1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

«ከ30 ዓመቴ በፊት ቢሌነር ሆኘ ፎርብስ ላይ መቅረብ እፈልጋለሁ» ኢዘዲን ካሚል

ረቡዕ፣ ጥር 1 2016

በሃያዎቹ መጀመሪያ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ወጣት ኢዘዲን ካሚል፤እስካሁን ከ30 በላይ የፈጠራ ስራዎችን ሰርቷል። እነዚህን ስራዎቹን ወደ ምርት እና አገልግሎት ለመቀየር ተቸግሮ የቆየ ቢሆንም፤ በቅርቡ ግን ሄክስ ላብ /Hex Labs./የተሰኘ የራሱን ኩባንያ በማቋቋም በፈጠራ ስራዎቹ ሚሌነር መሆን ችሏል።

https://p.dw.com/p/4b2mM
ወጣት ኢዘዲን፤ ሄክስ ላብ የተሰኘ  የራሱን ኩባንያ በማቋቋም  የተለያዩ የፈጠራ ስራዎቹን ወደ ምርት እና አገልግሎት ለመቀየር በመስራት ላይ ይገኛል
ወጣት ኢዘዲን፤ ሄክስ ላብ የተሰኘ የራሱን ኩባንያ በማቋቋም የተለያዩ የፈጠራ ስራዎቹን ወደ ምርት እና አገልግሎት ለመቀየር በመስራት ላይ ይገኛል ምስል privat

በፈጠራ ስራዎቹ ወደ ቢሌነርነት እያመራ ያለው ወጣት


በኢትዮጵያ በየጊዜው የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ በርካታ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች  ሲሰሩ ይታያል። ነገር ግን በገንዘብ ድጋፍ ማጣት የፈጠራ ባለሙያዎች ፈጠራዎቻቸውን  ለምርት እና አገልግሎት ማብቃት አለመቻላቸው ተደጋግሞ የሚነሳ ችግር ነው።

የሶፍትዌር ልማት ባለሙያው  እና ወጣቱ የፈጠራ ሰው  ኢዘዲን ካሚል ይህ ችግር ከገጠሙት ወጣቶች አንዱ ነው።በ14 ዓመቱ የስርቆት መከላከያ /Anti Teft/ በመስራት የፈጠራ ጉዞን የጀመረው ኢዘዲን አሁን ፤ በሀገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝተው የተመዘገቡ 38  የፈጠራ ስራዎች አሉት።ነገር ግን ከነዚህ የፈጠራ ስራዎቹ መካከል በገንዘብ እጥረት ሳቢያ በጣት የሚቆጠሩት  ብቻ  ነበሩ ተመርተው ገበያ ላይ የዋሉት።

«አዎ ከ38ቱ ውስጥ እስካሁን ድረስ ሶስቶቹ ናቸው።ወደ ምርት እና አገልግሎት የተቀየሩት ። በተለይ ከኮቪድ ጋር የተያያዙት ናቸው ወደ ምርት እና አገልግሎት ተቀይረው እየሰሩ ያሉት።»

ካለ በኋላ  ኮቪድን ለመከላከል ፊታችንን እንዳንነካ የሚያስታውስ መሳሪያ፤ከንክኪ ነፃ የሆነ የእጅ መታጠቢያ እና ከዕጅ ንክኪ ነፃ የሆነ የሳሙናና እና የሳኒታይዘር ማቅረቢያ መሆናቸውን አብራርቷል።

ወጣቱ፤ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን ሰርቷል
ኢዘዲን ካሚል፤ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን ሰርቷልምስል Ezedin Kamil

በቅርቡ ግን ሄክስ ላብስ /Hex Labs./የተሰኘ  የራሱን ኩባንያ በማቋቋም  የተለያዩ የፈጠራ ስራዎቹን ወደ ምርት እና አገልግሎት ለመቀየር በመስራት ላይ ይገኛል።   በሶፍትዌር ልማት ላይ ያተኮረው ይህ  ኩባንያ የተለያዩ መተግበሪያዎችን እና ድረ-ገፆችን በማልማት በሀገር ውስጥ እና በውጭ ለሚገኙ የተለያዩ  ድርጅቶች  በመሸጥ ላይ ነው።

«ስምንት ወር የሆነው ድርጅት አለኝ ሄክስ ላብስ የተሰኘ።ስለ ሄክስ ላብስ ስናወራ ራሴ ኢንቨስት በማድረግ የመሰረትኩት ድርጅት ነው።»ካለ በኋላ ፤ ቱርክ ላይ የሶፍትዌር ምህንድስና ትምህርቱን ሲከታተል ተጨማሪ ኮርሶች መውሰድዱን እና በእነዚያ ተጨማሪ ኮርሶች  ድረ-ገፅ መገንባት እንደጀመረ ተናግሯል።ከዚያም ለአንድ የግል ባንክ የሰራውን ስራ ፌስ ቡክ ላይ በማጋራቱ ይህንን የተመለከቱ «ወደ 24 የሚሆኑ ሰዎች እንድሰራላቸው ኦርደር አደረጉ» ብሏል።   አያይዞም «እነዚህን 24 ዌብሳይቶች በአራት ወር ውስጥ ሰርቼ አስረከብኩኝ።ወደ 1.2 ሚሊዮን ብር ማግኘት ቻልኩኝ።»በማለት ተናግሯል።ከዚያም መተግበሪያዎችን በብዛት ለመስራት በአዲስ አበባ ከተማ ሄክሰ ላብስ የተሰኘውን ኩባንያ በመመስረት 12 ሰራተኞችን በመቅጠር ኢትዮጵያ፣ ዱባይ፣ ደቡብ አፍሪቃ፣ብሪታንያ እና ቱርክ ለሚገኙ ድርጅቶች የድረ ገፅ እና የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያዎችን ሰርቷል።  በዚህ ኩባንያም እስካሁን 16 መተግበሪያዎችን እና ከ70 በላይ ድረ-ገጾችን ማልማታቸውን አመልክቷል። 

ወጣቱ  በፈጠራ ስራዎቹ በበርካታ ውድድሮች በማሸነፍ የተለያዩ የሰርተፊኬት እና የገንዘብ ሽልማቶችን አግኝቷል።ከነዚህም መካከል በኤለክትሪክ እና በሶላር በሚሰራው ባለ ሶስት እግር  ተሽከርካሪ  አሸናፊ በመሆን በጎርጎሪያኑ 2021 ዓ/ም ከብሪቲሽ ካውንስል COP26 ዓለም አቀፍ ውድድር  ያገኘው የ5 ሺህ  ፓውንድ ሽልማት ይጠቀሳል።ይህንን እና ከሌሎች ውድድሮች ያገኛቸውን የገንዘብ ሽልማቶች አንድ ላይ በማድረግ ታዲያ፤ የፈጠራ ስራዎቹን ወደ ምርት እና አገልግሎት ለመቀየር ቀደም ሲል አይከን አፍሪካ ከስምንት ወር በፊት ደግሞ ሄክስ ላብስ /Hex Labs/ የተሰኘ ድርጅቱን ለማቋቋም በቅቷል። 

ኢዘዲን ካሚል የፈጠራ ስራውን የጀመረው በ14 ዓመቱ የስርቆት መከላከያ መሳሪያ  በመስራት ነው
ኢዘዲን ካሚል የፈጠራ ስራውን የጀመረው በ14 ዓመቱ የስርቆት መከላከያ መሳሪያ በመስራት ነው ምስል Ezedin Kamil

ከዚህ ቀደም የፈጠራ ስራዎቹን ወደ ገበያ ለማቅረብ ባለሀብቶች አብረውት እንዲሰሩ ለረዥም ጊዜ  ሙከራ አድርጎ ሳይሳካለት መቅረቱን የሚገልፀው ኢዘዲን፤ በአሁኑ ወቅት ግን «ሄክስ ላብስ» በተሰኘው ኩባንያው ውጤታማነቱን የተመለከቱ ሁሉ አብረውት ለመስራት ፈቃደኛ መሆናቸውን ይናገራል።
ይህንን ዕድል በመጠቀምም  ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር በመሆን አይቬክስ  የተባለ ሌላ  የአክሲዮን ድርጅት መመስረቱን ያስረዳል።  እንደ ኢዘዲን ገለፃ «ሄክስ ላብስ» የተሰኘው ድርጅቱ ሶፍትዌሮችን አልምቶ በመሸጥ ላይ ያተኮረ  ሲሆን፤በቅርቡ ስራ የሚጀምረው አይቤክስ የተሰኘው ድርጅቱ  ግን ሰዎች በምዝገባ የተለያዩ ዲጅታል  አገልግሎቶችን የሚያገኙበት ነው። 

ኢዘዲን ቀደም ሲል መለኪያ ቀጥሎ አይከን አፍሪካ፣ ከዚያም  ሄክስ ላብ በአሁኑ ወቅት ደግሞ አቤክስን ለመመስረት ተዘጋጅቷል።ይህንን የሚደርገውም ለተሻለ የገበያ ስልት መሆኑን ገልጿል። በዚህ ሁኔታ የገንዘብ አቅሙን በማሳደግ በአሁኑ ወቅትም «ሄክስ ዲስተርብ» የተሰኘ ሌላኛውን የፈጠራ ስራውን ወደ ገበያ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ነው። «ሶስተኛው ምርቴ ሄክስ ዲስተርብ የተባለው ምርቴ ወደ ገበያ ለመቀየር «ኢንቨስትመንት ሴኩር» አድርገን ምርቱን ሰርተን ለማርኬት ዝግጁ እየሆንን እንገኛለን። ይህ የፈጠራ ስራዬ ወደ ላይብረሪ ፣ ቤተ እምነት ወደ ሚዲያ እና ሌሎችም  ፀጥታ የሚያስፈልግባቸው ቦታዎች ስንገባ ስልካችንን «ሳይለንት» ስንወጣ «ላውድ» የሚያደርግ ነው።መጀመሪያ ስሰራው በሀርድ ዌር ነበር አሁን ወደ ገበያ እያቀረብነው ያለነው በሶፍትዌር ነው።ወደ «አፕሊኬሽን» ለውጠነው ነው።»

የ22 ዓመቱ ወጣት ኢዘዲን ካሚል፤ ከፈጠራ ስራው ባሻገር በቱርክ ሀገር በሶፍትዌር ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪውን በመከታተል ላይ ይገኛል። ወጣቱ አብዛኛዎቹን የፈጠራ ስራዎቹን የሰራቸው የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ ተወልዶ ባደገባት ውልቂጤ ከተማ ሲሆን፤ አሁን ያገኘው ስኬት ላይ ለመድረስም በርካታ ውጣ ውረዶችን አይቷል።እናም ካጋጠመው በመነሳት ወጣቶች ተስፋ ሳይቆርጡ ደጋግመው እንዲሞክሩ ይመክራል።

የሶፍት ዌር  ምህንድስና ያጠናው ወጣት ኢዘዲን ካሚል፤ በፈጠራ ስራዎቹ ሀብት ማመንጨት ጀምሯል
የሶፍት ዌር ምህንድስና ያጠናው ወጣት ኢዘዲን ካሚል፤ በፈጠራ ስራዎቹ ሀብት ማመንጨት ጀምሯል ምስል Ezedin Kamil

 

«እኔ ለብዙ ወጣቶች በጎ ተምሳሌት ነኝ ብዬ አስባለሁ።ለብዙ ያልኩበት ምክንያት ደግሞ ያው ሀገራችን አብዛኛዎቻችን የድሃ ልጆች ነን።ይህም ለብዙ ወጣቶች የሚለውን እንዳነሳ አድርጎኛል።አብዛኛው የሚገኘው ደግሞ ከከተማ ይልቅ በገጠር ወይም በገጠር ከተማ የሚገኝ ነው።እኔ ደግሞ ገጠር ላይ ነው ያደኩት እና 12ኛ ክፍል እስክጨርስ ድረስ በጣም «ቻሌንጅግ» የሆነ ቦታ ላይ ነው ያደኩት።ቤተሰቦቼ የኢኮኖሚ አቅማቸው ይህን ያህል አይደለም።ደብተር ተገዝቶልኝ ቦርሳ ስፈልግ መግዛት የማይችሉበት ቤተሰቦች ነበሩኝ።ስለዚህ ወጣቶች ከኔ ምን መማር ይችላሉ የፈለገ ቻሌንጅግ ቦታ ቢሆኑ የፈለገ ማቴሪያል የማያገኙበት ቦታ ቢሆኑ፤ጎል ካላቸው ያንን ነገር ለማሳካት አንድ መንገድ ብቻ አይደለም ያለው።በጣም በርካታ መንገዶች አሉ።አንዱ መንገድ ካልተሳካ ሁለተኛውን ሁለተኛው ካልተሳካ ሶስተኛውን የተለያዩ መንገዶች እየተጠቀሙ ሀሳባቸውን ወደመሬት ለማውረድ ጥረት እንዲያረጉ።» በማለት ለእኩያዎቹ ምክር ለግሷል።

«ፈጠራ ማለት ዕሴት መፍጠር ነው» የሚለው ኢዘዲን፤ለዚህም የሰዎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ  የሚያቀሉ  እና ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የፈጠራ ስራዎችን በመስራት በተለያዩ ጊዜዎች  በመሰረታቸው ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎቹ አማካኝነት ሀብት የማመንጨት ስራ ላይ  በደንብ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።በዓለማችን በቴክኖሎጅ ላይ መዋዕለ ንዋይ ከሚያፈሱ ቱጃሮች መካከል በብዙ ምክንያቶች ኤሎን ማስክን ያደንቃል።ለወደፊቱም በፈጠራ ስራዎቹ እንደ ማስክ ቢሌነር የመሆን ተስፋ ሰንቋል። «የአፍሪቃን ትርክት በፈጠራ ስራ እንቀይራለን» ወጣት ኢዘዲን ካሚል 
«የስራ አጦችን ቁጥር ለመቀነስ ሰዎችን ማሳተፍ እንዲሁም ሀብት ማመንጨት ሲችል ነው።ፈጠራ የምለው። ብዙ ጊዜ ከ30 ዓመት በፊት ቢሌነር ሆኘ «አንደር 30» አርቲክል ማፃፍ እፈልጋለሁ።ብዬ አወራለሁ። ይህንን የምልበት ምክንያት «ቫሊዩ ክሬት» ሲደረግ የምለካበት ገንዘብ ነው። ስለዚህ ከ30 ዓመቴ በፊት ጥሩ የሆነ «ቫሊዩ»/እሴት/ ለ«ማርኬቱ ፕሮቫይድ»ማድረግ እፈልጋለሁ።ስለዚህ ለብዙ ስራ አጦች የስራ ዕድል በመፍጠር  በጎ ተምሳሌት መሆን እፈልጋለሁ»በማለት ተናግሯል።ይህንን ህልሙን ለማሳካትም በኢ-ኮሜርስ ላይ አተኮሮ እንደሚሰራ ገልጿል።

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ፀሀይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ