1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኮሮና ተህዋሲ የሚያዙት ሕፃናትና ወጣቶች ቁጥር ጨምሯል

ዓርብ፣ መጋቢት 24 2013

እስካሁን ድረስ የኮሮና በሽታ በሕጻናት እና ወጣቶች ላይ አስከፊ ችግር እንደማያደርስ ነው ባለሙያዎች የሚናገሩት። ከዚህ ድምዳሜ የደረሱትም በዚህ ዕድሜ ክልል ያሉ ልጆች ከተያዙ ህመሙ መለስተኛ አንዳንዴም ጨርሶ ምልክት እንኳን ስለማያሳዩ ነው።

https://p.dw.com/p/3rWJE
Äthiopien
ምስል DW/S. Wegayehu

በኮሮና ተህዋሲ የሚያዙት ሕፃናትና ወጣቶች ቁጥር ጨምሯል

ባዮንቴክ የተባለው የኮሮና ክትባት አምራች በዚህ ሳምንት ይፋ እንዳደረገው ክትባቱ በወጣቶች ላይም ተስፋ ሰጪ ሆኖ አኝቶታል። እናም ክትባቱ 12 ዓመት ከሆናቸው አዳጊ ልጆች አንስቶ ሊሰጥ ይችላል ባይ ነው። ከዚህ ቀደም የተደረጉት ሙከራዎች የኮሮና ክትባት ከ 16 ዓመት በላይ ላሉ ወጣቶች መሰጠት እንደሚችል ነበር ያረጋገጡት። የባዮንቴክ እና ፋይዘር ድርጅቶች ዕድሜያቸው ከስድስት ወር እስከ 11 ዓመት ያሉ ሕጻናት ልጆች ላይም ክትባቱ አስተማማኝ መሆኑን እየፈተሹ ነው። ሌሎች የመድኃኒት አምራቾችም እንዲሁ በምርምር ላይ ናቸው። እስካሁን ያለው የመድኃኒት አምራቾቹ ውጤት ተስፋ ሲጪ ቢሆንም ሕጻናት እና ወጣቶች መከተብ እስኪችሉ ግን ከወራት እስከ ዓመት ሊፈጅ እንደሚችል ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት። በቂ ክትባት ባለመኖሩ በአደጉት እና ክትባቱን የመግዛት አቅም ባላቸው አገሮች ሳይቀር እስካሁን ቅድሚያ እያገኙ ያሉት በዕድሜ የገፉ፣ ተጓዳኝ በሽታ ያላቸው ወይም የጤና ባለሙያ የመሳሰሉት ከብዙ ሰዎች ጋር የሚገናኙ ሰዎች ብቻ ናቸው። 
ኢትዮጵያ ውስጥ ሕጻናት እና ወጣቶች ትክባት ሊከተቡ ይቅርና በተህዋሲው መያዛቸው በምርመራ የሚረጋገጥላቸው እጅግ ውስን ናቸው። ነፃነት ኢትዮጵያ ውስጥ የምትኖር ወጣት እናት ናት። ከጥቂት ቀናት በፊት ተመርምራ በኮሮና መያዟን አውቃለች። « ያለው ህመም በጣም ከባድ ነው» የምትለው ነፃነት የሰባት ወር ልጇን አላስመረመረቻትም። ህፃንዋም እስካሁን ምንም አይነት የህመም ምልዕክቶች አታሳይም።
ኢትዮጵያ ውስጥ የምትኖረው  ወጣቷ ሀኪም ዶክተር እምነት፤ 25 ዓመቷ ነው። እስካሁን ሁለት ጊዜ በኮሮና ተይዛ ታውቃለች። « የመጀመሪያው ልክ ኮሮና ኢትዮጵያ እንደገባ ከወር በኋላ ነበር የያዘኝ። ያኔ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ውስጥ እሰራ ነበር። እና ስራዬ ንኪኪ ያላቸው ሰዎች ናሙና እንዲሰጡ ማመቻቸት ነበር። »  ለሁለተኛ ጊዜ የያዛት ደግሞ ከአራት ወር በፊት ነው። ዶክተር እምነት ኮቪድ ወጣት እና ህፃናት ላይ አይበረታም በሚለው ብዙም አትስማማም። ለዚህም በምሳሌነት የምታነሳው አባቷን ነው።« የሆነ ጊዜ አባቴን ይዞት ነበር። እና አባቴን ከእኔ በላይ ቀሎት ነበር።»
የ 27 ዓመቱ እዮሲያስ ኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮና ክትባት ካገኙ ወጣቶች አንዱ ነው።  ይህንንም ዕድል ያገኘው ሀኪም በመሆኑ ነው። አዲስ አበባ በሚገኘው የሚሊኒየም የኮቪድ ህክምና ማዕከል ውስጥ ይሠራል። « እኛ ጋር የሚሰሩ ሁሉም ማለት ይቻላል ቢያንስ የመጀመሪያውን ዙር ክትባት ወስደዋል።» ይህም ክትባት ዳግም በኮቪድ ተህዋሲ እንዳይያዝ ወጣቱ ሀኪም «ይከላከልልኛል» የሚል ተስፋ አለው። ከዚህ ቀደም አንድ ጊዜ በኮቪድ መያዙ በምርመራ የተረጋገጠ ሲሆን ለሁለተኛ ጊዜ ተመሳሳይ ምልዕክቶች ያለው ህመም ተሰምቶት ነበር። የናሙናው ውጤት ግን « ኔጌቲቭ» ወይም አለመያዙን የሚያመላክት ነበር። ዶክተር እዮሲያስ ከአንድ ዓመት በላይ በሠራበት የሚሊኒየም የኮቪድ ህክምና ማዕከል ውስጥ « ህፃናት ባይባልም ወጣቶች ከ 25-35 እድሜ ያሉ በጣም ታመው መጥተው፣ ህይወታቸውም ያለፉ አጋጥሞናል። » ይላል። ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥም በወጣት ኢትዮጵያውያን ላይ በሽታው ሲጠነክር እየታዘቡ እንደሆነ ዶክተር እዮሲያስ ይናገራል። ወጣቶች ምልዕክት ባለማሳየታቸው ለጎዜው ወደ ጎን ይባሉ እንጂ በኮቪድም ሆነ በሳምባ ምች በሽታ በብዛት እንደሚያዙም ነው ዶክተር እዮሲያስ የሚያስረዳው። « ወጣቶች በባክቴሪያ የሚተላለፈው የሳምባ ምች በሽታ ይይዛቸዋል። ይህም ከአስራዎቹ እድሜ አንስቶ እስከ 25 ድረስ የተለመደ ነው።» «ዕድሜ ሳይሆን ወሳኙ በሽታን የመቋቋም አቅማችን ነው» የምትለውም ዶክተር እምነት በምትሠራበት የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ይህን ያህል የጠናባቸውም ይሁን ለኮቪድ ምርመራ የሰጡ ሕጻናት እና ወጣቶች አልገጠሟትም። « ወጣት እና ህፃን ናሙና ሊሰጥ የሚመጣው ንኪኪ ሲኖረው ነው። »ትላለች።
ዶክተር እዮሲያስ የወሰደው ክትባት አዲስ እንደመሆኑ መደናገጥ ፈጥሮበታል። ይሁንና «ላለመውሰድ የሚያደርስ ጥርጣሬ አልነበረኝም» ይላል። ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ በማኅበረሱ ዘንድ ለክትባቱ ያለው ግንዛቤ ምን ይመስላል? ዶክተር እዮሲያስ «መጥፎ ዜናው ከጥሩ ዜናዎ ጎልቶ ስለሚወጣ የሰዎችን አመለካከት ቀይሯል» ይላል። የራሱ ወላጆች ሳይቀሩ ልጃቸው ባይከተብ ይመርጡ ነበር። የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ አንስቶ ስለ ተህዋሲው «ጠቃሚ» የሚላቸውን መረጃዎች በጽሑፍ እና በቪዲዮ ለኢትዮጵያውያን የሚያጋራው ዶክተር ኪሩቤልም  ቢሆን ካለመከተብ ይልቅ ሕጻናት እና ወጣቶችን ጨምሮ መከተቡ መፍትሄ እንደሆነ ነው የሚናገረው። የ 28 ዓመቱ ወጣት ሀኪም በአሁኑ ሰዓት ለቀጣይ ትምህርት በሄደባት ስፔን ሀገር ይኖራል። ክትባቱ « 100% አስተማማኝ ነው ለማለት ባልችልም ካለን አማራጭ አንፃር ከጉዳቱ ጥቅሙ ይበልጥብኛል።» ይላል።
የኮሮና ስርጭትን ለመግታት በሚል ፈረንሳይ ትምህርት ቤቶችን ለሦስት ሳምንታት መልሳ እንደምትዘጋ ሰሞኑን ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮ አስታውቀዋል።  እንደ የጀርመኑ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ተቋም ሮበርት ኮኽ ከሆነ ዕድሜያቸው ከ 14 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ከመቼውም የበለጠ በአዲሱ የኮሮና ዝርያ መያዛቸው ተረጋግጧል። ቁጥሩም እንደውም በእጥፍ የጨመረባቸው አካባቢዎች አሉ። ለቁጥሩ መጨመር አንዱ ምክንያት ሕጻናት እና ወጣቶች ከቀድሞው የበለጠ መመርመራቸው ሲሆን ሌላው ደግሞ ተህዋሲውን በማስተላለፍ ረገድ ዋና ሚና ይጫወታሉ። እንደ ዶክተር ኪሩቤል ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች በበሽታው መያዛቸው መጨመሩ ከትምህርት ቤት መከፈት ይልቅ ሌላ ምክንያት አለ።« እኔ የማያይዘው ረዥም ጊዜ ከሰው ሰው ሲተላለፍ የተፈጠረ አዲስ ዝሪያ ሊኖር ይችላል የሚል ግምት ነው ያለኝ።»ይላል።
እስካሁን ባለው ሁኔታ ወጣቶች እና ሕጻናት የህመም ምልክት ባያሳዩም እንኳን በተሐዋሲው መያዛቸው በራሱ ወደፊት ጉዳት ስለማስከተሉ  በቂ መረጃ ባይኖርም ባለሙያዎች ከወራት በኋላም የህመም ምልዕክቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ። 

Äthiopien Corona-Pandemie Dire Dawa Transport
ርቀትን መጠነቅ ትልቁ ፈተና ነውምስል DW/M. Teklu
Äthiopien l Start der COVID-19-Impfung
ኢትዮጵያ ከሶስት ሳምንት በፊት ክትባት መስጠት ጀምራለችምስል Solomon Muchie/DW

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሠ