1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቤንዚን እጥረትና የአርሶ አደሮች እንግልት 

ሐሙስ፣ የካቲት 11 2013

በባህርዳርና አካባቢው የተፈጠረው የነዳጅ እጥረት ነዳጅ በመጠቀም በመስኖ ለሚያለሙ አርሶአደሮች ፈተና እንደሆነባቸው አመለከቱ።የአማራ ክልል መንግስት በመስኖ የሚያለሙ አርሶ አደሮች ቅድሚያ ነዳጅ የሚያገኙበት ስልት መዘርጋቱን ገልፆአል፡፡ 

https://p.dw.com/p/3pXcf
Äthiopien I Benzinknappheit in Bahir Dar
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የነዳጅ እጥረት በመስኖ ለሚያለሙ አርሶአደሮች ፈተና ሆንዋል

በባህርዳርና አካባቢው የተፈጠረው የነዳጅ እጥረት ነዳጅ በመጠቀም በመስኖ ለሚያለሙ አርሶአደሮች ፈተና እንደሆነባቸው አመለከቱ።የአማራ ክልል መንግስት በመስኖ የሚያለሙ አርሶ አደሮች ቅድሚያ ነዳጅ የሚያገኙበት ስልት መዘርጋቱን ገልፆአል፡፡ 
አርሶ አደሮቹ የመስኖ ልማቶችን ለማከናወን ከወንዝ ውኃ በሞተር መሳብ ግድ ካቸዋል፣ ይህን ለማድረግ ደግሞ ቤንዚን በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሰሞኑን ቤነዚን ለመቅዳት በባሕር ዳር ከተማ ማደያዎች ከማደያ ማደያ ሲንከራረቱ ቢሰነብቱም ያለአግባብ ገንዘብ ይጠየቃሉ፣ ቤንዚን የለም ይባላሉ፣ ንብረታቸው ይዘረፋል፣ ላልተገባ ወጪም እየተጋለጡ ነው፡፡ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ ከሰጡን አርሶ አደሮች መካከል ሰፊዓለም አትንኩት ካለፈው እሁድ ጀምሮ ቤንዚን ለመቅዳት ባሕር ዳር ቢመጡም ከመንገላታት ውጭ ምንም ማግኘት አልቻሉም፡፡ 
አዝመረው በወቅቱ ውኃ ባለማግኘቱ ምርታማነቱ በእጅጉ እንደሚቀንስ ለቤት ፍጆታም በቂ እንደማይሆን አርሶ አደሩ ስጋታቸውን አመልከተዋል፡፡ 
ከተማው አደመ ወቅታዊ የግብርና ስራቸውን ትተው ባህር ዳር በሚገኙ የነዳጅ ማደያ ጣቢያዎች ቤንዚን ለማግኜት ሳምንት አሳልፈዋል፣ በየቀኑ ወጪ ከማውጣት በስተቀር እስካሁን ቤንዚን ማግኘት አልቻሉም፡፡ 
ከወጪና እንግልቱ ባለፈ መደብደብ፣ መዘረፍና በርካታ እንግልት እየደረሰባቸው እንደሆነም አብራርተዋል፤ 20 ሊተር ቤንዚን ለመቅዳት በተለያየ መንገድ ከ800 እስከ 1000 ብር ወጪ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ 
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አምሳሉ ጎባው ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ “የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ በመስኖ ልማት ለተሰማሩ አርሶ አደሮች ቅድሚያ እንዲሰጥ ደብዳቤ ተፅፎለታል” ብለዋል 
በአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የንግድ ውድድር፣ የሸማቾች ጉዳይና የመሰረታዊ እቃዎች ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ደመላሽ ታደለ እንዳሉት አርሶ አደሮች በሚያቅርቡት ማስረጃ መሰረት ቅድሚያ ተሰጥቶ ነዳጅ እንዲቀዱ መመሪያ ተላልፏል፡፡ 
ሆኖም ግን የተጭበረበረ መረጃ በመያዝ “ለኔም ይገባኛል” የሚሉ አታላዮች ሊኖሩ እንደሚችሉ አቶ ደመላሽ ጥርጣሪያቸውን አስቀምጠዋል፤ ይህን ተጠቅመው በህገወጥ መንገድ የሚቀዱ ሰዎችና እንዲሁም ከአርሶ አደሩ ያልተገባ ክፍያ የሚጠይቁ የነዳጅ ማደያ ሰራተኞች ካሉም እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡ 
የአማራ ክልል በሁለት ዙር 347 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት አቅዶ 228 ሺህ ተግባራዊ ማድረጉን ከክልሉ ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
 
ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ
 

Äthiopien I Benzinknappheit in Bahir Dar
ምስል Alemnew Mekonnen/DW