በፊታል ከተማ የፀጥታ ኃይሎች በዳኞች ላይ የፈጸሙት ድብደባ
ረቡዕ፣ ጥር 14 2017እለቱ ቅዳሜ ጥር 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ነው። የክስተቱ ቦታ ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ያያ ጉለሌ ወረዳ ፊታል ከተማ፡፡ ጄኔኑስ ነጋሳ የወረዳው የህግ ኦፊሰር በእለቱ የገጠማቸውን ለዶይቼ ቬለ ሲያስረዱ፤ “በእለቱ የወረዳው ጸረ-ሽምቅ ተዋጊዎች በቁጥጥር ስር አዋሉኝ፡፡ ቀጥታ በዚያው በፊታል ከተማ ወደሚገኘውም አራተኛ ካምፕ ወደ ሚባለው ካምፓቸው ወሰዱኝና በቆርቆሮ በተሰራች ትንሽ እስር ቤት ውስጥ አስገቡኝ፡፡ ትንሽ ቆይተው ከዚያ በማውጣት ስድስት ሆነው ከልክ በላይ ድብደባ ፈጸሙብኝ፡፡ እርግጫ አልቀረ በቀበቶ በብረት ፊቴ ላይ ሳይቀር ክፉኛ ድብደባ ፈጸሙብኝና ወደ እስር ቤቱ መለሱኝ” አሉ፡፡
በዳኛው ላይ የደረሰው አካላዊ ጥቃት
ተጎጂ ዳኛው አስተያየታቸውን ቀጠሉ፤ “በዚያው ቀን 11 ሰዓት አከባቢ ደግሞ የወረዳው ፡ ከ30 ደቂቃ ግድም በኋላ ደግሞ አዛዦች ይሁኑ ኃላፊዎች የማላውቃቸው የበላይዎቻቸው የሚመስሉ መጥተው ወደ ውጪ ጠሩኝና ምን አጥፍተህ ነው ብለው ጠየቁኝ፡፡ በወቅቱ ያዩኝ የባንኩ ማናጀር እና ጥበቃው አጠገቤ ነበሩና ያለምንም ጥፋት የደረሰብኝን ድብደባ ሳስረዳቸው ልብሴም በድብደባው እጅጉን ቆሽሾ ነበርና ያንን አራግፈውልኝ እንድንወጣ አዘዙን” ብለዋል፡፡
በዳኞች ላይ እየደረሰ ያለ እንግልትና ወከባ
ተጎጂው ዳኛ ወደ ቤታቸው ከገቡም በኋላ እሳቸውን ሲከታሉ የነበሩት ቀነኒሳ ጥበቡ የተባሉ የስራ ባልደረባቸው ላይ ማስፈራሪያ መድረሱንና ወደ ካምፑ ለተመሳሳይ አካላዊ ጥቃት ከገቡ በኋላ በወረዳው አመራሮች ተደውሎ እንዲለቀቁ መደረጉንም ነግረውናል፡፡ ዳኛው አክለውም እንዳሉን ከፍተኛውን የድብደባ ጉዳት ካስተናገዱ በኋላ በወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ዘነበ ነጋሽ እና በጓደኛቸው አማካኝነት ወደ ወረዳው ጤና ጣቢያ ቢወስዱም የተሻለ ህክምና እንደሚያስፈልጋቸው ተነግሯቸው ትናንትና እና ዛሬ ወደ ቤተሰባቸው በማምራት ምዕራብ ሸዋ ዞን ስር በምትገኘው በሆለታ ከተማ ህክምና ላይ መዋላቸውን አክለው ገልጸውልናል፡
የድብደባው መነሻ ምክንያት
የድርጊቱን መፈጸም ለዶቼ ቬለ ያረጋገጡት የወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ዘነበ ነጋሽ “ሕገወጥ” ላሉት ለዳኛው ድብደባ መነሻ የሆነውን በማስረዳት ነው አስተያየታቸውን የሰጡን፡፡ “ወደ ተከራየበት ህንጻ እያመራ ሳለ የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ የሚባሉ የህንጻው ጥበቃን ጨምሮ 3 ሰዎችን ይዘው ስወርዱ እሱ ጥበቃውን ቁልፍ ስጠይቅ ተገጣጥመው ነው ወደ ካምፕ ይዘውት ሄደው ድብደባ የፈጸሙበት” ብለዋል።
“የዳኞች እስራት አሳስቦኛል” የአማራ ዳኞች ማህበር
የተደበደቡት ዳኛ መላው አካላቸው ላይ ጉዳት መድረሱን መመልከታቸውን የገለጹት የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛው፤ ድርጊቱን የፍትህን ስርዓት በጣሙን የሚጎዳ ሲሉ ገልጸውታል፡፡ “በ2011 በወጣው የዳኝነት አዋጁ አንድ ዳኛ እጅ ከፍንጅ ወንጀል ስሰራ ካልተገኘ በማንም አይያዝም አይታሰርም ብልም በተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ይህ ተጥሷል” በማለት ድርጊቱም ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።
የዳኞች ጥቃት የፍትህ ሂደቱን ማስተጓጎሉ
ቀድሞም ውስን ዳኞች ብቻ በነበሩበት በወረዳው ፍርድ ቤት ፍትህ አሰጣጡ ተቋርጧል ያሉት የወረዳው ፍርድ ቤት ሃላፊው ድርጊቱን የፈጸሙ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ለዞኑ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማመልከታቸውን አስረድተዋል፡፡ “እነዚህ አካላት ካልተጠየቁ የህዝብ እምነት በኛ ላይ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገባል” ያሉት የሕግ ባለሙያውና የፍርድ ቤት ኃላፊው ድርጊቱ የተደጋገመ እንደመሆኑ አሁን ላይ በወረዳው የፍርድ ቤት ስራውን ለማቆም መገደዳቸውንም አስረግጠው ገልጸዋል፡፡
ዶይቼ ቬለ ስለጉዳዩ አሳሳብነትና ሊወሰድ ስለሚገባው እርምጃ ለመጠየቅ ለሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ከፋለ አደሬ ጥያቀውን ስያቀርብ “ጉዳዩን እያጣራን ነው” ከማለት ውጪ ለጊዜው የሰጡን ማብራሪያ የለም፡፡
ሥዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ