1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በደቡብ ኢትዮጵያ ዳውሮ ዞን የሚገኘው ከሰል ማዕድን

ሐሙስ፣ ሐምሌ 7 2014

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን የሚመረተው የከሰል ማዕድን በጥቂት ኩባንያዎች ለምዝበራ መዳረጉን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። ዶቼ ቬለ ከምንጮች እንዳረጋገጠው በአካባቢው በከሠል ማዕድን ምርት የተሠማሩ አራት ኩባንያዎች ባለፉት 6 ወራት ከ32 ሺህ ቶን በላይ የከሰል ድንጋይ አምርተው ወደ መሀል አገር አጓጉዘዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4E968
Coal mining in Dawro, Ethiopia
ምስል Dawro zone government communications affairs

የዳውሮ ዞን ከሰል ማዕድን

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን የሚመረተው የከሰል ማዕድን በጥቂት ኩባንያዎች ለምዝበራ መዳረጉን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። ዶቼ ቬለ DW ከታማኝ ምንጮች እንዳረጋገጠው በአካባቢው በከሠል ማዕድን ምርት የተሠማሩ አራት ኩባንያዎች ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ32 ሺህ ቶን በላይ የከሰል ድንጋይ አምርተው ወደ መሀል አገር አጓጉዘዋል፡፡ ይሁንእንጂ ኩባንያዎቹ እስካሁን ምርቱን ወደ የት እና በምን ያህል ዋጋ እንደሚሸጡ ምንም አይነት ሕጋዊ የግብይት ሠነድ ካለማቅረባቸውም በላይ  በሥራቸው ለተደራጁ ከ500 በላይ ወጣቶችም ክፍያ አለመፈጸማቸው እየተነገረ ነው። 

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በዳውሮ ዞን ከሚገኙት 10 ወረዳዎች 6ቱ ሰፊ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ክምችት እንዳላቸው ይናገራል፡፡ በዞኑ ከሚገኙት ወረዳዎች አንዱ በሆነው ተርጫ ዙሪያ ወረዳ በ4 የማዕድን አምራች ኩባንያዎች እና በስምንት ማሕበራት የተደራጁ ከ500 በላይ የአካባቢው ወጣቶች ከያዝነው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ በምርት ሂደት ላይ ይገኛሉ። የከሰል ማዕድን ምርት ሥራው ሲጀመር ከሽያጩ የሚገኘው ትርፍ 70 በመቶ ለኩባንያዎቹ ፣ 30 በመቶ ደግሞ ለማሕበራቱ እንደሚሆን በውል ላይ የተመሠረተ ሥምምነት መገባቱን ከዞኑ ውኃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት 32 ሺህ ቶን የከሰል ማዕድን ተመርቶ በኩባንያዎቹ አማካኝነት ለሽያጭ መቅረቡን ኑዋን እና ለውጥ የተባሉ የወጣት ማሕበራት ሊቃነመናብርት የሆኑት ዳዊት ደስታ እና እዝቅኤል ተረፈ ይናገራሉ፡፡ ይሁንእንጁ የወጣት ማሕበራቱ እስካሁን በውሉ መሠረት የሚገባቸውን ክፍያ አላገኙም፤ ኩባንያዎቹም ማቅረብ የነበረባቸውን የሸያጭ ሠነዶች አላቀረቡም።

Coal mining in Dawro, Ethiopia
ምስል Dawro zone government communications affairs

በዚህም የተነሳ የማዕድን ምርት ሂደቱ ግልጽነት የጎደለውና ለምዝበራ የተጋለጠ እንዲሆን አድርጎታል ይላሉ የማሕበራቱ ሊቀመናብርት። የማሕበራቱ  ሊቀመናብርት ዳዊት እና ሕዝቅኤል መንግሥት የሽያጭ ሂደቱን በመመርመር ግልጽ አሠራር እንዲሰፍን እና የትርፍ መጠኑም ተጣርቶ ክፍያዎች እንዲፈጸሙላቸው የዳውሮ ዞን ውኃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያን ቢጠይቁም ምላሽ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ዶቼ ቬለ DW በስልክ ያነጋገራቸው የዳውሮ ዞን ውኃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ዋዳ የከሰል ድንጋይ ምርቱ ለኃይል አገልግሎት እንዲውል ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች እየቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ኩባንያዎቹ ምርቱን በቀጥታ ለፋብሪካዎቹ ከማቅረብ ይልቅ በወኪሎች አማካኝነት እያቀረቡ እንደሚገኙ እና ለዚህም የገቡትን ጥቅል የሽያጭ ውል ሠነድ ማቅረባቸውን የጠቀሱት ኃላፊው የማሕበራቱ ክፍያን በተመለከተም ኩባንያዎቹን በደበዳቤ ጠይቀው ምላሽ እየጠበቁ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

Coal mining in Dawro, Ethiopia
ምስል Dawro zone government communications affairs

ዶቼ ቬለ DW የወጣት ማሕበራቱን ቅሬታ አስመልክቶ ካነጋገራቸው ኩባንያዎች መካከል የኢትዮ ስታር ኩባንያ ሥራ አስኪያጁ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ባይሆኑም  የኪቶራ ዳውሮ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ነሲብ ተርፋስ ግን ኩባንያቸው ሠነዶችን ማቅረቡን እንደሚያውቁ ተናግረዋል ፡፡

በአሁኑ ወቅት የማሕበራቱን ክፍያ ለመፈጸም የሚያስችሉ የትርፍ ልየታ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ እና ሂደቱ እንዳለቀ በቅርቡ ክፍያውን እንፈጽማለንም ብለዋል። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የማዕድን እና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጁ ኢንጅነር ፍቅሬ ኃይሌ በከሰል ድንጋይ ማዕድን ምርት ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ 

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ