1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የበልግ ዝናብ ተስፋ እና ስጋት

ማክሰኞ፣ መጋቢት 20 2014

ከሰሞኑ መጠነኛ የበልግ ዝናብ ኢትዮጵያ ውስጥ መዝነብ መጀመሩ እየተነገረ ነው። የዝናቡ መምጣት በተለይ በተከታታይ የዝናብ ወቅቶች መስተጓጎል ምክንያት በድርቅ ለተጎዱት የሀገሪቱ ቆላማ አካባቢዎች ተስፋ ቢሆንም አርብቶ አደሮች ግን ከብቶቻቸው እንዳያልቁባቸው ስጋት ገብቷቸዋል።

https://p.dw.com/p/49Byv
ምስል Seyoum Getu/DW

ጤና እና አካባቢ

የቦረናው አርብቶ አደር አሬሮ ጨሪ ድርቅ ከመከሰቱ በፊት 150 ከብቶች ነበሯቸው። ዛሬ ግን አካላቸው በድርቁ ምክንያት የደከመ 50 ከብቶች ብቻ እንደቀሯቸው ነግረውኛል። የበልግ ዝናብ ስለመዝነቡ ይወራ እንጂ ዝናቡ በሁሉም አካባቢዎች ገና አልተዳረስም ነው የሚሉት።

ድርቅ በጎዳው አካባቢ ዝናብ መዝነቡ ተስፋ ቢሆንም ለአርብቶ አደሮቹ ግን ሌላ የስጋት ምንጭ መሆኑን ነው የተረዳነው። ከወራት በፊት በድርቁ መሀል ድንገት ለአንድ ቀን የዘነበ ኃይለኛ ዝናብ በአንድ ምሽት አምስት ሺህ ገደማ ከብቶችን መፍጀቱን በቦረና ዞን የእንስሳት ጤና ጥበቃ ባለሙያው ዶክተር ገልማ ዋቄ ገልጸውልናል።

«ባለፈውም እንደዚህ ዘንቦ ነበር ብዙ እንስሳት ሞተዋል ያኔ። እንዲህ ቀስ ቀስ ብሎ ቢሆን ለአርብቶ አደሩም ለእንስሳውም ጥሩ ነው ብዬ እገምታለሁ። እንደባለፈው በአንድ ቀን ብዙ ዘንቦ ብዙ እንስሳት ወደ 75 ሺህ ከብቶችን ጨርሷል በአንድ ማታ ማለት ነው።»

BG Dürre | Äthiopien
ምስል picture-alliance/AP Photo/E. Meseret

የሰሞኑ ዝናብም ለከብቶች መሞት ምክንያት መሆኑን የቦረናው አርብቶ አደር አሬሮ ጨሪ ይናገራሉ።

«አሁን እራሱ ዝናብ መዝነብ ከጀመረ አምስተኛ ቀኑ እንደዚህ ነው። ሁሉ ቦታ ባያዳርስም፤ ዝናብ በዘነበ ማታ ለምሳሌ እኛ ወረዳ ዳስ ወረዳ ኦዳ አሬሮ የሚባል ሰው ወደ 80 ከብት በአንድ ማታ ሞቶበታል።»

ነው የሚሉት። ከብቶቻቸውን ማጣቱ ለእነሱ ከባድ የኑሮ ድቀት ነውና ከብርዱ እንዲከላከልላቸው በሚል ሸራ ገዝተው ለከብቶቻቸው መጠለያ እየሠሩ ነው። ከብቶቻቸውን በዚህ መልኩ የሚሳጣቸው ከሆነ መዝነቡን ይፈልጉት ይኾን?

«እንዴ መዝነቡንማ እንፈልጋለን። አንዴ እኮ ሞትም ትክክለኛ ቁርጠኛ መሞት ነው። ያለቀው ይለቅ እና የተረፈው እንዲኖር ዝናብ መዝነቡን እንፈልጋለን።»

በቦረና ዞን ሞያሌ ወረዳ የሚገኙት ሌላኛው አርብቶ አደር በበኩላቸው ዝናብ መዝነቡ አንድ ነገር ቢሆንም ለከብቶቹ የሚሆነው ሳር እስኪበቅል ጊዜ እንደሚፈልግ እንዲህ ነው የገለጹት።

Dürre in Somali Region
ምስል Michael Tewelde/World Food Programme/REUTERS

«ዝናብማ ዘንቧል፤ ዝናብ ግን ውኃ ነው የዘነበው ሳር አልዘነበም። ስለዚህ ድሮም ከብቱ የከሳው ውኃ ስላጣ ብቻ አይደለም ሳር የሚበላው ስልጣ እንጂ።»

ድርቁ ከብቶቹን ብቻ ሳይሆን ነዋሪውን ማኅበረሰብም ለችግር እንደዳረገው፤ ምንም እንኳን የእህል ርዳታ ቢቀርብም በቂ እንዳልሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል። የምሥራቅ አፍሪቃ አካባቢ ሃገራት ከ40 ዓመታት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ድርቅ ለከፋ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውን የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት በቅርቡ ይፋ አድርጓል። ለተከታታይ ዓመታት የተስተጓጎለው የዝናብ እጥረት መንስኤ በሳይንሱ ኤሊኞ እና ላኒኛ የሚባለው ክስተት ይኹን የተባባሰው የአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ እርግጠኛ ሆኖ መናገር እንደማይቻል የአካባቢ ተፈጥሮ ጉዳይ ባለሙያው አቶ ያለምሰው አደላ ይገልጻሉ።

ያነጋገርናቸው የቦረናዎቹ አርብቶ አደሮች አሁን ዝናብ መዝነቡ ተስፋ ቢሆናቸውም አቅማቸው የተዳከመው ከብቶቻቸውን እንዳያጡ ስጋት እንዳላቸው ነው የገለጹልን። ችግሩ በከብቶቻቸው ብቻ ባለማብቃቱም ዛሬም በቂ የምግብ እርዳታ ፈላጊዎች ናቸው። የቦረና ዞን ሞያሌ ወረዳው አርብቶ አደር፤

«እኔ በዚህ አጋጣሚ ማስተላለፍ የምፈልገው የውጭ እርዳታ እና የመንግሥትም ይኼንን ነገር ትኩረት ሰጥቶበት ቢያንስ የቦረና ከብት ዝርያ ለዘር እንኳን እንዳይዘፉ እያንዳንዱ መንግሥት ጥረት ማድረግ አለበት ነው የምለው።»

BG Dürre | Äthiopien
ምስል picture-alliance/AP Photo/E. Meseret

ድርቁ የጎዳቸው የአካባቢው ከብቶችን የጤና ሁኔታ የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች በየዞኑ እንደሚከታተሉ ነው የዞኑ የዘርፉ ባለሙያ ዶክተር ጋልማ የነገሩን። በአካባቢው አሁን የዝናብ ወቅት መሆኑን የገለጹልን ባለሙያው ምንም እንኳን ለጊዜው ዝናቡ ሁሉን አካባቢዎች ላይ ባይጥልም ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚችል ካለፈው የተለመደ የዝናብ ሁኔታ በመነሳት ይናገራሉ። የቦረና ዞን ዳስ ወረዳው አርብቶ አደርም በበኩላቸው መዝነብ የጀመረው የበልግ ዝናብ እንደተለመደው እስከ ግንቦት ሊቀጥል ይችላል የሚል ተስፋ አላቸው።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ድርቁ በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ ሚሊየኖችን ለምግብ እጥረት አጋልጧል። የበልግ ዝናብ በአንዳንድ አካባቢዎች መጀመሩ ተስፋ ቢሆንም ዛሬም ሚሊየኖች የምግብ ርዳታ ይፈልጋሉ።

ሸዋዬ ለገሠ