1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጥርሶቹ ብሩሽ ነክሶ በመሳል ተክኗል

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 22 2013

የአካል ጉዳተኛ ቢሆንም ልጅ ሳለ ሥዕል በእግሮቹ መሣል ጀመረ። በአንድ ወቅት እህቱ መጻፊያ እርሳስ እና ወረቀት ጠረጴዛ ላይ ተወችለት። እናም በድንገት ብሩሽ በጥርሶቹ ነክሶ መሣል ጀመረ። ሠዓሊ ዮሴፍ በቀለ በተፈጥሮ ሲወለድ ጀምሮ ሁለቱ እጆቹ የማይታዘዙለት ናቸው። ሥዕልን ግን በራሱ መንገድ ይሥለዋል።

https://p.dw.com/p/3nPB0
Äthiopien Addis Abeba | Maler Yosef Bekele malt trotz Behinderung
ምስል Solomon Muchie/DW

አካል ጉዳተኛነቱ ሠዓሊ ከመሆን አላገደውም

የአካል ጉዳተኛ ቢሆንም ልጅ ሳለ ሥዕል በእግሮቹ መሣል ጀመረ። በአንድ ወቅት እህቱ መጻፊያ እርሳስ እና ወረቀት ጠረጴዛ ላይ ተወችለት። እናም በድንገት ብሩሽ በጥርሶቹ ነክሶ መሣል ጀመረ። ከዛሬ 16 ዓመት ዘመናዊ የሥዕል ትምህርት ቀስሞ ዛሬ ሥዕል ሞያው ኾኗል። የሦስት ልጆች አባት የኾነው ሠዓሊ ዮሴፍ በቀለ ሸራ ወጥሮ መሣሉን ቀጥሏል።  እስካሁን ከመንግሥትም ኾነ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ሠዓሊው የሚደግፈው አልተገኘም። 

የኅብረተሰቡን የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ እና ሕይወት አኗኗርና ሁለንተናውን በመዳሰስ ፣ ከዚያም ሲያልፍ ባህል ወግ ልማዱን በመግለፅ ሁለንተናውን ታሳያለች። ኪነጥበብ። 

ከኪነ ጥበብ ዘርፎች አንዱ የሆነው የሥዕል ጥበብ ጥንታዊና ከብዙ ታሪኮች ጋር የተቆራኘ ጭምር ነው። ይህንንም በመረዳት እነ ፓብሎ ፒካሶ እርግብን የለመለመ የወይራ ቅጠል አስነክሰው በመሳል የሰላም አርማነቷን ዓለምን በሚያግባባ መልኩ በጥበባቸው አትመዋል። መሰሎቻቸው እነ ሚካኤል አንጀሎም የጥንታዊ አብያተ መንግሥታት እና ቤተ መቅደሶችን በተዋቡ ሥዕሎቻቸው እንዲያሸበርቁ በማድረግ ታላላቅ ታሪኮችን ሠርተው አልፈዋል።

በኢትዮጵያም ከጥንታዊ የአብያተ ክርስትያናት እና ቤተ መቅደሶች እስከ ዓለማዊ የሥዕል ጥበቦች በሌሎች ዘርፎች ድረስ ዓለም ክብርና ሞገሥ የቸራቸው ሠዓልያን አንቱታን ያተረፉባቸው ሥዕሎችን ቀለም በጥብጠው፣ ሸራ ወጥረው ሀሳብን ፣ ተፈጥሮን በጥበባቸው ተራቅቀውበት አልፈዋል። በእርግጥም ሥዕል ከሰው ልጅ የዕድገት ደረጃ ጋር አብሮ የዘመነ ይሁን እንጂ ሰው በዋሻ ውስጥ ይኖር ከነበረበት ዘመን ጀምሮ የነበረ ታላቅ የጥበብ ዘርፍ መሆኑ ይነገርለታል።

Äthiopien Addis Abeba | Maler Yosef Bekele malt trotz Behinderung
ምስል Solomon Muchie/DW

ሠዓሊ ዮሴፍ በቀለ በተፈጥሮ ሲወለድ ጀምሮ ሁለቱ እጆቹ የማይታዘዙለትና ለምንም ነገር ጥቅም የማይሰጡት ናቸው። ምናልባትም ሰዓት ለማሰር ካልሆነ በስተቀር።
ይህ ሰው ውስጡ ሥዕል የመሳል ፍላጎት እንዳለው የውስጥ ግፊቱን ካወቀ በኋላ ውሎ ሳያድር በእግሩ፣ በኋላም በአፉ ለመሳል ቁርጥ ሀሳብ ያዘ። የሰው ልጆች ያለ አንዳች ረብ ምድር ላይ ሕልው እንዳልሆኑ ሃይማኖቶችም ይሁን የተፈጥሮ ጥበብ ዳሳሽና አሳሾች የሚሉት ሀቅ ነው። በውስጥ የተቸሩትን ራእይ ማወቅ ላይ ግን ዝንፈቶች ይፈጠራሉ።

ጥሪያቸውን ማልደው ያወቁት ግን የአካልም ይሁን የመንፈስ ስብራት ሳይገድባቸው እምቅ ችሎታቸውን አውጥተው ሲያሳዩት ይስተዋላሉ። ሰዓሊ ዮሴፍ በቀለም ድርብርብ የአካል ጉዳት ቢኖርበትም ያንን ውስጡ ያለውን ፍላጎት በትምህርት ለማጠናከር አልዛለም። የሥዕል ሥራዎቹን በእግሩ ፣ ከዚያም በአፉ እየሳለ ያዳበረው ችሎታው ትልልቅ ሄቴሎችና አንዳንድ ግለሰቦች ሥራውን ፈልገው እንዲገዙት አድርጎታል።

ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት የሆነው ይህ ሰው ሥዕልን በአካል ጉዳት ውስጥ ፣ ያውም የእጅ ጉዳት ደርሶበት ከመሳል ወደኋላ አላለም። ካዛንችስ በሚገኘው ጠባብ አንድ ክፍል መኖሪያ ቤቱ ውስጥ ያዘጋጀውን ንድፍ ይዞ ወደ አቢሲኒያ የኪነጥበባት ትምህርት ቤት በመሄድ ሸራ ላይ ይሥላል። ሥራዎቹም በግልፅ የሚታዩ እና ፖርትሬት ላይ ያተኮሩ ናቸው። ሥሏቸው ለገበያ ያልበቁ ውስን ሥዕሎቹም በዚያው ካዛንችስ በሚገኝ ጠባብ ማሳያ ክፍል ውስጥ ተቀምጠው ይገኛሉ።

ሠዓሊ ዮሴፍ ከመንግሥት ድጋፍ በተደጋጋሚ ቢጠይቅም ማግኘት አልቻለም። ይህ ሰው ድጋፍ ቢያገኝ፣ አይዞህ ፣ በርታ ቢባል ግን የጥበብ ሥራው የበለጠ አድጎ ለሌሎችም ሰዎች ምሳሌ እና አርዓያ መሆን የሚችል መሆኑን ታዝበናል።

ሰለሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ