1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጦርነቱ የሞቱ የትግራይ ኃይሎች መርዶ ይነገራል መባሉ

ረቡዕ፣ መስከረም 9 2016

በጦርነቱ ወቅት የሞቱ የቀድሞ የትግራይ ኃይል ለቤተሰቦቻቸው መርዶ የመንገር ስርዓት በቅርቡ በይፋ እንደሚካሄድ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር አስታወቀ። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ፥ ቁጥሩ በትክክል ባያስቀምጡትም «በሺዎች የሚቆጠሩ» ያልዋቸው የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች አባላት በሁለት ዓመቱ ጦርነት መሞታቸው ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4WZ3q
በጦርነቱ ወቅት የሞቱ የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች ሥም ዝርዝር ይፋ ሊሆን ነዉ
በጦርነቱ ወቅት አካላቸዉን ያጡ የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች ምስል Million Hailesilassie/DW

በአስር ሽዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ የትግራይ ኃይሎች አካል ጉዳተኛ ሆነዋል

በጦርነቱ ወቅት የሞቱ የቀድሞ የትግራይ ኃይል ለቤተሰቦቻቸው መርዶ የመንገር ስርዓት በቅርቡ በይፋ እንደሚካሄድ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር አስታወቀ። የትግራይ የጦር ጉዳተኞች ማእከል ስራ ባስጀመሩበት ወቅት ንግግር ያደረጉ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ፥ ቁጥሩ በትክክል ባያስቀምጡትም "በሺዎች የሚቆጠሩ" ያልዋቸው የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች አባላት በሁለት ዓመቱ ጦርነት መሞታቸው ተናግረዋል። የሟች ቤተሰቦች ከማርዳት በተጨማሪ፣ የመደገፍ ስራም እንደሚከወን ጠቁመዋል።ጦርነቱ በትግራይ ላደረሰዉ ኪሳራ ልዩ የድጋፍ ማዕቀፍ ያስፈልጋል መባሉ

እስካሁን ድረስ ቁጥሮች በይፋ ባይገልፁም ለሁለት ዓመታት በትግራይ ሐይሎች እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል በተደረገው ጦርነት 'በሺዎች የሚቆጠሩ' የተባሉ የትግራይ ተዋጊዎች መሞታቸው፣ ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው እንዲሁም ለዘላቂ ድጋፍ መጋለጣቸውን በክልሉ ባለስልጣናት በኩል ይነገራል። ደም አፋሳሹ ጦርነት በፕሪቶርያው ውል መሰረት ከቆመ አንድ ዓመት ሊሞላው የተወሰኑ ሳምንታት ቢቀሩትም፥ በትግራይ ያሉ የቀድሞ ተዋጊ ቤተሰቦች 'የቀድሞ የትግራይ ሰራዊት አባላት ልጆቻቸው፣ ወንድም እህቶቻቸው፣ ባሎቻቸው ወይም ሌላ የቅርብ ዘመዳቸው' ያሉበት ሁኔታ እስካሁን ባለማወቃቸው ችግር ላይ መሆናቸው ይገልፃሉ። ስላለው ሁኔታ ሀሳባቸው ያካፈሉን የቀድሞ ታጋዩ ታናሽ ወንድማቸው ይኑር አይኑር የማያውቁት አቶ መሓሪ ካሕሳይ፥ በዚህ ሁኔታ እሳቸው እና መላ ቤተሰባቸው የከፋ የመከራ ግዜ እያሳለፉ መሆኑ ነግረውናል። ከፌደራሉ መንግስት ጋር ጦርነት ላይ የነበሩ የትግራይ ሐይል አዛዦች የተሰው ታጋዮች መርዶ በክብር ለቤተሰብ ማሳወቅ እንዳለባቸው የሚያነሱት አቶ መሓሪ፥ ቁርጡን ያላወቀ ወላጅ እና ሌላ የቤተሰብ ክፍል አስከፊ ግዜ እያሳለፈ መሆኑ ይጠቁማሉ። መሓሪ "በተለይ በእኛ አካባቢ በይፋ የደረሰን መርዶ የለም። ሰው በራሱ መንገድ የልጆቹ፣ የወንድም እህቱ፣ የቤተሰቡ ሁኔታ ለማጣራት ይሞክራል፥ ይንከራተታል" የሚል ሲሆን "ለምሳሌ የእኛ ቤተሰብ፥ የታናሽ ወንድሜ ሁኔታ ሁለት ዓመት አናውቅም። በዚህ ሁኔታ በርካታ ቤተሰብ ነው እየተጎዳ ያለው። ተረጋግቶ መኖር፣ ቁርጡን ማወቅ አልቻለም። ሁሌም በይፋ መርዶ እንዲነገር ነው የምንጠይቀው። እስካሁን ግን አልሆነም። ሰው በውስጡ ያልጠራ ነገር ስላለው፥ ተረብሾ ነው እየኖረ ያለው" ሲል አክሏል።በትግራይ ክልል በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ

በጦርነቱ ወቅት በርካታ አካላቸዉን ያጡ የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች አሉ ተብሏል
በጦርነቱ ወቅት አካላቸዉን ያጡ የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች ምስል Million Hailesilassie/DW

ይህ በእንዲህ እንዳለ በተወሰኑ አካባቢዎች በጦርነቱ ያለፉ የቀድሞ ተዋጊዎች መርዶ የመንገር ስነስርዓት እየተከወነ መሆኑ ሰምተናል። በመቐለ ከተማ ጨምሮ በዙርያዋ ባሉ የገጠር አካባቢዎች፣ በውቅሮ እና አቅራቢ አካባቢዎች እንዲሁም ሌሎች ሰሞኑን ቤተሰቦች መርዶ ሲነገራቸው ሰንብቷል። ዛሬ በመቐለ ለጦር ጉዳተኞች የተገነባ ማእከል ስራ ያስጀመሩት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ባደረጉት ንግግርም፥ ግዜው እና ቁጥሩ በውል ባያስቀምጡትም በቅርቡ በሺዎች ለሚቆጠሩ መርዶ እንደሚነገር አንስተዋል። አቶ ጌታቸው ረዳ "ሕይወታቸው የከፈሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰማእታቶቻችን በቅርቡ፥ ክብራቸው በጠበቀ መልኩ በይፋ መርዶ ነግረን፥ ለቤተሰቦቻቸው በተወሰነ መልኩ እንኳን ቢሆን ከእናንተ ጋር ነን የሚል መልእክት እናስተላልፋለን። የሆነ ይሁን ያለን ሀብት ለጀግኖቻችን፣ ለጀግና ወላጆች የማይሆንበት ምክንያት የለም። . . . የጀግኖችን መርዶ የመንገር ጨምሮ የታጋዮች፣ የአካል ጉዳተኞች እንዲሁም ሌሎች ጥያቄዎች ለመመለስ የጀመርናቸው እንቅስቃሴዎች አጠናክረን እንቀጥላለን" ብለዋል።

በጦርነቱ ወቅት በርካታ አካላቸዉን ያጡ የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች አሉ ተብሏል
በጦርነቱ ወቅት አካላቸዉን ያጡ የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች ምስል Million Hailesilassie/DW

በትግራይ ጦርነት የደረሱ የወሲብ ጥቃቶች

በጦርነቱ ሕይወታቸው ካጡ በርካቶች ውጭ ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ የተባሉ ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች ተዋጊዎች በቂ ድጋፍ እያገኙ እንዳልሆነ በማንሳት በተደጋጋሚ ቅሬታ ያቀርባሉ፣ የተቃውሞ ሰልፍ በጎዳናዎች ያደርጋሉ። ዛሬ በመቐለ ለነዚህ የከፋ የጦር ጉዳት የደረሰባቸው የቀድሞ ተዋጊዎች የሚያገለግል ማቆያ እና እንክብካቤ ማእከል በ180 ሚልዮን ብር ተገንብቶ ስራ ጀምሯል። በማእከሉ ያገኘነው በ2013 ዓመተምህረት በነበረው ጦርነት ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶበት በተሽከርካሪ ወንበር የሚንቀሳቀሰው የ25 ዓመት ወጣት ሀፍቶም ኪዳይ ፥ ከትግራይ አስተዳደር እና ሌሎች ድጋፍ አድራጊ አካላት የሕክምና አገልግሎት ሊያገኝ ይጠብቃል። "ለሀገሬ፣ ለህዝቤ፣ ለራሴ ብዬ ነው ወደ ትግል የወጣሁት። የከፈልኩት መስዋዕትነት ምንም አይቆጨኝም ብቻ ሳይሆን የሚጠበቅም ነው" የሚለው የቀድሞ ታጋይ ሀፍቶም ኪዳይ "አሁን ግን እኛ አካል ጉዳተኛ ሆነናል። የሚያስፈልገን ነገር አለ። ዋናው ነገር ሕክምና ነው። የተሻለ ሕክምና ሊመቻችልን ይገባል። ሕክምና አግኝቼ ከቆምኩኝ ተመስገን ነው። ምንም መስዋዕትነት እንዳልከፈልኩ ነው የምቆጥረው" ባይ ነው።

ከጦርነቱ በኃላ በትግራይ የቀድሞ ተዋጊዎች አያያዝ ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ በብዙሐን ይገለፃል። ከ50 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች ከትግራይ ሐይሎች መሰናበታቸው በቅርቡ የተገለፀ ቢሆንም ለነዚህ ተሰናባቾች የተደረገ የማቋቋሚያ ድጋፍ አለመኖሩ ቅሬታ የፈጠረ ሆንዋል። በሌላ በኩል ሌሎች ከመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የተባሉ የቀድሞ ተዋጊዎችም ወደ መደበኛ ሕይወት እንዲመለሱ የማቋቋሚያ ድጋፍ እንደሚሻ የትግራይ አስተዳደር ሲገልፅ ቆይቷል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ 

አዜብ ታደሰ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ