቡድን በማቋቋም ለተራቡት ለመድረስ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጿል ።  እንደ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መረጃ፦በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል 2 ሚልዮን ዜጎች ለረሃብ ተጋልጠው ይገኛሉ ።

በትግራይ ክልል የከፋ ድርቅና ረሃብ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች መካከል በሆነችው አፅቢ ወረዳ የሚኖሩት እኝህ አባት አቦይ ፍፁም ብርሃን የዘንድሮው ድርቅና ያስከተለው ረሃብ የገለፁት "በሕይወት ዘመኔ አጋጥሞኝ የማያወቅ" ብለው ነው። አቦይ ፍፁም ብርሃን "ሰባሰባት ዓመተምህረት አልፏል። ሀምሳ አንድ ዓመተምህረትም ረሃብ ነበረ አልፏል። እንደዘንድሮው ዓይነት ድርቅና ረሃብ ግን አላየንም" ይላሉ። እንደ የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር መረጃ በአሁኑ ወቅት በትግራይ 2 ሚልዮን ዜጎች ለረሃብ ተጋልጠው ይገኛሉ። ረሃብ የወለደው ሞት፣ በሽታና ስደት መንሰራፋቱ ተገልጿል።

በትግራይ ክልል ያለው ረሃብ በተንሰራፋበት፥ የክልሉ አስተዳደር እና የፌደራሉ መንግስት በቂ ምላሽ እየሰጡ አይደለም የሚል ትችት ከተለያዩ ወገኖች ይሰነዘራል። በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ በረሃብ እየሞተ ያለው ህዝብ የሚታደግ እርምጃ ባለመውሰዱ የክልሉ አስተዳደር የሚመራው ህወሓትን ወቅሷል። የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ "ምንም ችግር እንዳልተፈጠረ፣ በድርጅታዊ የስልጣን ሽኩቻ ተጠምደው የትግራይ ረሃብ ትኩረት አላደረጉበትም" ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ አቶ ዓምዶም በትግራይ ያለው ረሃብ  ለመፍታት የኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ ለዓለም ማሳወቅ አለበት ብለዋል።

ትግራይ ክልል ረሐብ
ትግራይ ክልል፤ ስለ ረሐብ አደጋ ውይይት ምስል Million Hailesilassie/DW

ረሃብ ላይ ላሉ ዜጎች በጎ ፍቃደኛ ግለሰቦች በግል ከሚያደርጉት ውሱን ድጋፍ ውጭ ይህ ነው የሚባል የመንግስት ይሁን የዓለምአቀፉ እርዳታ ድርጅቶች ርዳታ እንደሌለ ይገለፃል።

የዓለም ምግብ ድርጅት እና ዮኤስአይድ ለትግራይ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ያቀርቡት የነበረ የምግብ ርዳታ ካቋረጡ 10 ወራት እንዳለፋቸዋል። እነዚህ ዓለምአቀፍ ተቋማት የርዳታ አቅርቦት ዳግም እንደሚቀጥሉ በቅርቡ ተስፋ የሰጡ ሲሆን ፥ ከዚህ ውጭም በትግራይ ክልል ላሉ የተራቡ ዜጎች ለማገዝ የክልሉ አስተዳደር፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፖርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት ያካተተ አስቸኳይ ምላሽ ለትግራይ የተባለ ኮሚቴ ተመስርቶ ገቢ ማሰባሰብ ጀምሯል። የትግራይ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን ኮምሽነር ዶክተር ገብረሕይወት ገብረእግዚአብሔር "የትግራይ የአስቸኳይ ምላሽ ኮሚቴ የመጀመርያው የስራ እቅድ አውጥቶ ወደተግባር ገብቷል" ሲሉ ገልፀዋል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ