1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተቃዉሞ በኦሮሚያ ዳግም ማገርሸቱ

ሰኞ፣ ኅዳር 24 2011

በኦሮሚያ ክልል ቢያንስ ከ20 ያላነሱ ከተሞች ዉስጥ ዛሬ ተቃዉሞ ሲደረግ ውሏል። ተቃውሞው በኦሮሚያ ክልልና በቤንሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኝ ድንበሮች የተከሰተዉን ግድያና መፈናቀል በመቃወም እንደሆነም ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች ለDW ገልፀዋል።

https://p.dw.com/p/39NWi
Ethiopia State of Emergency Merkel (picture alliance / AP Photo)
ምስል picture-alliance/AP Photo

ተቃዉሞዉ ከተደረገባቸው ቦታዎች አንዷ ቤጊ ወረዳ በምዕራብ ኦሮሚያ ዉስጥ ሆና ግን በደቡብ ቤንሻንጉል ጉሙዝ የምታዋስን ናት። ባለፈዉ ቅዳሜ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ዞን በካማሽ ዉስጥ በሰዎች ላይ የደረሰዉን ግድያና መፈናቀል ለመቃወም ሰልፍ መዉጣታቸዉን ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የፈለጉ የቤጊ ነዋሪ ለDW ተናግረዋል።

የቤጊ ነዋሪ፥ «ማህበረሰቡ የወጣዉ ባለፈዉ ቅዳሜ ነዉ። ዛሬ ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ነበሩ። ተማሪዎቹም በሰላም ወጥተው፣ ድምፃቸዉን አሰምተው፣ ወደ ቤታቸዉ ተመልሰዋል። ከተማዉ ዉስጥ ግን አሁንም ዉጥረት አለ። መንግሥት ቶሎ ብሎ ይህን የሕዝብ እልቂት ጣልቃ ገብቶ ካላስቆመ ማኅበረሰቡ የንግድ፣ የግብይትና የሥራ  ማቆም አድማ ለመምታት እየተዘጋጀ ነዉ።»

የንግድ ወይም የሥራ ማቆም አድማዉም ከነገ ጀምሮ ለሦስት ቀን የሚዘልቅ መሆኑንም የቤጊ ነዋሪዉ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤት በክልሎቹ አዋሳኝ ድንበሮች ላይ የፌዴራል የፀጥታ አስከባሪ ኃይላት እንዲሰማሩ መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ አስገንዝቧል። የቤጊ ነዋሪዉም ፀጥታ አስከባሪዎች በአሮሚያ በኩል የመሠማራታቸዉ መረጃ እንደሌላቸዉ ተናግረዉ ግን በአሶሳ ከተማ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ የፀጥታ ኃይላት መግባታቸዉን እንደሰሙ ተናግረዋል።

ይህን ለማረጋገጥ የቤንሻንጉል ጉምዝ ዋና ከተማ ወደሆነችዉ  አሶሳ በመደወል ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያለፈለጉ ግለሰብ ተከታዩን ነግረውናል።

አሶሳ ነዋሪ፥ «ትናንት ወደ ኖክ ሰፈር ተብሎ የሚታወቅ አካባቢ ሠራዊቱ ሲገቡ እኔም አይቻለሁ። ከየት እንደመጡ አላወቅንም፣ ግን ብዙ ቁጥር ያለዉ የመከላክያ ሠራዊት ነዉ። እኔ ያየሁት ሦስት ኦራል ሙሉ ነዉ። የነሱ ተልዕኮ አሁን በካማሽ ዞን ዉስጥ ያለዉን ግጭት ለማረጋጋት መሆንኑም ሰምተናል።»

የፖለቲካና የሰብኣዊ መብት አቀንቃኝ የሆነዉ ላሚ ቤኛ አሁን ለተከሰተዉ ግጭት መፍትሄዉ ፖለቲካዊ እንጂ ሠራዊትን ማሰማራት አይደልም ይላል።

ግጭቱን በመቀስቀስ ወይም በማስፋፋት የተጠረጠሩ እስካሁን 208 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸዉን በኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ኦዲፒ የገጠር አደረጃጀት ኃላፊ እና የኦዲፒ የሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ አዲሱ አረጋ በፌስቡክ ገፃቸዉ ላይ አስፍረዋል።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሰ