1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሰላም ለማስፈን የሚደረገው ጥረትና አፍሪቃውያን በጀርመን

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 1 2015

ድርድሩ በባለዘጠኝ ነጥብ እቅድ ቢጠናቀቅም፣ውጤቱ አሁንም ግልጽ አይደለም።በግልጽ የተታወቀው የኮንጎ መንግሥትና የአካባቢው ማኅበረሰብ ውይይት ይቀጥላል መባሉ ነው።ኬንያታ ደግሞ በኮንጎ ሰላም ሊሰፍን ጅምር ላይ ነው ብለዋል። ይሁንና በለንደኑ ቻተም ሃውስ የጥናት ተቋም የአፍሪቃ መርሀግብር ሃላፊ አሌክስ ቪነስ ግን ይህ ተግባራዊ መሆኑን ይጠራጠራሉ።

https://p.dw.com/p/4Kktk
Kenia Nairobi | Friedensgespräche Delegation DR Kongo
ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሰላም ለማስፈን የሚደረገው ጥረት

የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ መንግሥትና ታጣቂ ሚሊሽያዎች በቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታ አደራዳሪነት ያካሄዱት የናይሮቢው የሰላም ጉባኤ  ባለ ዘጠኝ ነጥብ እቅድ በማውጣት በዚህ ሳምንት ተጠናቋል። ይሁንና በዚህ ድርድር መሳተፉ አስፈላጊ ነበር የተባለው አማጺው ኤም 23  በድርድሩ አልተካፈለም። ሆኖም ቡድኑ በዚህ ሳምንት ከተጠናቀቀው ድርድር በኋላ በሰጠው መግለጫ ባልተጠበቀ ሁኔታ ምሥራቅ ኮንጎ ከሚገኘው ከሰሜን ኪቩ ለቆ እንደሚወጣ አስታውቋል። ምንም እንኳን ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ባጎርጎሮሳውያኑ ህዳር መጨረሻ ተኩስ ለማቆም ተስማምተው የነበረ ቢሆንም በሰላም ድርድሩ ወቅት አማጺው የኤም 23 ቡድን ውጊያ ተፋፍሞ መቀጠሉ አስስቧል።በዚህ ውጊያ አማጽያኑ በከባድ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተከሰዋል። በኮንጎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ በቅርቡ ባወጣው ዘገባ የኤም 23 ተዋጊዎች ድርድሩ እየተካሄደ ሰሜን ኪቩ ውስጥ 131 ሰዎችን መግደላቸውን አስታውቋል። ኪሺሼና ባምቦ በተባሉት ከተሞች የተፈጸመው ፍጅት የተመድ ዘገባ የበቀል እርምጃ አካል ነው ያለው ።በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካባቢውን ለቀው ሸሽተዋል። ዶቼቬለ ያነጋገራቸው የኮንጎ የኢንዱስትሪ ሚኒስትርና የቀድሞ የሰሜን ኪቩ ሀገረ ገዥ ጁልየን ፓሉኩ በዚያ የሆነውን በኮንጎ ምድር የተካሄደ የታቀደ የዘር ማጥፋት ወንጀል ብለውታል። ምሥራቅ ኮንጎ ውስጥ በቅርቡ የተቀሰቀሰው ግጭት በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክን በምሥራቅ በኩል  በምትጎራበታት በሩዋንዳ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ፈጥሯል።የተመድ የኤም 23 አማጺያን የሩዋንዳ ድጋፍ እንዳላቸው መረጃ አለኝ ይላል።የኪጋሊ መንግሥት ግን ክሱን አይቀበልም። ለሁለተኛ ጊዜ ሰላም ለማውረድ በናይሮቢ የተሞከረው  ድርድር አሁን አብቅቷል።ድርድሩ በባለዘጠኝ ነጥብ እቅድ ቢጠናቀቅም፣ውጤቱ አሁንም ግልጽ አይደለም።በግልጽ የተጨበጠ ውጤት ቢኖር የኮንጎ መንግሥትና የአካባቢው ማኅበረሰብ  ውይይት ይቀጥላል መባሉ ነው።ዋናው አደራዳሪው ኬንያታ ደግሞ  በኮንጎ ሰላም ሊሰፍን ጅምር ላይ ነው ብለዋል። ይሁንና በለንደኑ ቻተም ሃውስ የጥናት ተቋም የአፍሪቃ መርሀግብር ሃላፊ አሌክስ ቪነስ ግን ይህ ተግባራዊ መሆኑን ይጠራጠራሉ።
«የኮንጎ የሰላም ስምምነት በጎርጎሮሳዊው 2022 በጣም ይንገጫገጭ የነበረ ሂደት አካል ነበር።  በህዳሩ የሉዋንዳ የሰላም ሂደት ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክና ሩዋንዳን በአንጎላ አግባቢነት ወደ አንድ ስምምነት ላይ ለማድረስ ነበር የታሰበው።ይሁንና የተኩስ አቁም ጥሪው አልተሳካም።  ስለዚህ ወደፊት አለመረጋጋትና መንገጫገጭ እጠብቃለሁ። ስምምነት ላይ እንዲደረስ የኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክና የምሥራቅ አፍሪቃ ማኅበረሰብ ፍላጎት አለ። የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የምሥራቅ አፍሪቃ ማኅበረሰብ አካል እንደሆነ አምናለሁ።ሆኖም ፖለቲካው ግን በጣም መርዛማ ነው። በዚህ የተነሳም እኔ የምሥራቅ ኮንጎ የፀጥታ ሁኔታ በቅርቡ ይሻሻላል ብዬ አልገምትም። » 
የምሥራቅ ኮንጎው ቀውሱ በዚህ ከቀጠለ የሀገሪቱ ምርጫ መዘግየቱ አይቀርም።ኤም 23 የተባለው አማጺ ቡድን ከኮንጎ አማጽያን እጅግ ኃይለኛው ነው።የዚህ ቡድን መነሻ የጎርጎሮሳዊው 1994 የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው።በቱትሲዎች የሚመራው ቡድኑ የታጠቀው በአሁኑ የሩዋንዳ ፕሬዝዳንት ፓውል ካጋሜ ወታደሮች ነው ይባላል ።ዓላማውም በሩዋንዳ በቱትሲዎች ላይ ግድያ ፈጽመው ወደ ምሥራቅ ኮንጎ የሸሹትን የሁቱ ሚሊሽያዎች ማሳደድ ነበር።ፕሬዝዳንት ካጋሜ የኮንጎ አቻቸውን ፌሊክ ችሴኪዲን በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ፍላጎት የላቸውም ሲሉ ይከሱዋቸዋል።ካጋሜ ችሴኬዲ ይህን የሚያደርጉት በምሥራቅ ኮንጎው ቀውስ ሰበብ በጎርጎሮሳዊው 2023 በሀገሪቱ ሊካሄድ የታቀደውን ምርጫ ለማስቀረት አስበው ነው ይሏቸዋል። የችሴኬዲና የካጋሜ የቃላት ምልልስ ታዲያ ሁለቱን ሀገራት ወደ ወታደራዊ ፍጥጫ ይወስዳል የሚል ስጋት አሳድሯል።

DR Kongo Frauen schließen sich Armee an zur Bekämpfung von M23-Rebellen
ምስል Benjamin Kasembe/DW

አፍሪቃውያን በጀርመን

በደቡብ ምዕራብ ጀርመንዋ ከተማ ካርልስሩኽ የሚገኘው «ኤም ኤንድ ዲ አፍሮ ካሪቢያን »የተባለው የምግብና ሸቀጣ ሸቀጦች መደብር በገበያተኞች ተጨናንቋል።መደብሩ በተለይ ፉፉ ያምና ሌሎች የምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት ዜጎች ምግቦች የሚሸጡበት ስፍራ ነው። የሱቁ ባለቤት የ42 ዓመቱ መሐመድ ከአክራ ጋና ነው የመጣው። ሱቁ ከመደበኛ ስራው ጎን ለጎን የሚያካሂደው ንግድ ነው። በቋሚነት የሚሰራው በሱቁ አቅራቢያ በሚገኘው ቅንጡ የሜርሰዲስ መኪናዎች ማምረቻ ኩባንያ ዳይምለር ነው። ሱቁን የምታንቀሳቅሰው ጋናዊቷ ባለቤቱ ፋውስቲና ናት። ከሱቁ ሥራ ጋር አራት ልጆቻቸውን የምትንከባከበውም እርስዋ ናት።ሞሐመድ ለዶቼቬለ እንደተናገረው ከአውሮጳ ጀርመን ለኑሮ የምትመች አገር ናት ይላል። 
«ጀርመን ለኔ እዚህ ለመቆየት በጣም ጥሩ ናት። በተለይ የጤና ዋስትናው በጣም ጥሩ ነው። አንድ ሰው ጀርመን ውስጥ የጤና ዋስትና ካለው የህይወት ዋስትና ይኖረዋል። ጀርመን ውስጥ የዚህ ችግር አይገጥምም።»
መሐመድ ከአውሮጳ ለኑሮ አመቺዋ ጀርመን ናት ይላል።ይህ ሲባል ግን መሐመድ ምንም ችግር አልገጠመውም ማለት አይደለም።ጀርመን የመጣው ከዛሬ 20 ዓመት በፊት የፖለቲካ ስደተኛ ሆኖ ነው። ያኔ አጎቱ ጀርመን ነበሩ።መጀመሪያ ላይ ጀርመን መቆያ ወረቅትና የስራ ፈቃድ ማግኘት ከቢሮክራሲው ጋር ብዙ ፈትኖታል። በሱ አስተሳሰብ ይህ ጀርመን ልታሻሽለው የሚገባ ጉዳይ ነው። ጀርመንና ቋንቋ መማርም ሌላው በጣም ከባዱ ነገር ነበር። እሱ ጀርመን በመጣበት ዘመን እንደአሁኑ የጀርመንኛ ቋንቋ ትምሕርት ለስደተኞች በነፃ አይሰጥም ነበር። ሌላው የሚያነሳው ጉዳይ ጀርመኖች ስለ አፍሪቃውያን ያላቸውን አስስተሳሰብ ነው።አብዛኛዎቹ  ጀርመኖች እዚህ ሀገር ያሉ ጥቁሮችን እንደ ስደተኛና አደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪ ማየታቸው ያሳዝነዋል። 84 ሚሊዮን ህዝብ እንዳላት በሚነገረው በጀርመን ያሉት አፍሪቃውያን ስደተኞች ብዙም አይደሉም። በ2021 ይፋ በሆነ አሀዝ መሠረት ከሰሀራ በረሀ በታች ከሚገኙ ሀገራት ጀርመን የመጡ ቁጥራቸው የተመዘገበ አፍሪቃውያን ቁጥር 450 ሺህ ነው።ይህ አሀዝ ጀርመናዊ ዜግነት ያገኙትን አያካትትም።ሞሐመድ ከመጣበት ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ከሰሀራ በታች ከሚገኙ የአፍሪቃ አገራት የመጡት ቁጥር 164 ሺህ ነበር።ሞሐመድ ከካርልስሩ መሀል ከተማ ወጣ ባለ መንደር በሚኖርበት ጊዜ ፖሊስ በተለያዩ ጊዜያት እያስቆመው የተለያዩ ጥያቄዎችን ያቀርብለት እንደነበርና አንዳንዴም በእጁ ባንጠለጠላቸው ፌሽታሎች ውስጥ ለሚገኙ እቃ መክፈል አለመክፈሉን ይጠየቅ እንደነበር ይናገራል። እርሱ እንደሚለው በጣም በሚያሳፍር ሁኔታ በአንድ ወቅት አደንዛዥ እጽ መያዝ አለመያዙን ለማወቅ ልብሱን እንዲያወልቅ የተደረገበት ጊዜም ነበር።
«መንደሮች ውስጥ ስትንቀሳቀስ ፖሊስ ይቆጣጠርሀል።መኪና ከያዝክ ያስቆሙሀል።ከጓደኛዬ ጋር ሆኜ አንድ ሱቅ ገብተን እቃ ገዝተን ስንገዛ ይቆጣጠሩን ጀመር ።ለምን ብዬ ጠየቅኩ።ይመስለኛል ለስልኬ የዶልቼ ጋባና እቃ ነበር የገዛሁት።ገንዘቡን ከየት አመጣህ ብለው ጠየቁኝ።የራሴ ነው ብዬ መለስኩላቸው።ይህን መሰሉ አጠያየቅ በጣም በጣም ያሳዝነኛል። 
በጎርጎሮሳዊው 2018 የተካሄደ አንድ ጥናት ጀርመን ከሚኖሩ አፍሪቃውያን አንድ ሦስተኛው መጥፎ አያያዝ እንደሚገጥማቸውና እንደሚበደሉ ይገልጻል።ይህ በሌሎች የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ከሚፈጸመው ተመሳሳይ ድርጊት በጣም ከፍተናው ነው። ብዙዎች ስራ ወይም ቤት ፍለጋ ላይ አፍሪቃዊ በመሆናቸው እንደሚገለሉ ይናገራሉ ።ይሁንና ሞሐመድ በስራ ቦታው ላይ ይህ ችግር አልገጠመውም። የዳይምለር ሰራተኛ በመሆኑም በመኪና አከራዮች ዘንድ አስተማማኝ ደንበኛ ተደርጎ ነው የሚወሰደው። ከደቡብ አፍሪቃ የመጣችው ዴሊስያ ሆፍማን ከነመሐመድ ሱቅ ከመንገድ ባሻገር ነው የምትኖረው።ኔልሰን ማንዴላ የደቡብ አፍሪቃ መሪ ሆነው ከተመረጡ ከሁለት ዓመት በኋላ ነበር ደቡብ አፍሪቃን ሊጎበኝ ከመጣ ጀርመናዊ ጋር ተዋውቃ ትዳር የመሰረተችው።ያኔ በሀገርዋ በደቡብ አፍሪቃ ከውጭ ዜጋ ጋር ለሚታይ  ጥሩ ጊዜ አልነበረም።በዚህ ከተጋቡ በኋላ ጀርመን መጡ ።እንደ እድል ሆኖ በደቡብ አፍሪቃዋ በሽቴልንቦሽ ከተማ በትምሕርት ቤት ጀርመንኛ የተማረችው የዩኒቨርስቲ ምሩቅዋ ሆፍማን ጀርመን ስትመጣ ወዲያውኑ ነበር ስራ ያገኘችው። በአንድ የጡረታ ድርጅት ውስጥ የደንበኞች አገልግሎት ክፍል ውስጥ ነበር ስራ የምትሰራው።ሆፍማን ከድርጅቱ 800 ሠራተኖች ብቸኛዋና የመጀመሪያዋ ጥቁር ነበረች።መጀመሪያ ላይ ጥሩ አቀባበል እንደገጠማት ይሰማት ነበር።ሆኖም ይህ የሆነው በምክንያት ነበር ትላለች።
«በብዙ ቦታዎች ተቀባይነት እንዳገኘሁ ነበር የሚሰማኝ።ከዓመታት በኋላ ግን ሰዎች የሚያቀርቡኝ ቋንቋቸውን ስለምናገር መሆኑን ተረዳሁ።ሰዎች በተለየ መንገድ ነበር የሚመለከቱኝ ።ሆኖም ከኅብረተሰቡ የራቅኩ ያህል ወይም እንደተገለልኩ አይሰማኝም ነበር።»በአሁኑ ጊዜ ከካርልስሩኽ ነዋሪ 306 ሺሁ ከውጭ ዜጎች የተወለደ ነው።ለሆፍማን ጀርመን የመኖርዋ ትልቁ ጠቀሜታ የመንቀሳቀስ ነጻነትዋ ነው።«እንደ ሴት፣ ከቤት መውጣት እንደምትወድ ሴት በጎዳናዎች መንቀሳቀስ መሄድን አደንቃለሁ። አምሽቼ በብስኪሌት ብጓዝም ደኅንነቴ የተጠበቀ መሆኑን አውቃለሁ።ቢስክሌት መንዳትን እንደ ቅንጦት ነው የማየው።በጣም እወደዋለሁ።»ጀርመን ጥምር ዜግነት ስለማትፈቅድ ሞሐመድም ሆነ ሆፍማን የጀርመን ዜግነት ለማግኘት ብለው የተወለዱበትን ሀገር ፓስፖርት አላስረከቡም።ሆፍማን የጀርመን ፓስፖርት አለመያዟ የተለያዩ ጥቅሞችን እንደሚያስቀር ታውቃለች። 
«ፓስፖርቱ ወረቀት እንደሆነ አውቃለሁ።ሆኖም ይህ ብጣሽ ወረቀት ከማንነት ጋር የተያያዘ ነው።፤ለዚህም ነው እሺ አሁን የጀርመን ዜጋ ነኝ ብዬ የምናገርበትን ጊዜ የምናፍቀው።ምክንያቱም ጀርመን ቤቴ ሆኖ ነው የሚሰማኝ።በተለይ የመምረጥ መብት እንዲኖረኝም እፈልጋለሁ።»  በመሐመድ ሱቅ አካባቢ በሚገኝ ስፍራ ጸጉራቸውን ለመስተካከል የሚጠባበቁ ጥቂት ሰዎች ይታያሉ።ከመካከላቸው አንዱ የ24 ዓመቱ ዋሀም ነው። ጀርመን ከመጣ ሰባት ዓመት ሆኖታል።ጀርመን ከመምጣቱ በፊት ኢጣልኢ ነበር።ከኢጣልያ ይልቅ ጀርመን የተሻሉ እድሎች እንዳሉ ይናገራል።ጀርመንና ቋንቋም መማር ችሏል።እርሱና መሰል ኤርትራውያን በጀርመን ጥገኝነት ለማግኘት የሚያስገቡት ማመልከቻ ሂደት ጠመዝማዛ መሆኑ አይገባውም።ሂደቱ እስከሚጠናቀቅ መስራት አለመቻላቸው ክህሎታቸውን ጥቅም ላይ አለማዋል ነው ብሎ ነው የሚያስበው።በጀርመን ብዙ የስራ እድሎች ቢኖሩም ትክክለኛው ሰነድ የሌለው ሰው ግን መስራት አለመቻሉ ያሳዝነዋል።ቤተሰብን መልሶ የማገናኘት ሂደትም እንዲሁ ከሚያሳስቡት ጉዳoce ውስጥ ነው።እርሱ እንደሚለው በርካታ ኤርትራውያን ባለቤቶቻቸውና ልጆቻቸው እንዲመጡ በመጠበቅ ብዙ ጊዜያት እየጠበቁ ነው።በጀርመን ሕግ ስደተኞች የኑሮ አጋሮቻቸውንና ልጆቻቸውን ጀርመን ማምጣት ይፈቀድላቸዋል። ይሁንና ኤርትራውያን ከሀገራቸው አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት ስለማይችሉ ብዙውን ጊዜ ይህ አይሳካላቸውም።ዋሃም  እንደሚለው ካለቤተሰብ ማለትም ያለ ሚስትና ልጆች ሕይወት በጣም ከባድ ነው።

Afrikaner in Deutschland Mo aus Ghana
ምስል Kate Hairsine/DW
Kongo I Kanyaruchinya Lager für Binnenvertriebene
ምስል Guerchom Ndebo/AFP

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ