1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረቱን በዩክሬኑ ጦርነት ላይ ያደረገዉ የቡድን 20 ጉባኤ

ረቡዕ፣ ኅዳር 7 2015

የቡድን 20 ጉባኤ ዛሬ ኢንዶኔዥያ ባሊ ላይ በይፍ ተጀምሯል። የዩክሬኑ ጦርነት፤ የዓለም የገጠማትን የኃይል አቅርቦትና የምግብ ቀውስ፤ ብሎም የኢኮኖሚ ውድቀት ስጋትን አበይት ርስሱ ያደረገዉ የቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ ፤ በሩሲያ ቻይናና በምዕራብ ሃገራት መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት የሚያሳይ ግን በአንድ ጠረቤዛ ዙርያ መቀመጣቸዉ ጥሩ ተብሎለታል።

https://p.dw.com/p/4JYck
Indonesien Bali | G20-Gipfel | Themenbild
ምስል Christoph Soeder/dpa/picture alliance

በቡድን 20ዉ ጉባኤ የሩሲያዉ የዉጭ ጉዳይ ሚ/ር ለጦርነቱ ዩክሬን ተጠያቂ አርድርገዋል።

በኢንዱስትሪ የበለፀጉት 20 የዓለም ሃገራት የሚሳተፉበት ጉባኤ ዛሬ ኢንዶኔዥያ ባሊ ላይ በይፍ ተጀምሯል። የዩክሬኑ ጦርነት፤ የዓለም የገጠማትን የኃይል አቅርቦት እና የምግብ ቀውስ፤ ብሎም የኢኮኖሚ ውድቀት ስጋትን አበይት ርስሱ ያደረገዉ የቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ ፤ በሩሲያ ቻይና እና በምዕራብ ሃገራት መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት የሚያሳይ ይሆናል ተብሎ ተገምቷል። እንዲያም ሆኖ የሃገራቱ በአንድ ጠረቤዛ ዙርያ ለዉይይት መቀመጥ ትርጉም አለዉ ተብሎለታል።

Indonesien | G20 Gipfel in Bali | Treffen Guterres und Lawrow
የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶንዮ ጉተረስና የሩስያ የዉጭ ጉዳይ ሚ/ር ሰርጌይ ላቭሮቭ በኢንዶኔዥያ ባሊ ቡድን 20 ጉባኤ ላይ ምስል SNA/IMAGO

ቡድን 20 ተብለዉ የሚጠሩት የዓለማችን በኢንዱስትሪ የበለፀጉት  ሃገራት ጉባኤ በኢንዶኔዥያዋ የመዝናኛ ከተማ ባሊ ላይ ዛሬ በይፋ ሲጀመር የዩክሬኑ ጦርነትም እንደቀጠለ ነዉ። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ የጀርመን ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ፣ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮ፣ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭን ጨምሮ የበለፀጉት ሃገራት መሪዎች እና ተጠሪዎች በዝግጅቱ ላይ ተገኝተዋል። የሩስያዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ፤ ፕሬዚዳንት ፑቲንን ተክተዉ ለስብሰባዉ ኢንዶኔዥያ ባሊ ትናንት ሲደርሱ የጤና እክል ገጥሟቸዉ ቀጥታ ሆስፒታል መግባታቸዉ ተዘግቦ ነበር። ነገር ግን ቆየት ብሎ ሰርጌይ ላቭሮቭ ስብሰባዉ እስኪጀመር  በኢንዶኔዥያዋ የመዝናኛ ደሴት ባሊ ላይ በሚገኘዉ ማረፍያ ቦታ ተዝናንተዉ መጽሐፍ ሲያነቡ መታየታቸዉ፤ ጉምቱዉ ባለስልጣን ወደ ጤና መመለሳቸዉን ማረጋገጫ ነዉ ተብሎላቸዋል። የቡድን 20 ጉባኤ አስተናጋጅ ሃገር የሆነችዉ የኢንዶኔዢያው ፕሬዝዳንት ጄኮ ዊዶዶ ዛሬ ጉባዔውን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር አባል ሃገራት ጦርነቱን እንዲቋጩ ጥሪ በማቅረብ ነዉ። ዊዶዶ ሌላ ምንም ምርጫ የለም ነዉ ያሉት።

Ukraine Krieg | Wolodymyr Selenskyj in Cherson
የዩክሬይኑ ፕሬዚዳንት ቭላዶሚር ዜሌንስኪ ምስል Ukraine Presidency/IMAGO

« ሌላ ምንም አማራጭ የለንም። ሁላችንም ለሕዝባችን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ህዝብም ኃላፊነት አለብን። ኃላፊነት የሚሰማው መሆን ማለት ዓለም አቀፍ ሕግጋቶችን እና የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር መሠረታዊ ድንጋጌዎችን ማክበር ማለት ነው ። ኃላፊነት አለብን ማለት፤ ጦርነትን ማቆም አለብን ማለት ነው ። ጦርነትን ካላበቃን ዓለምን ወደፊት ለማምጣን አስቸጋሪ ይሆንብናል። ጦርነቱ ካላበቃ ለአሁኑ እና ለመጭዉ ትውልድ የወደፊት ዕጣ ኃላፊነቱን መውሰድ ይከብደናል። ዓለምን መከፋፈል የለብንም። ዓለም በሌላ ቀዝቃዛ ጦርነት ዉስጥ እንድትወቅድ መፍቀድ የለብንም። »

ዩክሬይን የቡድን 20 አባል ሃገር ባትሆንም፤ በጉባዔዉ አዘጋጅ  ሃገር በኢንዶኔዢያዉ ፕሬዚዳንት ጄኮ ዊዶዶ የተጋበዙት የዩክሬይኑ ፕሬዚዳንት ቭላዶሚር ዜሌንስኪ፤ በጉባኤዉ ላይ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፤ አዉዳሚ ጦርነት የምታካሂደዉንም ሩስያ ማስቆም ይችላሉ» ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

«የሩሲያ አውዳሚ ጦርነት መቆም ያለበትና ሊቆም የሚችልበት ጊዜ አሁን እንደሆነ አምናለሁ። በየቀኑ መዘግየት ማለት አዲስ የዩክሬናውያን ሞት፣ በዓለም ላይ አዲስ ስጋት፣ እንዲሁም በሩሲያ እብደት ቀጣይነት ምክንያት የሚከሰተዉ ኪሳራ ማለት የዓለም ላይ ሁሉ ኪሳራ ማለት ነዉ።»

Indonesien G20 Olaf Scholz
የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ በቡድን 20 ጉባኤ ላይ ምስል Dita Alangkara/dpa/picture alliance

የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልስ ከጉባኤዉ ቀደም ብሎ በሰጡት መግለጫ «የዓለም ኤኮኖሚ እንዲያገግም ከተፈለገ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የጀመረችዉን ጦርነት ማስቆም ነው» ብለዋል። በቡድን 20 ጉባኤ ዋዜማ የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ሚኒስቴር ጃኔት ዬለን ፤ «የሩሲያን ጦርነት ማቆም ሥነ ምግባራዊ ግዴታ እና ለዓለም ኢኮኖሚ ማገገም፤ ማድረግ የምንችለው ከሁሉ የተሻለ ነገር ነው» ሲሉ ተመሳሳይ አስተያየትን ሰጥተዋል።

የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በቡድን 20 ጉባኤ ላይ ባሰሙት የመክፈቻ ንግግራቸዉ፤ የሞስኮዉን መንግሥትም ሆነ ቭላድሚር ፑቲንን በቀጥታ አላወገዙም። ይሁንና በዩክሬን ለተከሰተው ግጭት ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ እንዲሰጥ ነዉ ያሳሰቡት።። «በተደጋጋሚ እንደተናገርኩት በዩክሬን የተኩስ አቁም እንዲደረግ የዲፕሎማሲ መንገድን መፈለግ አለብን ።» ባለፈዉ መስከረም ሙዲ ፑቲንን ፊት ለፊት ባገኝዋቸዉ ጊዜ ግን « ፑቲን ያለንበት ዘመን የጦርነነት አይደለም» ሲሉ እረፍ ቢጤ ነገር ብለዋቸዋል።  ሩስያ ለህንድ ከፍተኛ የጦር ቁሳቁስ አቅራቢ ሃገር ስትሆን፤ ሩስያ ደግሞ ህንድ ለዓለም ከምታቀርበዉ የህክምና መድሃኒት አራተኛዋ ሸማች ሃገር ነች።

Indonesien Bali G20 Treffen Stills
በኢንዶኔዥያ ባሊ ላይ የቡድን 20 ጉባኤ ምስል Cheng Chunglan/DW

የቡድን 20 መሪዎች ያወጡት ባለ 16 ገፅ ረቂቅ የአዋጅ ንድፍ በዩክሬን የሚታየዉን  ጦርነት አጥብቆ ያወገዘ፤ በመላው ዓለም የኢኮኖሚ ቀውስ እንዲባባስ አስተዋጽኦ ማድረጉን አጉልቶ ያሳየ ነዉ።  ረቂቅ አዋጁ ላይ እንደተጠቀሰዉ «ቡድን 20 የደህንነት ጉዳዮችን ለመፍታት የተሰበሰበ ባይሆንም፤ መሪዎቹ ግን የደህንነት ጉዳዮች በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ ውጤት ሊኖራቸው እንደሚችል አምነው ይቀበላሉ» ይላል። የሩስያዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ፤ «የቡድን 20 ሃገራት የጉባኤዉን የጋራ መግለጫ ፖለቲካዊ ለማድረግ ሞክረዋል ሲሉ ተችተዋል። የዩክሬይን ጦርነት እና በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ያሳደረዉን ቀዉስ በመመልከት የጀመረዉ የቡድን 20 ጉባኤ ነገ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።  

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ