1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትግራይ ክልል ሰብአዊ ሁኔታው የከፋ ሆኖ ቀጥሏል ተባለ

ረቡዕ፣ የካቲት 13 2016

መሻሻሎች ቢታዩም ከጦርነቱ በኋላም በትግራይ ክልል ያለው ሰብአዊ ሁኔታ የከፋ ሆኖ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮምሽን (ኢሰመኮ) ዐስታወቀ ። ኮምሽኑ ያወጣው የክትትል ዘገባ እንደሚያሳየው አሁንም የዜጎች መፈናቀል ቀጥሏል ። በጦርነቱ የተፈናቀሉ ዜጎች በአቅርቦት እጦት እየተሰቃዩ መሆኑንም አመላክቷል ።

https://p.dw.com/p/4ch68
በትግራይ ክልል በትግራይ ክልል የሰብአዊ ቀውስ
በትግራይ ክልል በትግራይ ክልል የሰብአዊ ቀውሱ አሳሳቢ ነው ተብሏልምስል Mariel Mueller/ Haileselassie Million/DW

በትግራይ ክልል ያለው ሰብአዊ ሁኔታ የከፋ ሆኖ መቀጠሉ ተገለጠ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ትናንት ያወጣው የክትትል ዘገባ እንደሚያሳየው፥ ከጦርነቱ በኋላ ባለው ግዜ ጭምር በክልሉ የከፋ ሰብአዊ ሁኔታ መቀጠሉ ገልጿል ። በጦርነት ላይ የነበረው አካባቢ የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦት ተቆርጦበት መቆየቱ፥ ችግሩን የከፋ እንዳደረገው አመላክቷል። በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ በትግራይ የሚገኙ ዜጎች በከፋ የረድኤት አቅርቦት ችግር ላይ መሆናቸው ባደረገው ዳሰሰ የጠቆመው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮምሽን፥ ከሰላም ስምምነቱ በኋላም ቢሆን በተለይም ተፈናቃዮች በረሃብ ምክንያት የሚሞቱበት ሁኔታ መኖሩ፥ ተፈናቃዮቹ ወደ ቀዬአቸው የመመለስ እና የማቋቋም ሥራም ውሱንና ያልተፈፀመ መሆኑ የክትትል ዘገባ ያመለክታል።

ዜጎችን በኃይል ማፈናቀል አሁንም መቀጠሉን ያነሳው የኢሰመኮ ዘገባ እንደ ክልሉ ባለስልጣናት መረጃም 12 ሺህ አዳዲስ ተፈናቃዮች በቅርቡ ከቀየአቸው መፈናቀላቸው መዝገቡ ንገልጿል። የዜጎች የጤና እና ትምህርት አገልግሎት የማግኘት መብትም እንዲሁ የተወሰኑ መሻሻሎች ቢኖሩትም አሁንም ፈተና እየገጠመው መሆኑ የኢትዮጵያ ስብአዊ መብቶች ኮምሽን የክትትል ዘገባ አመላክቷል። በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮምሽን የክትትል እና ምርመራ ሪጅናል ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ ለዶቼቬለ እንዳሉት የሰብአዊ ድጋፍ መደናቀፍ የከፋ ቀውስ ፈጥሮ ቆይቷል።

በክትትሉ መቐለን ጨምሮ የክልሉ ማእከላዊ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ ዞኖች ማካለሉ የሚገልፀው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮምሽን በክልሉ የፀጥታ ሐይሎች በተጠርጣሪዎች እና እስረኞች አያያዝ ላይ የነበራቸው ክፍተትም አትቷል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮምሽን (ኢሰመኮ)
በትግራይ ክልል ስላለው ሰብአዊ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮምሽን (ኢሰመኮ) ዘገባ አቅርቧል ምስል Solomon Muche/DW

የሰብአዊ መብቶች ኮምሽኑ በትግራይ በተለይም የፆታ ጥቃቶች እና ጥቃቱ ለደረሳቸው የሚደረግ ድጋፍ እና ክትትል አለመኖር አሳሳቢ መሆኑ አንስቷል። በኮምሽኑ የክትትል እና ምርመራ ሪጅናል ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ "በማሕበረሰቡ የባህል ጫናዎች ምክንያት ራሳቸው ያላወጡ እና፥ የሕክምና ድጋፍ ያላገኙ የፆታ ጥቃት ሰለባዎች አሉ" ሲሉ ገልፀዋል።

በትግራይ ያለ የከፋ ሰብአዊ ሁኔታ ለመግታት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት፣ የክልሉ አስተዳደር ጨምሮ የዓለምአቀፉ ተቋማት ተሳትፎ እንደሚፈልግም ኮምሽኑ አስታውቋል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ