1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወጣት ሥራ አጥነት እና ሕገ-ወጥ ስደት በትግራይ

ማክሰኞ፣ ጥር 14 2016

በትግራይ የወጣቶች ሥራ አጥነት እና ሕገ-ወጥ ስደት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለፀ። የኢትዮጵያ ሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በመጀመርያ ዙር በትግራይ ለሚገኙ 2 ሺህ ወጣቶች የስልጠናና ፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ መጀመሩ፥ ከዚህ ውጭም የተለያዩ ፕሮጀክት እየተገበረ እንደሚገኝ አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/4barz
እያሻቀበ የመጣዉ ስራ አጥነት በትግራይ
ሥራ ፈላጊ ወጣት በትግራይ ምስል Million Hailesilassie/DW

ስራ አጥነት የወለደው የወጣቶች ስደት አሳሳቢ ሆንዋል

በትግራይ የወጣቶች ስራ አጥነት እና ሕገ-ወጥ  ስደት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለፀ። የክልሉ አስተዳደር ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር የፋይናንስ እጦት ፈተና እንደሆነበት ይገልፃል። በጦርነቱ ምክንያት ከስራ ውጭ የሆኑ ጨምሮ ሌሎች ወደ ስራ ለመመለስ እየጣረ መሆኑ የሚገልፀው የኢትዮጵያ ስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በመጀመርያ ዙር በትግራይ ለሚገኙ 2 ሺህ ወጣቶች የስልጠናና ፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ መጀመሩ፥ ከዚህ ውጭም የተለያዩ ፕሮጀክት እየተገበረ እንደሚገኝ አስታውቋል።

በትግራይ በተለይም ከጦርነቱ በኃላ በዋነኛነት ስራ አጥነት የወለደው የወጣቶች ስደት በከፍተኛ መጠን እያሻቀበ መምጣቱ የመንግስት እና ሌሎች ተቋማት መረጃዎች ያመለክታሉ። መነሻቸው ከትግራይ የተለያዩ ከተሞች እና ገጠር ቀበሌዎች ያደረጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ወደ ዓረብ፣ አውሮፓ እና አፍሪካ ሀገራት ለመድረስ በሕገወጥ መንገድ አስቸጋሪው እና አደገኛው ጉዞ እንደሚያደርጉ የትግራይ ወጣቶች ቢሮ ይገልፃል።

በትግራይ ከጦርነቱ በኃላ የተበራከተ የወጣቶች ስራ አጥነት እና ስደት ለመቀነስ ያለመ እንቅስቃሴ መጀመሩ የሚገልፀው የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር፥ ለዚህም በክልሉ ለሚገኙ ወጣቶች ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ስልጠና እና የፋይናንስ ድጋፍ መስጠት መጀመሩ ይፋ አድርጓል። ትላንት በመቐለ በተደረገ ስነስርዓት የተናገሩት የኢትዮጵያ ስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ወይዘሮ ሙፈርያት ከሚል፥ በመጀመርያ ዙር ለ2 ሺህ ወጣቶች ስልጠናና ለእያንዳንዱ 50 ሺህ ብር መነሻ ገንዘብ መመደቡ አስታውቀዋል።

በትግራይ የስራ ፈጠራ እንቅስቃሴ አካል የተባለ፥ 65 ሚልዮን ብር በመመደብ በክልሉ የሚገኙ የቴክኒክ እና ሙያ ማሰልጠኛ ማእከላት የመደገፍ እንዲሁም 3 ሺህ የሚሆኑ ኢንተርፕራይዞች ወደ ስራ የመመለስም ጥረት እንደሚደረግ በሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ተገልጿል። ከበርካቶች መካከል በመጀመርያ ዙር የስልጠናና ስራ ዕድል ያገኘችው ብርክቲ ተክላይ እንቅስቃሴ በአወንታ የሚታይ ቢሆንም በትግራይ ካለው ችግር አንፃር ሁሉም ያካተተ እንዳልሆነ ትናገራለች። ብርክቲ "የነበራቸው ስራ ያጡ፣ አልያም ከመጀመርያውም ስራ ያልነበራቸው በርካቶች አሁንም የስራ ዕድል ጠባቂ ናቸው። በትንሹም ቢሆን ይህ መጀመሩ መልካም ቢሆንም በርካቶችን ማካተት አለበት ነው የምለው" ባይ ናት። 

የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ለወጣቶች ስራ ፈጠራትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ስለመሆኑ የሚገልፅ ሲሆን ይሁንና የመነሻ ካፒታል ችግር ፈተና መሆኑ ያነሳል። የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ጨምሮ ዓለምአቀፍ ተቋማት በጦርነት ላይ ለቆየችው ትግራይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጥሪ የሚያቀርበው አስተዳደሩ ሰላሙ ዘላቂ እንዲሆንም ለወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት እንዲደረግ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ ጥሪ አቅርበዋል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ