1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በግጭት የተናጠችው የምራቅ ወለጋዋ ኪረሙ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 6 2015

ባለፉት ጊዜያት በተደጋጋሚ ግጭቶች በተናጠችው የምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ካለፉት ሁለት ሳማንታት የተሻለ የፀጥታ ሁኔታ እንዳለ የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናገሩ። ተፈናቃዮችን በተወሰነ መልኩ መልሶ የማስፈር ሥራም መጀመሩን ገልጠዋል። ሆኖም በተወሰኑ የገጠር ቀበሌያት ግጭት እና አለመረጋጋት እንዳለም ተገልጧል።

https://p.dw.com/p/4KzhM
Karte Äthiopien Gutin EN

«ከወረዳው አስተዳደር ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ቀበሌያት ይበዛሉ»

ባለፉት ጊዜያት በተደጋጋሚ ግጭቶች በተናጠችው የምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ካለፉት ሁለት ሳማንታት የተሻለ የፀጥታ ሁኔታ እንዳለ የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናገሩ። ተፈናቃዮችን በተወሰነ መልኩ መልሶ የማስፈር ሥራም መጀመሩን ገልጠዋል። ሆኖም በተወሰኑ የገጠር ቀበሌያት ግጭት እና አለመረጋጋት እንዳለም ተገልጧል። ቀደም ሲል በነበሩ ግጭቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ በዚሁ ኪረሙ ወረዳ ውስጥ በነበረው ግጭት እስረኞች የማስለቀቅ እና የወረዳ ጽ/ቤቶች እንዲሁም ንብረቶቻቸውን የማውደም ተግባር ተፈጽሟልም ተብሏል። ነዋሪዎች እና ባለሥልጣናት በወረዳው ከተወሰኑ አከባቢዎች ውጪ በሁሉም የኪረሙ ወረዳ ቀበሌያት አሁንም ድረስ መረጋጋት አለመረጋገጡን አመልክተዋል። 

ልክ የዛሬ ሁለት ሳምንት ተጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት በቆየው የምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ግጭት የወረዳዋ ከተማ ኪረሙን ጨምሮ ከ19 ቀበሌያት ነዋሪዎችን በብዛት አፈናቅሎ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል። በዚህች ወረዳ ላለፉት ሁለት ሳምንታት የፀጥታ ኃይላት አከባቢው ላይ ተበራክተው መድረስ፤ የፀጥታ ችግሩ የተሻለ መልክ ይዞ መቆየቱ ቢነገርም አሁንም ግን አልፎ አልፎ በተወሰኑ ቀበሌያት ግጭት ማፈናቀሉ እንዳላቧራ ነው የሚነገረው፡፡ ከኪረሙ ተፈናቅለው አሁን ላይ አጎራባች በሆነችው የአሙሩ ወረዳ ተጠልለው የሚገኙትና ስማቸውን ለደህንነታቸው ስባል መግለጽ ያልፈለጉ ነዋሪ እንደሚሉት በትናንትናውም እለት በኪረሙ ወረዳ ከተማ እና ሀሮ በተባለች የወረዳዋ ቀበሌ መሃል ባሉ አከባቢዎች በተቀሰቀሰው ግጭት ቤቶች ተቃጥለው ተጨማሪ ማፈናቀል ተከስቷል፡፡ “አሁን የተሻለ የመረጋጋት ሁኔታ የሚታየው በኪረሙ የወረዳዋ ከተማ ብቻ ነው፡፡ እሱም የተሻለ የፀጥታ ኃይል ስላለበት ነው፡፡ ከዚያ ወጣ ሲባል ኖሌ፣ ሀሮ እና ቦቴ በሚባሉ ቀበሌያት አሁን መረጋጋት የለም፡፡ በተለይም አሁን ትናንት በኖሌ የአርሶ አደሮች ቤት ሲቃጠሉ ነበር” ብለዋል አስተያየት ሰጪው፡፡

Äthiopien Vertriebene aus Wollega in Bahir Dar angekommen | Hauptstadt der Amhara-Region
የወለጋ ተፈናቃዮች በባሕር ዳር ከተማምስል Alemnew Mekonnen/DW

ስማቸው እንዳይገለጽ ጠይቀውን አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ የኪረሙ ወረዳ ባለስልጣን በበኩላቸው በኪረሙ አሁን አንጻራዊ መረጋጋት መኖሩን ያወሳሉ፡፡ በተለይም ሙሉ በሙሉ ነዋሪዎች የተፈናቀሉባት የኪረሙ የወረዳ ከተማ በቂ ያሉት የፀጥታ ሃይሎች እንዲገቡ ተደርጎ ወደ አጎራባች ወረዳዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ወደ ቀዬያቸው የመመለሱ ስራ መጀመሩንም አመልክተዋል፡፡

“ያው አሁን በቂ የፀጥታ ድጋፍ ደርሶናል፡፡ ለተፈናቃዮችም የሚሆን የተወሰኑ የእርዳታ ምግቦች አሁን ትናንት ኪረሙ ደርሷል፡፡ ቢያንስ አሁን የፀጥታ ሃይሉ የወረዳ ከተማዋን አረጋግቶአታል፡፡ ወጣ ያሉ ቀበሌያትን ለማረጋጋት ግን ገና ስራዎች ይቀራሉ፡፡ አሁን በወረዳዋ ከተማ ከዚያ ከሶስት ቀናቱ ጥቃት በኋላ የሆነ ነገር የለም፡፡ በተለይም ወደ ጊዳ አያና ወረዳ የተፈናቀሉትን በእርዳታ እና በጦር ሰራዊት ተሽከርካሪዎች የመመለስ ጥረት ተጀምሯል” ብለዋልም፡፡

ለሶስት ቀናት ቆይቶ በነበረው የኪረሙ ወረዳው የታጣቂዎች ጥቃት መሰረተልማቶች መውደማቸውን እና የበርካታ ሰዎች ህይት ማለፉም ነው የሚነገረው፡፡ አስተያየቱን የሰጡን የአከባቢው ባለስልጣንም ይህንኑን ሲያረጋግጡ፤ “በዚያች በሶስት ቀናት ግጭቱ 250 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ከነዚህ ሲቪሎች በተጨማሪ ከ40 በላይ የሚሆኑ የፀጥታ ሃይሎችም ተገድለዋል፡፡ ንብረትም በሚሊየኖች የሚገመት ነው የወደመው፡፡ ከወረዳው ጽህፈት ቤት ተሸከርካሪዎችን ማቃጠል እና ኮምፒዩተሮች ጨምሮ የቢሮ እቃዎችንም የማውደም ተግባር ተከናውኖ ነበር፡፡ የወረዳው ፖሊስ መምሪያ ጽ/ቤት ከነ መሳሪያዎቹ ተቃትሏል፡፡ ከወረዳው ከ100 በላይ እስረኞችም ተለቀዋል” ብለዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ ሀሮ ቀበሌን ጨምሮ አሁንም ከወረዳው አስተዳደር ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ቀበሌያት ይበዛሉ፡፡ ለውድመቱም ጽንፈኛ ያሏቸው የአማራ ታጣቂዎችን ነው ተጠያቂ የሚያደርጉት፡፡

ይሁንና ከዚህ በፊት አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የወረዳው የአማራ ተወላጆች በመንግስት መዋቅር የሚደገፍ ጥቃት ይደረግብናል ሲሉ ነው የሚከሱት፡፡ በአከባቢው ተደራጅቶ ሰላማዊ ዜጎችን የሚያጠቃ ሃይል እንደሌላቸውም ጭምር በማንሳት፡፡

IDPs from Horo guduru wollega
የሆሮ ጉዱሩ ተፈናቃዮች በሻምቡ ዩኒቨርሲቲምስል Seyoum Getu/DW

በሰሞነኛው የምስራቅ ወለጋው ግጭት ከኪረሙ እና ጊዳ አያና ወረዳዎች እንዲሁም ከአንገር ጉቲን ከተማ 31 ሺህ ገደማ ነዋሪዎች ከሃብት ቀዬያቸው መፈናቀላቸውን የሚያረጋግጡት የምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደር ምክትል ኃላፊ አቶ ገመዳ ተፈራ፤ አሁን ተፈጥሯል ባሉት የተሻለ አንጻራዊ ሰላም ነዋሪዎችን ወደ ቀዬያቸው የመመለስና እርዳታ የማቅረብ ጥረት መጀመሩን አመልክተዋል፡፡ ምክትል አስተዳዳሪው “ተከታታይ ውይይት በማድረግ ሰላም ወርዶ ህዝቡን ወደ ቀዬው መመለስ ቀዳሚው ትኩረታችን ነው፡፡ አሁን አንጻራዊ ሰላም ስለተፈጠረ፤ ትኩረት የሚፈልገው ከዚህ ቀደም የመፈናቀል ታሪክ ያልነበረውና ለሌላውም ይተርፍ የነበረውን ህዝብ በመርዳት መልሶ ማቋቀዋም ነው፡፡ በመንግስት በኩል አሁን በሶስቱም ወረዳዎች መጀመሪያ ደረጃ እርዳ ደርሶ የሌሎችም ርብርብ ይጠይቃልም” ብለዋል፡፡

በምስራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች ውስጥ በተደጋጋሚ ለሚከሰተውና እየተወሳሰበ ለመጣው የፀጥታ ችግር መንግስት ሸነ ያለው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ቡድን እና ጽንፈኛ በሚል የተገለጹ የአማራ ታጣቂዎች መኖራቸውን ከዚህ በፊት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መገልጹ ይታወሳል፡፡

በምስረቅ ወለጋ ዞን የኪረሙ እና ጊዳ አያና ወረዳዎች እንዲሁም በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ የጃርደጋ ጃርቴ፣ አሙሩ እና ጉዱሩ ወረዳዎች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አስከፊ በሆነ ግጭት ውስጥ ከገቡ ወረዳዎች መካከል መሆናቸውን በተደጋጋሚ መዘገቡም አይዘነጋም፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ