በጋምቤላ የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ ተፈናቃዮች ቁጥር አሻቀበ
ዓርብ፣ መስከረም 18 2016በጋምቤላ ክልል የባሮ ወንዝ ሞልቶ በተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ በትናንትናው ብቻ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎችን በአንድ ወረዳ ውስጥ መፈናቀላቸው ተዘገበ ። በክልሉ ከመስከረም ወር መጀመሪያ አንስቶ በባሮ፣ አኮቦና ጊሎ ወንዞች መሙላትና የጎርፍ መጥለቅለቅ የተፈናቀሉ ዜጎች 28ሺ845 መድረሱን የክልሉ መንግስት ዐስታውቋል ። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ የሆኑት አቶ ኡሞድ ኡሞድ 36,000 የሚደርሱ ነዋሪዎች ደግሞ በ9 ወረዳዎች ውስጥ ንብረታቸው መውደሙን አብራርተዋል ። ከትናንት በስትያ በክልሉ ጂካዎ በተባለ ወረዳ ሰዎች መፈናቀላቸው እና በርካታ ንብረት መውደሙ ተገልጿል ። በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ የወንዝ ሙላት እየጨመረ ሲሆን፤ በጋምቤላ ከተማ ግንመጠኑ መቀነሱ ተገልጿል ።
በኢትዮጵያ የጋምቤላ ክልል ከመስከረም 5 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ጀምሮ በጋምቤላ ክልል የባሮ፣ አኮቦና ጊሎ ወንዞች መጠን በዚህ ክረምት ወቅት በመጨመሩ በወንዞቹ ዳርቻ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ኡሙድ አመልክተዋል፡፡ የወንዝ ሙላት በተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ያስከተለው ጉዳት መጠን መጨመሩን የተናገሩት አቶ ኡሞድ ከትናንት በስትያ በጂካዎ ወረዳም በውኃ መጥለቅለቅ 3ሺ845 ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ገልጸዋል፡፡ በኑዌር ዞን 5 ወረዳዎችና ሌሎች ስፍራዎች የበርካታ ነዋሪዎችን ሰብል ማውደሙን ተናግረዋል፡፡ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ የአደጋ መካለከል ቢሮ በኩል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸው በመንግስትና የግል ድርጅች በኩል ለተወሰኑ የተፈናቀሉ ዜጎች የቤት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን አክለዋል፡፡
በኑዌር ብሔረሰብ ዞን የጂካዎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ አንድሪው ቱት በወረዳው የባሮ ወንዝ ሙላት ሰዎችን ከማፈናቀሉ በተጨማሪ በተቋማት ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ በወረዳው በሚገኙ ጤና ኬላዎችና ትምህርት ቤቶች ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል፡፡ የነዋሪው ሰብልና ቁም እንስሳትም ተጎድተዋል፡፡ የተፈናቀሉ ዜጎች በየእምነት ቤቶችና የተለያዩ ስፍራዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ በርካታ የነዋሪው ንብረት በመውደሙ የተፈናቀሉ ዜጎችም ሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አንድሪው አብራርተዋል፡፡
ጋምቤላ ከተማ ውስጥ በአራት ቀበሌዎች የተከሰተ የወንዝ ሙላት ከዚህ ቀደም ከ5ሺ በላይ ሰዎችን ማፈናቀሉ የተነገረ ሲሆን ሰሞኑን በጋምቤላ ከተማ ላይ የወንዝ ሙላት መቀነሱን አንድ የከተማው ነዋሪ ተናግረዋል፡፡
በጋምቤላ ክልል ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ በደረሰው የጎርፍ አደጋ175ሺ የሚደርሱ ሰዎች ተፈናቅለው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስትቲውት እስከ ነገ የሚኖረውን የአየር ሁኔታ አስመልክቶ በገለጸው ትንቢያ በሀገሪቱ አንድ አንድ ስፍራዎች ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ጠቅሷ፡፡ የሚጠበቀው ከባድ ዝናብ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ የአፈር መሸርሸር እና በእርሻ ማሳዎች ላይ የውሀ መተኛት ሊያጋጥም እንደሚችልና አርሶ አደሩ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል ።
ነጋሣ ደሳለኝ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሐንስ ገብረ-እግዚአብሔር