1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዘብጥያ የወረዱት የሰላም ሚኒስትር፤ የጀነራሉ ቃለ ምልልስ፤ ለፋኖ የቀረበ የሰላም ጥሪ

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 5 2016

ዘብጥያ የወረዱት ታዬ ደንደአ፤ ከሰላም ሚኒስትር ስልጣን በተጨማሪ፤ የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የኦሮሚያ ም/ቤት አባል ናቸዉ። ሌላዉ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያነስዋቸዉ ነጥቦች በርካታ ዜጎችን እያነጋገረ ነዉ። የአማራ ክልላዊ መንግሥት በበኩሉ የሰላም ጥሪ ማስተላለፉ በርካታ ዜጎችን አወያይቷል።

https://p.dw.com/p/4aDmk
የኢትዮጵያዉ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
የኢትዮጵያዉ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላምስል Fana Broadcasting Corporate

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ከሰላም ሚኒስትር ስልጣናቸዉ በዚሁ ሳምንት ሰኞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደብዳቤ እና ፊርማ ተነስተዉ፤ በነጋታዉ “መንግሥትን ለመጣል በማሴር” ተጠርጥረው ዘብጥያ የወረዱት አቶ ታዬ ደንደአ  ኢህአዴግን የተካው፤ የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የኦሮሚያ ምክር ቤት አባል ናቸዉ። አቶ ታዬ  በፓርቲው፣ በኦሮሚያ ክልል እና በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ቦታ ላይ ሰርተዋል። ከስልጣን እስከተነሱበት እስከ ታኅሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስም ከሁለት ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው አገልግለዋል።

እዚህ አገር በሀሳብ መለየት ሲሉ በፌስቡክ ላይ አስተያየታቸዉን የጀመሩት ጎበና በሻ ሹራሞ፤ እዚህ አገር በሀሳብ መለየት ማንም ብትሆን፤ ገዥዉ መንግስት ስም ለጥፎ ወደ ወህኒ የማውረድ ባህል መቼ ነው የሚቆመዉ? እሱ እራሱ ከስልጣን በጠመንጃ ተገዶ ሲወርድ ነው? ሲሉ በጥያቁ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

አረጋ ሴማ የተባሉ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸዉ፤ ከአንድ የሰላም ሚኒስትር የማይጠበቅ ነገር አይደለም ያደረገው፤ እንደውም ያነሠ እንጂ። ሲጀመር የጦርነቱ ነጋሪት ሲጎስም ተያይዞ የሚመጣውን እልቂትና ጉዳት ማሳየት ነበረበት። ግን ነገሩ  አድሮ ነው የገባው። ይህ ደግሞ፤ ከተጠያቂነት ባያድነውም፤ አስቀድሞ እጅ መሥጠቱ፤ ፓርቲውንም ጭምር ኃላፊነቱን እንዲወሥድ ምስክር ሆንዋል። ምናልባት እሥር ቤት ሆኖ የጸጸት ጊዜ ይኖረዋል፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን አጋርተዋል።

ታዬ ደንደአ
ታዬ ደንደአምስል Million Haileselasi/DW

ተፈራ ታዲሱ የተባሉ ሌላዉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ፤ የመንግሥቱን የአሰራር ስርአት ፣ መርህ መከተል ተቀዳሚ ግዴታው ነው። የሰላም ሚኒስትር ደኤታ ሲሆን የሚንስትሮች ምክር ቤቱን ውሳኔዎች እና የአሰራር ደንቦች መከተል ይጠበቅበታል። የፓርቲ አባልም፤ በተመሳሳይ አግባብ ነው የሚታየው። የተናገረው ነገር እውነት እና ትክክለኛ ቢሆን እንኳን፤ የመንግሥቱንም ሆነ የፓርቲውን መርህ ጥሷል።"ሌላ ተልዕኮ" ከሌለው በስተቀር፤ በመንግሥቱም ሆነ ፓርቲው ውስጥ መቆየት አልነበረበትም ። ከሥራ እና ከፓርቲ አባልነቱ በራሱ ጊዜ ለቆ በመውጣት ተመሳሳዩን እርምጃ መውሰድ ነበረበት። ከዚያ የተናገራቸው ነገሮች ቢያንስ ሚዛን ይደፉለት ነበር ። ግን በፓርቲ አባልነቱ እና በመንግሥት ባለስልጣንነቱያገኘውን መድረክ እና ልዩ ጥቅሞች "ለአክቲቪስትነት" ተጠቀመበት። ይህ በራሱ የጥቅም ግጭት (conflict of interest) ፈጥሮበታል ። የመርህም የፕሮሲጀርም ችግር አለበት። ከስራ መሰናበቱም ሆነ መታሰሩ፤ ብዙም የማይጠበቅ ነገር አልነበረም። መንግሥት ይህን ጉዳይ በቸልታ ቢያልፈው ኖሮ፤ ወደፊት በተመሳሳይ ለሚወስዳቸው ውሳኔዎች፤ ከፍተኛ ክፍተት ይፈጥርበት ነበር። ሲሉ ረዘም ያለ አስተያየት ጽፈዋል።

ወርቁ አስፋዉ ደሞ እንዲህ ይላሉ፤ ''ማወቅ እናውቃለን፤ ብንናገር እናልቃለን ''ብለው ነበር የደርግ ካድሬዎች። እነሆ ታሪክ እራሱን ደገመ ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

ታመነ ገበየሁ ፤ ሚኒስትሩ ትክክል አይደሉም ነዉ የሚሉት፤ ታዬ ብቻቸዉን አይደሉም ከስልጣን የተባረሩት። እነ ታከለ ኡማ፤ ገዱ አንዳርጋቸውን መጥቀስ  ይቻላል።  የርሳቸው ለየት የሚያደርገው በቀጥታ ትዛዝ ከርቸሌ መግባታቸውን ነው። እንደ ታከለ ለምን አልመለጡም? በምን ተማምነዉ  ነው አዲስ አበባ ቁጭ ብለው ሲናገሩ ቃላት መምረጥ ያቃታቸዉ? ጨፈጨፈ ብለው መወረፍቸዉ ትክክለኛ ትግል ነዉ ብየ አላምንም ብለዋል።

የሪያድ ማህበረሰብ ድምጽ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚም ተመሳሳይ አስተያየት ነዉ ያላቸዉ፤ ክቡር አቶ ታዬ በግል ሶሻል ሚዲያቸው፤ መንግስታቸው ላይ ሂስ ሲሰነዝሩ ይህ የመጀመሪያቸው ባይሆንም፤ የአሁኑን ከበፊቱ ለየት የሚያደርገው እና ለእስር የዳረጋቸው ፖለቲካዊ ብስልት በጎደለው ቃላት፤ መንግስትን በመተቸታቸው ነው። የሆነው ሆኖ የአቶ ታዬ ከኃላፊነት መነሳት እና በህግ ቁጥጥር ስር መዋል ከመቶ ሚሊዮን ህዝብ ሰላም እና ከሀገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት አንፃር ኢምንት ስለሆነ ይህን ያህል የሚጋነን አይደለም፤ ብለዋል።

ጤና ደስታ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይበበኩላቸዉ፤  ወይ ግፍ? ይላሉ በጥያቄ ምልክት ወይ ግፍ? ስልጣን ባላቸው ግዜ የኖሩበትን ቤት ዛሬ ሲታሰሩ ቤተሰቦቹን በ3 ቀን ውጡ ማለት? ምን አይነት ፍርድ ነው? ሲሉ በጥያቄ ምልክት አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል።

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተደራሽነት
የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተደራሽነትምስል STEFAN HEUNIS/AFP/Getty Images

የኢትዮጵያዉ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከአገር ዉስጥ መገናኛ ብዙሃን ጋር ያካሄዱት ቃለ ምልልስ እና ያነስዋቸዉ ነጥቦች በርካታ ዜጎችን ሲያነጋግር ነዉ የሰነበተዉ። በእርግጥ ቃለ ምልልሱን ተከትሎ ከተሰጡት አስተያየቶች መካከል ለሚዲያ የሚመጥን ማግኘት እጅግ ከባድ ሆንዋል ይሁንና አንድ ሁለቱን ይዘናል።  

ትንሳኤ ዳህሌ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ ፤ ሰላም አውርዱልን እና  ሰላም ብቻውን በቂያችን ነዉ ሲሉ ተማፅነዋል።  

ሳሚ ያለዉ ካሳ በአስተያየታቸዉ፤ ኢትዮጵያ ይላሉ ፤ ኢትዮጵያ በለየላቸው እብዶች መተዳደር ከጀመረች ድፍን አምስት ዓመት አለፈው ሲሉ አስተያየታቸዉን በአራት ነጥብ ዘግተዋል።  

ከፍያለዉ ካሎስ የተባሉ አስተያየት ሰጭ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላምና ሰላም ብቻ ነው ። ምክንያቱም ሰላም ለሕዝባችን መሠረታዊና የመኖር ዋስትና ነውና ነው ። በአንፃሩ ደግሞ ለሌሎች አካላት 'ሰላም' እንደ አማራጭና የቢዝነስ ማግኛ መንገድ (ስልት) የሚያገለግል ስለሆነ ፣ ሲፈልግ ግጭት ወይም ጦርነት ይፈጥራል። ሲያሻው ጦርነትን ያስቆማል።  አልያም ደስ ሲለው የግጭት ዕድሜ እንዲራዘም በማድረግ ' conflict business ' ያጧጡፋል። ተጨማሪ አዳዲስ አጀንዳዎችን ይፈጠራል።  የሕዝቡ የሰቆቃ ጊዜ ይራዘማል። ...ብቻ ግን...ሰላምን ማን ይጠላል ? ሲሉ በጥያቄ አስተያየታቸዉን ዘግተዋል።

ሃብታሙ ቦሩ የተባሉ ፤ ሌላ አስተያየት ሰጭ፤ መንግስት በምንም አይነት አገሪቱ የገጠማትን ችግር በሩቅ አሳቢነት በረጋና በማስተዋል ፣ ነፃነትን በሚያስቡ ሙያተኞች እየታገዘ ካልሰራ፤ ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ችግር ለመሻገር ከፍተኛ ፈተና እንደሚሆንባት መገንዘብ ይኖርበታል ሲሉ በቃል አጋኖ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል።

ታድዮስ አሰፋ የተባሉ አስተያየት ሰጭ ፤ የመጀመሪያው ጥያቄዬ ሲሉ አስተያየታቸዉን ይጀምራሉ፤ የመጀመርያዉ ጥያቄዬ፤ መከላከያ እና የፍትህ ሚንስትሮች ከፓለቲካ ነፃ እና ገለልተኛ ናቸው ከተባለ በዚህ ድርድር ውስጥ ለምን ገቡ? ሁለተኛው ጥያቄዬ፤ የሁለም ነገር ባለ መብት ህዝብ እንደመሆኑ አጠቃላይ ኢትዬጵያ ላይ የሚካሄዱ ድርድሮች ለምን ለህዝብ አይገለፁም (ብልፅግናም ቢሆን እኮ አንድ ፓርቲ እንጂ 100% የኢትዬጵያን ህዝብ አይወክልም፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን በአራት ነጥብ ደምድመዋል።  

ፋኖ
ፋኖ ምስል Marcello Valeri/ZUMA/picture alliance

በያዝነዉ ሳምንት ማክሰኞ የአማራ ክልላዊ መንግስት ተጨማሪ ደም መፋሰስን ለማስቀረት ሲባል በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪ አስተላልፏል። የሰላም ጥሪዉ ለሰባት ቀናት የሚቆይ እንደሆነም ተገልጿል። በሰባት ቀናት ዉስጥ በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ለሚሰጡ ኃይሎች የተኃድሶ ስልጠና ይሰጣቸዋል ይላል መግለጫዉ።   

የሐርላዎች ልጅ ነኝ የሚል ስም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ያላቸዉ ተጠቃሚ፤ አስባችሁታል ለሺህ ዘመናት የኢትዮጵያን ታሪክ ወደኋላ ከተመለከትን፤ እርስ በእርስ ስንጨፋጨፍ ነው እስካዛሬ ድረስ ያለነው። እስቲ በዚህ በኛ ዘመን እንኳን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ፤ የእርስ በእርስ ጭፍጭፍን ለማስቆም፤ ከፌደራል መንግሥት ውጪ የትኛውም አንጃ፤ ትጥቅ እንዳይታጠቅ፤ የዞን እና የክልል ፖሊሶችም፤ ከዱላ ሌላ እንዳይታጠቁ፤ ሁላችንም ትግል እናድርግ። የዛኔ እንደ አውሮፓና መካከለኛው ምሥራቅ አገራት፤ ዜጎቻችን በሠላም ወጥተዉ ይገባሉ፣ አገራችንም ታድጋለች ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

ያሬድ አሰፋ ይመር የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንበድሮን ንጹሐን እንደተጨፈጨፉ እየመሰከረ፣ ኤታማዦር ሹሙ የሚናገሩትን የሚያምን ኢትዮጵያዊ አለ ብለው ያስባሉ? ሲሉ በሁለት ጥያቄ ምልክት አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

አቡ አብዱል ከሬም መሃመድ የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጭ ፤ አማራ ሲሞት እና ሲፈናቀል እንዲሁም ሲታሰርና ሲዘረፍ የማይናገር የወረዳ አስተዳዳሪ የሸኔ ነገርን ለማራገብ ይራወጣል። አማራው ያለ ነፍጡ የሚታደገዉ አለመኖሩን ከተረዳም ሰንብቷል፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ጽፈዋል።

ልዑል ጥላሁን፤ የተባሉ በበኩላቸዉ የሚሻለን ሰላም ነው ከሰላም የሚገኘው ትርፍ በምንም አይተካም ሲሉ ደምድመዋል

አዜብ ታደሰ 

ሸዋዬ ለገሠ