1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጀርመን ማግድቡርግ ከተማ የደረሰ ጥቃት

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 12 2017

በጀርመን ማግድቡርግ ከተማ የገና በዓል በማክበር ላይ በነበሩ በርካታ ነዋሪዎች ላይ አንድ ግለሰብ መኪናውን በከፍተኛ ፍጥነት በማሽከርከር በፈጸመው ጥቃት 5 ሰዎች ሲሞቱ ከ 200 በላይ በላይ ቆስለዋል። በጥቃቱ የተጠረጠረ አንድ ሳውዲአደቢያዊ ዶክተር በቁጥጥር ሥር ውሏል።

https://p.dw.com/p/4oSPG
መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስየጥቃቱ ቦታ ሲጎበኙ
መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስየጥቃቱ ቦታ ሲጎበኙምስል Ebrahim Noroozi/AP Photo/picture alliance

በጀርመን ማግድቡርግ ከተማ በገና ገበያ ላይ በነበሩ በርካታ ነዋሪዎች ላይ አንድ ግለሰብ መኪናውን በከፍተኛ ፍጥነት በማሽከርከር በፈጸመው ጥቃት 5 ሰዎች ሲሞቱ ከ200 በላይቆስለዋል። በጥቃቱ የተጠረጠረ አንድ ሳውዲአደቢያዊ ሀኪም በቁጥጥር ሥር ውሏል።
ጀርመኖች የገና በዓል ከመድረሱ አንድ ወር ገደማ ሲቀረው በገና ዛፎችና መብራቶች ባሸበረቁ አደባባዮች «ግሉቫይን» እየተባለ የሚጠራውን ለብ ያለ ባሕላዊ የወይን መጠጥና ባሕላዊ ምግቦች እየተጠቀሙ በየምሽቱ መዝናናት የተለመደ ባሕላዊ እሴታቸው እንደሆነ ይታወቃል። በዘንድሮ የገና አከባበር ድንገተኛ ጥቃቶች ሊፈጸሙ እንደሚችሉ የጀርመን ፖሊስ ቀደም ሲል ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበረ። ትላንስ ምሽት ከበርሊን በስተደቡብ ምስራቅ በምትገኘው ማግድቡርግ ከተማ የገና በዓል በማክበር ላይ በነበሩ በርካታ ነዋሪዎች ላይ አንድ ግለሰብ መኪናውን በከፍተኛ ፍጥነት በማሽከርከር በፈጸመው ጥቃት 5 ሰዎች ሲሞቱ ከ 200 በላይ ደግሞ መቁሰላቸውን ፖሊስ አስታውቋል። ከቆሰሉት ውስጥ 41ዱ ክፉኛ መጎዳታቸውንም ዘገባዎች ያመለክታሉ።
ፖሊስ በጥቃቱ የጠረጠረውን የ50 ዓመቱ ሳውዲአረቢያዊ ሐኪም በቁጥጥር ሥር አውሏል። ይህ የሥነአእምሮ ሕክምና ባለሙያ የሆነው ሳውዲአረቢያዊ እንደጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ2006 ጀምሮ በጀርመን ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ አግኝቶ ይኖር እንደነበር ፖሊስ አክሏል። ይሁንና ድርጊቱ ከጽንፈኛ የፖለቲካ አልያም የሃይማኖት እሳቤ የመነጨ ይሁን አይሁን ለመናገር ጊዜው እንዳልሆነ ፖሊስ አስታውቋል።
የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ጉዳት የደረሰበትን ቦታ የጎበኙ ሲሆን የሐዘን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ሾልስ በመልዕክታቸው ይህን ጭካኔ የተሞላበት ያሉትን ድርጊት አውግዘው ህጉ የሚፈቅድልንን ሃይል ተጠቅመን ለጥቃቱ ምላሽ እንሰጣለን ብለዋል።  ጀርመኖች በአንድነት እንዲቆሙም ጥሪ አስተላልፏል።
ጥቃት የፈጸመው የሥነአዕምሩ ሐኪሙ የእስልምና ጠል መሆኑን የጀርመን የሐገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፌዘር አስታውቀዋል። የተለያዩ የዜና ምንጮች ደግሞ ተጠርጣሪው በግል የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ገጹ ቀደም ሲል የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ እንደነበረ መግለጹን፤ የእስልምና ሃይማኖትን የሚያንቋሽሽ ይዘት ያላቸው መልእክቶች ያስተላልፍ እንደነበረም ዘግበዋል።
 የዛሬ 8 ዓመት በተመሳሳይ በጀርመኖች ባሕላዊ የገና ገበያ ላይ በአንድ ቱኒዝያዊ በተፈጸመ የመኪና ጥቃት 13 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።
የጀርመን የእግር ኳስ ማህበር በበኩሉ በሳምንቱ መጨረሻ የሚካሄዱ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት በማድረግ እንዲጀመሩ አዟል። የዜናዎቹ ምንጮች የጀርመን ዜና አገልግሎትና (DPA) እና አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ናቸው።