1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችኢትዮጵያ

በድሮን ጥቃቶች በአማራ ክልል የሚገደሉ ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ነው

ዓርብ፣ ኅዳር 20 2017

በአማራ ክልል በመንግሥት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በድሮን ጥቃቶች የሚገደሉ ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት እና መከላከያ ሠራዊት እርምጃዎቹ ንጹኃንን ዒላማ እንደማያደርጉ ቢገልጹም ሕጻናት፣ እናቶች የጤና ባለሙያዎች ጭምር መገደላቸውን ዘገባዎች ያሳያሉ።

https://p.dw.com/p/4nZLf
የቱርክ ሥሪት የሆነው ባይራክታር ቲቢ2 (Bayraktar TB2) ድሮን
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከታጠቃቸው ሰው አልባ አውሮፕላኖች መካከል የቱርክ ሥሪት የሆነው ባይራክታር ቲቢ2 (Bayraktar TB2) የሚገኝበት ሲሆን ድሮኖቹን የሚያመርተው የግል ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሐይሉክ ባይራክታር ባለፈው ዓመት ከመከላከያ ሠራዊት የክብር ሜዳይ ተሸልመዋል። ምስል Getty Images/AFP/B. Bebek

ትንሿ የገጠር ከተማ ዝብስት በአማራ ክልል ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ “በአንድ ጊዜ ብዙ ሰዎች የተገደሉበት የአየር ጥቃት” አስተናግዳለች። የኢትዮጵያ መንግሥት እና የፋኖ ታጣቂዎች ከፍተኛ ውጊያ ከሚያደርጉባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች አንዱ በሆነው በምዕራብ ጎጃም ዞን በምትገኘው “ንዑስ ከተማ” ጥቃቱ የተፈጸመው ጥቅምት 26 ቀን 2017 ነው።

በገበያ፣ በትምህርት ቤት እና በጤና ጣቢያ ላይ በተፈጸመው ጥቃት መጀመሪያ 43 ሰዎች መገደላቸው በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሪፖርት ቢደረግም የሟቾች ቁጥር “ወደ 51” መድረሱን የአካባቢው ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በግብርና ሥራ የሚተዳደሩት የደቡብ አቸፈር ነዋሪ እንደሚሉት በዕለተ-ማክሰኞ ጥቃት ሲፈጸም ከዝብስት አቅራቢያ ነበሩ። 

“ሲሔድ ድምጹ በጣም አይሰማም” የሚሉት የዐይን እማኝ ለደሕንነታቸው በመስጋት ማንነታቸው እንዲገለጽ አይፈልጉም። “ጥጥጥ…ጥጥጥ…ጥጥጥ…እያለ ነው የሔደው” ይላሉ በወቅቱ የሰሙትን ድምጽ ሲያስረዱ። “እኛ ባናውቀውም ሰው ይኸ ድሮን የሚባለው ነው ይላል” ሲሉ ተናግረዋል።

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የዐይን እማኞች ጥቃቱ በፋኖ ሰልጣኞች ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ይናገራሉ። ሰልጣኞቹ “ምንም መሣሪያ የላቸውም። እየተከተለ የማጥፋት ሥራ እየተሰራ መሰለኝ” ሲሉ ሁለተኛ የዐይን እማኝ ተናግረዋል። በሰልጣኞቹ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ “አካባቢውን ደጋግሞ ሕጻናትንም ሳይቀር በዙሪያው ያሉትን መትቶ ወደ 40 ያሕል ሰዎች አጥፍቷል” ሲሉ አክለዋል። ሌላ የዐይን እማኝ ጥቃቱ “ወዲህ እና ወዲህ እያለ፤ እያካበበ፣ እየተመለሰ” የተፈጸመ እንደሆነ ገልጸዋል።

“በአማራ ክልል ግጭት ከተጀመረ ወዲህ በአንድ ጊዜ ብዙ ሰዎች የተገደሉበት” ሆኖ በኢትዮጵያ ፒስ ኦብዘርቫቶሪ በተመዘገበው የዝብስት ጥቃት ሕይወታቸውን ካጡ መካከል ሕጻናት፣ እርጉዝ እናቶች፣ እና የጤና ባለሙያዎች ጭምር እንደሚገኙበት ዘገባዎች ይጠቁማሉ።

ከዝብስት በፊት በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ፣ በደቡብ ወሎ ዞን መኻል ሣንይት ወረዳ ደንሳ የተባለ ቦታ፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ማጀቴ እና ሰላ ድንጋይ የተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች በቁጥር ብዙ ሰዎች የተገደሉባቸው ነበሩ።

በደቡብ አቸፈር ወረዳ በምትገኘው ከተማ የተፈጸመው ጥቃት ግን በአይነቱ የተለየ እንደሆነ በአክሌድ የኢትዮጵያ ፒስ ኦብዘርቫቶሪ ከፍተኛ ተመራማሪ ብራንደን ፉለር ይናገራሉ። “አብዛኞቹ ጥቃቶች የሚፈጸሙት በአቅራቢያው ወይም በቦታው በሚኖር የግጭት አውድ ውስጥ ነው” የሚሉት ብራንደን ፉለር በዝብስት “ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት በቦታው ግጭት ያልነበረ በመሆኑ በተወሰነ ደረጃ የተለየ ነው” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የዐይን እማኞችም በአካባቢው የፋኖ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ ቢኖርም ጥቃቱ ሲፈጸም ግን ግጭት እንዳልነበር ገልጸዋል።

በክልሉ በመንግሥት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ከሚያዝያ 2015 እስከ ሕዳር 2017 ባለው ጊዜ የኢትዮጵያ ፒስ ኦብዘርቫቶሪ 54 የድሮን እና የአየር ጥቃቶች መፈጸማቸውን መዝግቧል። ይሁንና “ራቅ ባሉ የሀገሪቷ አካባቢዎች የሚፈፀሙ የድሮን ጥቃቶችን ለመዘገብ ያለው አስቸጋሪ ሁኔታ ሲታይ ይህ አሃዝ ዝቅተኛ ግምት” ሊሆን እንደሚችል አስታውቋል። ሰሜን ሸዋ እና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች ብዛት ያላቸው የድሮን እና የአየር ጥቃቶች የተፈጸመባቸው ናቸው።

የመጀመሪያው የድሮን ጥቃት በምዕራብ ጎጃም ዞን በምትገኘው ቡሬ ከተማ ነሐሴ 6 ቀን 2015 የተፈጸመ ነው። በማግሥቱ ማለትም ነሐሴ 7 ቀን 2015 ቀን በዚያው በምዕራብ ጎጃም ዞን የምትገኘው የፍኖተ-ሰላም ከተማ በርካታ ሰዎች የተገደሉበት የአየር ጥቃት አስተናግዳለች። 

በአጠቃላይ በጥቃቶቹ 449 ሰዎች በድሮኖች እና የአየር ጥቃቶች መገደላቸው ሪፖርት እንደተደረገ በኢትዮጵያ ፒስ ኦብዘርቫቶሪ ተመዝግቧል።

የአማራ ማኅበር በሰሜን አሜሪካ የአድቮኬሲ ዳይሬክተር ሆነ ማንደፍሮ በአማራ ክልል እየተደረገ ባለው ጦርነት መንግሥት “በከፍተኛ ደረጃ ድሮን መሠረት ያደረገ” በመሆኑ “ንጹኃን ዜጎች ላይ ከፍተኛ ሰብአዊ ጉዳት እየደረሰ ነው” ሲሉ ይናገራሉ።

ጥቃቶቹ ሰዎች የሚሰበሰቡባቸው አደባባዮች፣ የትምህርት፣ የጤና እና የዕምነት ተቋማት ዒላማ ማድረጋቸውን የሚናገሩት አቶ ሆነ “ምንም አይነት ከጦርነቱ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ንጹኃኖችን እየጨፈጨፉ ነው። ይኸ ደግሞ በስሕተት አይደለም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

መንግሥት “በተደጋጋሚ ተዋጊ ሠራዊት ልኮ ስለተሸነፈበት ያለው አማራጭ ሕብረተሰቡን አሸብሮ ፋኖዎቹ ድጋፍ እንዳያገኙ ማድረግ ነው” ሲሉ አቶ ሆነ ይከሳሉ።

ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ
ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ “የጽንፈኛ ስብስብ ስናገኝ በድሮን እንመታለን” ሲሉ በታኅሳስ 2016 ተናግረው ነበር። በወቅቱ በጥቃቶቹ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ቢባልም ፊልድ ማርሻሉ “ሕዝብ ላይ ድሮን አይጣልም” ሲሉ ተደምጠዋል። ምስል Office of the Prime Minister

ማኅበራቸው ከጥቅምት 5 ቀን 2016 እስከ ሕዳር 14 ቀን 2017 ባለው ጊዜ ውስጥ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ 125 የድሮን እና የአየር ጥቃቶች 754 ሰዎች መገደላቸውን እና 223 መጎዳታቸውን መዝግቧል። “እኛ የምንመዘግባቸው የድሮን ጥቃቶች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ብቻ ዒላማ ያደረጉ ናቸው” የሚሉት አቶ ሆነ “ተዋጊ ኃይሎች ላይ የድሮን ጥቃት ከደረሰ አንመዘግብም” ሲሉ አስረድተዋል።

መከላከያ ሠራዊት እና የኢትዮጵያ መንግሥት ምን ይላሉ?

መከላከያ ሠራዊት በተለይ የፋኖ ታጣቂዎች በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ከዚህ ቀደም የፈጸማቸው የድሮን ጥቃቶች በነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ሐዘን የፈጠረ ነው። አቶ ሆነ ማንደፍሮ “ሰዎች ወደ ገበያ መሔድ አይችሉም። ወደ ጤና ተቋማት መሔድ አይችሉም። ወደ የዕምነት ተቋማት መሔድ አይችሉም። ከተማ ውስጥ እንኳን በአደባባይ ከሰዎች ጋር መገናኘት አልቻሉም” ሲሉ ተጽዕኖው ኃይለኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዶይቼ ቬለ ከመከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ እና ከአማራ ክልል የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

መከላከያ ሠራዊት በአማራ ክልል ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር በሚደረጉ ውጊያዎች ሰው አልባ አውሮፕላኖች ግልጋሎት ላይ መዋላቸውን ባያስተባብልም በጥቃቶቹ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ግን አይቀበልም።

በሰሜን ጎጃም ዞን የተሠማራው የመከላከያ ሠራዊት የምሥራቅ ዕዝ አመራሮች ጥቅምት 2 ቀን 2017 በሰሜን ሜጫ ወረዳ አማሪት ከተሰኘች ከተማ አቅራቢያ በድሮን በተፈጸመ ጥቃት የፋኖ ታጣቂዎች መገደላቸውን ለብሔራዊው ቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

የአማራ ማኅበር በሰሜን አሜሪካ በጥቃቱ ስድስት ገበሬዎች መገደላቸውን እና አራት መቁሰላቸውን ይፋ አድርጓል። የምሥራቅ ዕዝ የ302ኛ ኮር ኅብረት ዘመቻ ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ብርሀኑ አሻግሬ ግን የተፈጸመው የድሮን ጥቃት “ጽንፈኛው ኃይል” ባሉት በፋኖ ታጣቂዎች ላይ ብቻ ያነጣጠረ እንደሆነ ተናግረዋል።

የጦር መኮንኑ “በንጹኃን ሰው ላይ ነው እርምጃ የተወሰደው እንጂ ጽንፈኛውን ኃይል አልነካም” ተብሎ መዘገቡን “ከእውነት የራቀ ውሸት” ሲሉ አጣጥለዋል።

የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሠ ቱሉ “ጽንፈኛ ኃይል” ባሉት የፋኖ ታጣቂዎች ላይ መንግሥት የሚወስደው እርምጃ “በተመረጠ እና በታቀደ መልክ” እንደሆነ ሕዳር 7 ቀን 2016 ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ተናግረዋል። መገናኛ ብዙኃን “ንጹኃን ላይ የተወሰደ እርምጃ አድርገው ያቀርቡታል” ያሉት ዶክተር ለገሠ “ይኸ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም” ሲሉ ተደምጠዋል።

ዶይቼ ቬለ ተጨማሪ አስተያየት ለመጠየቅ ወደ ዶክተር ለገሠ ቱሉ ስልክ ቢደውልም ምላሽ አላገኘም።

መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከሐምሌ 2015 እስከ ሰኔ 2016 በክልሉ በከባድ መሣሪያ፣ ድሮንን ጨምሮ በአየር በተፈጸሙ ድብደባዎች “ሴቶች፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች እና ሕጻናትን ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሲቪል ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ” መገደላቸውን በዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚደረገው ውጊያ በተፋፋመበት ወቅት “በሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሌሎች ጥቃቶች በአማራ ክልል ሕዝብ ላይ የሚደርሰው አስከፊ ጉዳት አሳሳቢ” መሆኑን በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ሰይፍ ማጋንጎ ገልጸው ነበር።

የፋኖ አባል በላሊበላ
መከላከያ ሠራዊት በአማራ ክልል የሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች የፋኖ ታጣቂዎችን ብቻ ዒላማ ያደረጉ እንደሆኑ ቢገልጽም በጥቃቶቹ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን በርካታ ዘገባዎች ይጠቁማሉምስል Solan Kolli/AFP/Getty Images

በኢትዮጵያ የውጊያ ድሮኖች በስፋት ጥቅም ላይ መዋል የጀመሩት በፌድራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ለሁለት ዓመታት ውጊያ በተደረገበት ወቅት ነው። ጦርነቶቹ ታንኮችን ጨምሮ ከባድ የጦር መሣሪያዎች የታጠቁት የትግራይ ኃይሎች ከመንግሥት ጋር ያደርጉት በነበረው ውጊያ ላይ ብራንደን ፉለር “ከፍተኛ” የሚሉት ጫና አሳድረዋል።

በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ላይ ግን የድሮን ጥቃቶች ይኸ ነው የሚባል ተጽዕኖ ማሳደር እንዳልቻሉ ይናገራሉ። “የታጣቂዎቹን ከፍተኛ አመራሮች ዒላማ አድርገው ሊሆን ይችላል” የሚሉት ብራንደን ፉለር “የድሮን ጥቃቶቹ በፋኖ ታጣቂዎች ላይ ጉልህ ተጽዕኖ አሳርፈዋል” የሚል እምነት የላቸውም። “የድሮን ጥቃቶቹ በተደጋጋሚ ሲቪል ዒላማዎችን እየመቱ ነው። ይኸ ደግሞ የመንግሥትን ተቀባይነት ሊጎዳ፣ ሰዎች ግጭቱን እና የመንግሥት የድሮን አጠቃቀም በተመለከተ ያላቸውን አተያይ ሊቀይር ይችላል” ሲሉ ያብራራሉ።

“ባለፉት ሣምንታት እንደታየው ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የሕዝቡን አመለካከት ሊቀይሩ እና ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲጥ” ሊያስገድዱ እንደሚችሉ ብራንደን ፉለር ያምናሉ። ይሁንና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት “ከዚህ ቀደም በሕዝብ እና በዓለም አቀፍ ጫና” አቋሙን ሲለውጥ እንዳልታየ የሚያስታውሱት ብራንደን ፉለር “ድሮን መጠቀማቸውን ይቀጥላሉ። ነገር ግን ውጤታማ አይሆኑም” የሚል አስተያየት አላቸው።

የአማራ ክልል ቀውስ ውስጥ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ታኅሳስ 2016 ውጊያ፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸም ጥቃት፣ የአየር ድብደባ እና ፍንዳታዎች የመሳሰሉ አብዛኞቹ የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች የተመዘገቡት በምዕራብ ጎጃም፣ ሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ እና ምሥራቅ ጎጃም ዞኖች ውስጥ እንደ ቅደም ተከተላቸው እንደሆነ በአክሌድ የምሥራቅ አፍሪካ የትንታኔ ከፍተኛ አስተባባሪ ዶክተር ጃለሌ ጌታቸው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ፒስ ኦብዘርቫቶሪ ምዝገባ መሠረት ከታኅሳስ 2016 እስከ ጥቅምት 2017 ባለው ጊዜ በአንጻሩ ምዕራብ ጎጃም፣ ምሥራቅ ጎጃም፣ ሰሜን ሸዋ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች በቅደም ተከተላቸው ብዛት ያላቸው የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች የተመዘገበባቸው ናቸው።