1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አማራ ክልል በአዲስ ዓመት ዋዜማ የዋጋ ንረት

አለምነው መኮንን
ማክሰኞ፣ ጳጉሜን 5 2016

በአማራ ክልል አዲሱን ዓመት ተመልክቶ ምርቶች ወደ ገበያው የደረሱ ቢሆንም በሁሉም በሚባል ደረጃ በምርቶች የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ነዋሪዎች ተናግረዋል ። የክልሉ መንግስት በበኩሉ የምርት እጥረት እንዳይፈጠር አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ዐሳውቋል ።

https://p.dw.com/p/4kTLq
Äthiopien | Markt in Bahir Dar
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

አማራ ክልል የአዲስ ዓመት ዋዜማ የገበያ ዋጋ ንሯል

በአማራ ክልል አዲሱን ዓመት ተመልክቶ ምርቶች ወደ ገበያው የደረሱ ቢሆንም በሁሉም በሚባል ደረጃ በምርቶች የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ነዋሪዎች ተናግረዋል ። የክልሉ መንግስት በበኩሉ የምርት እጥረት እንዳይፈጠር አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ዐሳውቋል ።

አዲሱን 2017 ዓ.ም ለመቀበል ተዘዋውረንና በስልክ ያነጋገርናቸው የአማራ ክልል ነዋሪዎች እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጠዋል፡፡ የቢቸና፣ የደብረማርቆስ፣ የባህር ዳር፣ የእንጅባራ፣ የደብረወርቅ፣ የጎንጂ ቆለላ፣ የሸዋሮቢት፣ የጎንደርና የቆቦ ከተማ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት ህብረተሰቡ ምንም እንኳ በጦርነት፣ በመንገድ መዘጋጋትና በዋጋዎች መጨመር ቢማረርም አዲሱን ዓመት በተስፋ ለመቀበል በቻለው መጠን ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡

አንድ የጎንደር ከተማ ነዋሪና የባህር ዳር ከተማ ሸማቾች ምርት ገበያ ላይ ቢኖርም ዋጋቸው ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዋ እንደሚሉት ሽንኩርት ከሳምንት በፊት ከነበረበት 110 ብር ለኪሎ ዛሬ 140 ብር ገብቷል፣ ዶሮ እስከ 1400 ብር እየተሸጠ ነውም ብለዋል፡፡ ሁሉም ሸቀጦች ዋጋ መጨመራቸውን ነው እኚህ አስተያየት ሰጪ የሚገልፁት፡፡ የጎንደር ከተማ ነዋሪውም ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ "ገበያ ላይ ምርት ቢኖርም ዋጋው ግን በጣም ከፍተኛ ነው” ብለዋል፡፡

በሰሜን ሸዋ ዞን የሸዋ ሮቢት ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው ከዓመት በዓሉ በፊትም ቢሆን የዋጋ ጭማሪው በነዋሪው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየፈጠረበት ነው ብለዋል፡፡ "ሽሮ ገዝቶ ለመብላት ሰው አቅም እያጠረው ነው” ሲሉ ያለውን የዋጋ ንረት ገልጠውታል፡፡ ዘይት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እንዳለው የጠቀሱት የሸዋ ሮቢት ነዋሪው፣ ጤፍ እስከ 14 ሺህ ብር በኩንታል መሸጡን ይገልፃሉ፡፡

የቆቦ ከተማ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው አሁን አሁን ለቅንጦት የሚገዛው የምግብ እህል ቀርቶ በልቶ ለማደር ፈተና እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ እያንዳንዱ ምርት ጭማሪ ማሳየቱን በምሬት የሚናገሩት እኚህ አስተያየት ሰጪ ሽንኩርት 130 ብር በኪሎ ደርሷል ነው ያሉት፡፡ ጤፍ ፣አተር፣ ባቄላና ሌሎች ምርቶችም ዋጋቸው በጣም ማደጉን አስረድተዋል፡፡

በአማራ ክልል የእንጂባራ ከተማ አስተያየት ሰጪ እንደነገሩን አንድ በግ እስከ 17 ሺህ ብር ዋጋ ተቆርጦለት እየተሸጠ ሲሆን የአንድ ሰንጋ ዋጋ 100 ሺህ ብር ደርሷል ነው ያሉት፡፡  የአማራ ክልል  ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አቢታ ገበየሁ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 7ሺህ በሚጠጉ ነጋዴዎች ላይ የተለያየ ርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል መንግስት የምርት እጥረት እንዳይፈጠር አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ዐሳውቋል
የአማራ ክልል መንግስት የምርት እጥረት እንዳይፈጠር አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ዐሳውቋል ምስል Alemnew Mekonnen/DW

5ሺህ 187 ነጋዴዎች ላይ ማስጠንቀቂያ፣ 2ሺህ529 ንግድ ቤቶች ላይ የማሸግና በ33 ነጋዴዎች ላይ ደግሞ ክስ መመስረቱን አቶ አቢታ ገልጠዋል፣ በ38 የሉካንዳ ቤቶች ላይም ልተገባ ጭማሪ በማሳየታቸው ቅጣት እንደተጣለባቸው አመልክተዋል፡፡ የአቅርቦት እጥረት እንዳይኖርም ከአቅራቢዎችና ከአምራቾች ጋር በተደረሰ ስምምነት መሰረት ግብዓቶች ወደ ገበያው እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህም መሰረት ከ360 አምራቾች ጋር ስምምነት በመፍጠር ወደ 3 ሚሊዮን እንቁላል ወደ ገበያ እንዲደርስ ጥረት መደረጉን፣ ከ407 ዶሮ አቅራቢዎች ጋር በተደረሰ ስምምነት መሰረትም 300ሺህ ዶሮዎች ወደ ገበያ የሚያቀርቡ ይሆናል፣ 686 ወተት አቅራቢ ድርጅቶች ደግሞ 4 ሚሊዮን ሊትር ወተት እንዲያቀርቡ ስምምነት መደረሱን ተናግረዋል፣ 686 የዳልጋ ከብት አድላቢዎች 65ሺህ እንስሳት ወደ ገበያ የሚያቀርቢ ሲሆን 679 አቅራቢዎች ደግሞ 130ሺህ በግና ፍየሎችን የሚያቅርቡ እንደሚሆን ኃላፊው ገልጠዋል፡፡ ከመደበኛ የገበያ ማዕከላት በተጨማሪ በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች ተጨማሪ 114 ገበያ ማዕከላት መዘጋጀታቸውንም አብራርተዋል፡፡

24 ሚሊዮን ሊትር የፓልም ዘይት  ለአማራ ክልል የተመደበ ቢሆንም እስካሁን ወደ ክልሉ የደረሰ ከ2.4 ሚሊዮን ሊትር እንደማይበልጥ አብራርተዋል፣ 49ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ስኳር ለአማራ ክልል ከማዕከል ለነሐሴ ወር የተመደበ ቢሆንም እስካሁን የደረሰው ከ11 ሺህ ኩንታል አይበልጥም ነው ያሉት፤ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በፀጥታ ምክንያት መንገዶች በተደጋጋሚ ስለሚዘጉ እንደሆነ አቶ አቢታ ተናግረዋል፡፡ በብዙ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ሁኔታ እየተሸሻለ ቢሆንም በሽንኩርት ዋጋ ላይ ግን አሁንም መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ቢሮው ቀደም ሲል ለዶቼ ቬሌ በሰጠው መግለጫ ዐሳውቋል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ