1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ንድፍአፍሪቃ

ኑሃሚን ትርፌ - የዳና ዲዛይን መስራች

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ግንቦት 30 2016

ኑሃሚን ትርፌ በአጭር ጊዜ ውስጥ በፋሽን ዲዛይን ስራ ተሰማርታ ስራዎቿን ከሀገር ውጪ ድረስ ለማስተዋወቅ የበቃች ወጣት ኢትዮጵያዊት ናት። በቅርቡ ናይሮቢ በተካሄደው የምስራቅ አፍሪቃ የጨርቃጨርቅ እና የቆዳ ዓውደ ርዕይ ስላቀረበቻቸው ስራዎቿ እና «ዕውን አደረኩት» ስለምትለው የልጅነት ህልሟ የምትለን ይኖራል።

https://p.dw.com/p/4gkVf
ኑሃሚን ትርፌ ዳና ሞዴሎች
ኑሃሚን ትርፌ ዳና በኬንያ ናይሮቢ በተካሄደው እና East Africa Textile and Leather Week በተሰኘ የምስራቅ አፍሪቃ የጨርቃጨርቅ እና የቆዳ ዓውደ ርዕይ ላይ ስራዎቿን ስታስተዋውቅ ምስል tallam_pixels

«ኮሮናን ማመስገን ባይቻልም ትክክለኛው ፍላጎቴን ያሳየኝ ነው»

ኑሃሚን ትርፌ ዳና ትባላለች። ከአንድ ዓመት በፊት ያቋቋመችው ዳና ዲዛይን ባለቤት ናት። « ዳና ያው የአያቴ ስም ነው። ግን ብራንዴ ላይ ሳስገባው ሁለት አይነት ትርጉም እንዲይዝ አድርጌ ነው። አንድ አያቴን ማስታወሻ ነው።  ሁለተኛው ደግሞ ዳና የሚለው ቃል የእግር አሻራ እንደማስቀመጥ ማለት ነው። እኔ ደግሞ እዚህ የፋሽን ዲዛይን ኢንዱስትሪ ላይ አንድ አሻራ ጥዬ ማለፍ እፈልጋለሁ።» ትላለች። ስለሆነም ይህንን ስሟን ይዛ ከሁለት ሳምንት በፊት በኬንያ ናይሮቢ በተካሄደ እና East Africa Textile and Leather Week በተሰኘ የምሥራቅ አፍሪቃ የጨርቃጨርቅ እና የቆዳ ዓውደ ርዕይ ላይ ተካፍላለች። « እንደ አሻራ ምን መቀመጥ ይችላል የሚለውን ነገር ሳነሳ አንድ ያገኘሁት ትልቁ ነገር የኢትዮጵያ የሆነውን ጋቢ ወይም ፈትል የምንለውን በእጅ ተደውሮ ተሸምኖ እኔ እጅ እስኪገባ ድረስ ያለውን ጋቢን ወሰድኩ እና ምን አይነት ነገሮችን ብጠቀም በዓለም አቀፍ ደረጃ መግባቢያ የሆነ ነገር መፍጠር እችላለሁ ብዬ ሳስብ የማሊ «መድ አርት» የሚባለውን አገኘሁ።» 

ከማሊ «መድ አርት»ጋር ባህላዊ ትስስር

ይህም ኑሃሚን ናይሮቢ ላይ ካቀረበቻቸው የሥራዎቿ አንዱ ማሳያ ነው። ባህላዊ ትስስር መፍጠር ፍላጎቷ እንደነበር የገለፀችልን ኑሃሚን ከ 1000 ዓመት በላይ እንዳስቆጠሩ የሚነገርላቸውን የማሊ ምልዕክቶች በሥራዎቿ ላይ ያካተተችው በጥቁር ቀለም ነበር። ይህም «በነጩ ጋቢ ላይ ተቃራኒ ቀለሞቹ በደንብ ጎልተው ስለሚታዩ ነው » ስትል ለምን ለሁለቱ ቀለማት ብቻ እንደወሰነች ኑሃሚን ታብራራለች።  ጥንት ላይ ማሊያውያን የተለያዩ ትርጓሜ ያላቸውን ምልዕክቶች በእጅ ሥራዎቻቸው ላይ ለመጠቀም ከወንዝ ዳር የሰበሰቡትን እና ለረዥም ጊዜ ያስቀመጡትን ጭቃ ይጠቀሙ ነበር።

የኑሃሚን የልብስ ንድፎች ከማሊ ታሪካዊ ምልዕክቶች ጋር የተዋሀዱ ብቻ ሳይሆኑ እንደ የኢትዮጵያዊ የባህል ልብስም ቀለል ያሉ እና ዘመናዊ የሚባሉ ናቸው። ይህም ባህላዊ ልብሶቹ ዘላቂነት እንዲኖራቸው ይረዳል ትላለች ኑሃሚን፤« ለዚህም አንድ የምጠቀመው ነገር አለ። «ይህ አለባበስ ኢትዮጵያዊነትን ባለቀቀ መልኩ፤ በሚስብ እና ባልተለመደ መልኩ ፤ ዕለት ከዕለት፣ ቢሮ፣ መዝናኛ ቦታዎች ላይ ፣ ድግሶች ላይ እንዲለበሱ የማድረግ ሥራ ነው እየሰሠሁ ያለሁት።»

ኑሃሚን ሥራዋን መድረክ ላይ ለብሰው ያስተዋወቁላት ሞዴሎችን የመረጡት አዘጋጆቹ ነበሩ። እሷ እንደምትለው አብዛኞቹ ኬንያውያን ሲሆኑ ጥቂት ሱዳናውያንም ይገኙበታል። « የሞዴሎቹ ልኬት ሲላክልኝ፤ ይኼኛውን ልብስ ለእሷ ይኼኛውን ለሌላኛዋ ብዬ የተወሰነም ጨምሬበት በዛ መልኩ ነው የሠራሁላቸው»

ወንድ ሞዴል
የማሊ ምልዕክቶቹ አንድ ምንም አይነት ፍርኃት የሌለው ጀግና ወንድን ያመላክታሉ ትላለች ኑሃሚን ትርፌምስል tallam_pixels

ለ3ኛ ጊዜ የተካሄደው የጨርቃጨርቅና የቆዳ ውጤቶች ዓውደ ርዕይ

በጨርቃ ጨርቅ እና የቆዳ ውጤቶች ላይ ያተኮረው East Africa Textile and Leather Week ዘንድሮ ለሦስትተኛ ጊዜ የተዘጋጀ ሲሆን ከ 30 ሃገራት የተውጣጡ ከ 3000 በላይ ነጋዴዎች ተሳታፊ እንደነበሩ የዝግጅቱ ድረ ገፅ ላይ ይነበባል። ኑሃሚን ከኢትዮጵያ ብቸኛዋ ተሳታፊም አልነበረችም፤« ሞዴሎችን ይዘን የቀረብን ሁለት ነበርን። ከዛ በተረፈ አንድ በቆዳ ኢንዱስትሪ ላይ የተሰማሩ ነበሩ። ሌሎች ደግሞ በኢንዱስትሪ ደረጃ ከፍ ያሉ እና የሚያስተዋውቁ ነበሩ። ዘንድሮ ለምሳሌ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ሆስቴሶች የሚለብሱትን የሀበሻ ልብስ የምታዘጋጀው እጅግ ጥበብ ነበረች ። ፋሽን ዲዛይን ዘላቂለት እንዲኖረው በትልልቅ ውይይቶች ላይ ተሳታፊ ነበረች።  »
ኑሃሚን በዚህ ዝግጅት ላይ ስትሳተፍ ሁለተኛ ጊዜዋ ቢሆንም ብቸዋን የዳና ዲዛይን ሥራዎችን ስታቀርብ ግን የመጀመሪያዋ ነው።« የዛሬ ዓመት ከሌላ ፓርትነር ጋር በትብብር ሠርቼያለሁ። ኔቸር እና ብሉ ላግን በሚል ርዕስ ወደ 14 ልብሶች ሠርተን ሄደናል። ይህንንም እድል ያገኘሁት ኢንስታግራም ላይ ያገኘሁትን ማስታወቂያ አይቼ ነው የተመዘገብኩት።»

ኑሃሚን እንዴት የልጅነት ፍላጎቴ ነበር ለምትለው ሙያ በቃች?

« ራሴን ሙሉ በሙሉ ሰጥቼ ወደ ፋሽን ኢንዱስትሪ የገባሁት በኮቪድ ወቅት ነው።ከዛ በፊት በሌላ ዘርፍ ላይ እየሠራሁ ነበር። የኮቪድ ሰዓት ግን በነገሮች መዘጋጋት ብዙ ሰዎች ላይ ጫና ፈጥሯል። ያኔ እኔም ማስክ መሥራት ጀመርኩ። የተለያየ ዲዛይን እያደረኩኝ እሠራ ነበር። ጥበቦችን፤ ጥለቶችን እየቀያየርኩ መሥራት ጀመርኩ። ከዛ በፊት ከሚራክል ዲዛይን ተቋም ኮርሶች ወስጄ ነበር። ሌላ ዘርፍ ላይ ቆይቼ እንድሠራበት ያደረገኝ ግን ኮቪድ ነው። ።»
ኑሃሚን ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ባገኘችው የመጀመሪያ ዲግሪ በትምህርት እቅድ አስተዳደር ዘርፍ ትምህርት ቤት ውስጥ ሠርታለች። ከዛ በኋላ ደግሞ  ወደ ፋሽን ሥራ ከመግባቷ በፊት በእርሻ መስክ ላይ የተሰማራ የአስመጪ እና ላኪ ድርጅት ውስጥም ትሠራ ነበር። ከአሁን በኋላ ግን በፋሽኑ ኢንዱስትሪ ላይ ብቻ ለመሥራት እቅድ አላት። ከ ጀርመን ተራድኦ ድርጅት  GIZ ያገኘችው የ6 ወራት ነፃ የፋሽን ዲዛይን ስልጠና እና የ150 000 ብር የፕሮጀክት ድጋፍ ህልሟን እውን ለማድረግ ረድቷታል። 

ሴት ሞዴል
«ኢትዮጵያዊነትን ባለቀቀ መልኩ፣ በሚስብ እና ባልተለመደ መልኩ ቢሮ፣ መዝናኛ ቦታዎች ላይ ፣ ድግሶች ላይ እንዲለበሱ የማድረግ ስራ ነው እየሰራሁ ያለሁት።» ትላለች ኑሃሚንምስል tallam_pixels

«ልብስ አትተብትቢ አጥኚ እየተባልኩ ብዙ ተገርፌያለሁ»

« ከልጅነቴ አንስቶ የአሻንጉሊት ልብስ እሠራ ነበር። ግን በእኛ ጊዜ ልብስ ሰፊ፣ አዝማሪ የሚባሉ ነገሮች የሚመከሩ አልነበሩም። እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ወላጅ የሚፈልገው ዶክተር፤ ፓይለት ነው የሚባለው። ልብስ ሰፊ ማለት የሚከብዳቸው ጊዜ ነበር። ዝምብለሽ ልብስ አትተብትቢ፤ አጥኚ እየተባልኩ ብዙ ተገርፌያለሁ። ግን ውስጤ ያለ ነገር ስለነበር ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተመርቄ እንደወጣሁ ነው ሚራክል ዲዛይን ሄጄ ለመመዝገብ የሞከርኩት። በመሀል ግን የተወሰኑ ፈተናዎች ስለነበሩ እነሱን ነገሮች እስኪያልፉ ሌላ ዘርፍ ላይ ልስራና ልመለስ አልኩኝ። መቼም ኮሮናን ማመስገን ባይቻልም ለእኔ ትክክለኛውን የህይወቴን አቅጣጫ ወይም ፍላጎቴ ያስገባኝ ኮቪድ ነው» የምትለው ኑሃሚን
ተስፋ አለመቁረጥ እና ጥረት ለሌሎች መሰል ፍላጎት ላላቸው ወጣቶች የምትመክረው ነገር ነው። « እዚህ ዝግጅት ላይ እጅጋየሁ እኔን ስትተዋወቀኝ ያለችኝ ነገር « በጣም ጠንካራ መሆን አለብሽ» ብላ እንደ ማስጠንቀቂያ ነው የነገረችኝ። ስለዚህ እኔም ለሌሎች ማስተላለፍ የምፈልገው እኔም እየታገልኩ የመጣሁበት ነገር አለ። ከእኔም በታች ላለ ይሔን ኢንዱስትሪ እየፈለገም ላልቻለ ሰው የምመክረው ጠንካራ እና ቆራጥ እንዲሆን ነው» ትላለች በአጭር ጊዜ ውስጥ በፋሽን ዲዛይን ሥራ ተሰማርታ ሥራዎቿን ከሀገር ውጪ ድረስ ለማስተዋወቅ የበቃች ኑሃሚን ትርፌ ።

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሠ