1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦነግ አመራሮች እስራት የሂዩማን ራይትስ ዎች ጥሪ

ሰኞ፣ ሐምሌ 17 2015

“ፖሊስ በኢትዮጵያ ፍትህን በጣሰ መልኩ የኦነግ አመራሮቹን ለተራዘመና ጭካኔ ለተሞላ ክስ አልባ እስር ዳርጎአቸዋል”

https://p.dw.com/p/4UJjx
Äthiopien | Feierlichkeiten zum 50. Jahrestag der Äthiopischen Oromo Liveration Front
ምስል Seyoum Getu/DW

"የኦነግ አመራር አባላት የነበሩት ይፈቱ"

ላለፉት ሶስት ዓመታት ገደማ በእስር ላይ የቆዩ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮች በአስቸኳይ ከእስር እንዲፈቱ ሲል ዓለማቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ሒዩማን ራይትስ ዎች ጠየቀ፡፡
ሰብዓዊ ድርጅቱ ሰባት የኦነግ አመራሮች የታሰሩትና አሁንም በእስር ላይ ያሉት በፖለቲካ ሚናቸው ብቻ ሲሆን ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስት የፍትህ ስርዓቱን እንዲፈትሽ አንዱ ማሳያ ነው ብሏልም፡፡
የሂዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራር የነበሩት ሰባት ግለሰቦች የታሰሩት በኦሮሚያ ፖሊስ መሆኑን በመጥቀስ ዘገባውን ይጀምራል፡፡ ሪፖርቱ አብዲ ረጋሳ፣ ዳዊት አብደታ፣ ለሚ ቤኛ፣ ሚካኤል ቦረን፣ ኬኔሳ አያና እና ገዳ ኦልጂራ የተባሉ ስድስት የኦነግ አመራሮች በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት በ2012 ዓ.ም. ሲሆን ገዳ ገቢሳ ደግሞ በ2013 ዓ.ም. መታሰራቸውን ያመለክታል፡፡ የኦነግ አመራሮቹ በእስር ላይ ያሉት በተደጋጋሚ እንዲለቀቁ የተሰጡ የዳኝነት ውሳኔዎች በመጣሱ ነው ያለው ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ ባለስልጣናትም "ለዚህ የሚያቀርቡት ህጋዊ መሰረት ያለው አመክንዎ የላቸውም" ብሏል፡፡
“ፖሊስ በኢትዮጵያ ፍትህን በጣሰ መልኩ የኦነግ አመራሮቹን ለተራዘመና ጭካኔ ለተሞላ ክስ አልባ እስር ዳርጎአቸዋል” ሲሉ ሂደቱን የወቀሱት የሂዩማን ራይትስ ዎች አፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ላይቲታ ባደር፤ “የኢትዮጵያ መንግስት ባስቸኳይ ከእስር ሊለቃቸውና የተሳሳተ እስሩን በማብቃት ፖለቲካዊ ጭቆና” ያሉት ተግባር ሊያበቃ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዎች ከአገር ውስጥ እና ዓለማቀፍ የመብት ተሟጋቾች ጋር በፖለቲካ ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ እስራቶች ለዓመታት በኢትዮጵያ ሲከናወኑ መቆየታቸው መመዝገቡን አስታውሶ፤ በ2010 ዓ.ም. የወንጀል ፍትህን ለማሻሻል የተገባው ቃልም እምብዛም የታዩትን ክፍተቶች ያልዘጋ ሆኗል ብሏል፡፡
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ቃል አቀባይ አቶ ለሚ ገመቹ ሪፖርቱ የዘገየ ቢሆንም ያልተጋነነና እውነታውን ያስቀመጠ ብለውታል፡፡
የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቱ ለሪፖርቱ ማስረጃ ይሁኑት ዘንድ ዘጠኝ የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች፣ የህግ ጠበቆች እና የፓርቲው አመራሮችን በስልክ አነጋግሮ የፍርድ ቤትና ህክምና ማስረጃዎቻቸውን መዳሰሱንም ጠቁሟል፡፡ ሪፖርቱ የኦሮሚያ ፖሊስን የታሳሪዎች መብት በሚጻረር መልኩ ለወራትና ለሳምንታት ጠበቆቻቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን እንዳያገኙ አድርጓል በሚልም ከሷል፡፡ ለአብነትም ታሳሪዎቹ ለ8 ወራት ገደማ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ በመታሰራቸው ከቤተሰቦቻቸው እይታም የተሰወሩበት ጊዜ መኖሩን አንስቷል፡፡
የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ዘርዘር ባለው መግለጫው የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አብዲ ረጋሳ በየካቲት ወር 2012 ዓ.ም. በቡራዩ የመንግስት ጸጥታ አመራርን በመግደል ተጠርጥረው በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች ከተወሰዱ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ስድስት ኪሎ አከባቢ ታስረው ቆይተው ወደ ቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ መመለሳቸውን ገልጿል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አብዲ ለ8 ወራት ከሰው እይታ ተሰውረዋል ከተባሉበት የ8 ወራት የገላን ፖሊስ ቆይታን ጨምሮ ስምንት ቦታዎች ተዘዋውረው መታሰራቸውን አብራርቷል፡፡
ለሚ ቤኛ፣ ዳዊት አብደታ፣ ኬኔሳ አያና እና ሚካኤል ቦረን ደግሞ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በፖሊስ ታስረው አዋሽ መልካሳን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረው መታሰራቸውን ነው ሪፖርቱ ደረሱኝ ያለውን መረጃዎች የተነተነው፡፡ እስረኞቹ በተለይም አቶ ኬኔሳ አያና እና ገዳ ገቢሳ አሁን ላይ የሚገኙበት የጤናቸው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑንም ይህ የሒዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ጠቃቅሷል፡፡ 
የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ለሚ ገመቹ፤ ይህን የመብቶች ተሟጋች ድርጅቶችን ውትወታ አስፈጻሚ አካላት ከሰሙ ፍትህን ያገኛሉ ብለው እንደሚምኑ ጠቁመዋል፡፡ “ከዚህ በፊትም እንደ አሚነስቲ ኢንተርናሽናል እና ከአገር ውስጥም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ተመሳሳይ ይዘት ያለውን ዘገባ አውጥተዋል፡፡ አሁንም ሰሚ ካለ ፍትህ ያገኛሉ ብለን ተስፋ እናረጋለን፡፡”በዚሁ ዓመት እንኳ በሚያዚያ ወር ውስጥ ኦሮሚያ ፖሊስ ፖለቲከኞቹን ከታሰሩበት ቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ ሰውረው ከሁለት ሳምንታት በኋላ ቤተሰቦች ዱከም ከተማ እንዳገኙዋቸው መረዳቱንም አንስቷል፡፡ ይህም የሆነው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የታሳሪዎቹን ይዞታ ለመጎብኘት ማቀዱን ተከትሎ ነው ብሏል ሪፖርቱ፡፡ ለድርጊቱ ግን ከፖሊስ የተሰጠ ምንም አይነት ማብራሪያ አለመኖሩንም አክሏል፡፡ 
ድርጊቱ የዓለማቀፉ ሰብዓዊ መብቶች ህግን የሚጻረር ነው ያለው ሪፖርቱ እስረኞቹ እንዲለቀቁ ለክልሉ እና ለፌደራል መንግስት ጥሪ አቅርቧል፡፡ ከሳሹ የክልሉ መንግስት በሚካኤል ቦረን፣ ኬኔሳ አያና እና ገዳ ገቢሳ ላይ ማስረጃ በማጣቱ ክሱ መቋረጡን ገልጾም በገዳ ኦልጂራ ላይ ደግሞ እስካሁን የተመሰረተ ክስ አለመኖሩን ጠቅሷል፡፡ ሌሎች ተከሳሾችም በፍርድ ቤት ቢለቀቁም ፖሊስ መልሶ እያሰራቸው ዛሬ ላይ ደርሰዋል ይላል ሪፖርቱ በዝርዝር መግለጫው፡፡ 
የዛሬ ዓመት ገደማ ክልላዊው ፍርድ ቤት አራት ተከሳሾችን የአካል ነጻ ማውጣት ብያኔ ቢያስተላልፍም እስካሁን እስር ላይ መሆናቸው ተጠቁሟልም፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ ቤተሰብ፣ የፖለቲካ ፓርቲውን እና የህግ ጠበቆቻቸውን በማሰልቸት ተስፋም አስቆርጧቸዋል ይላል ሪፖርቱ፡፡ 
ያለ ክስ እና ፍርድ ቤት መቅረብ የተራዘመው እስር የአገሪቱን፣ የአፍሪካ እና ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ህግጋትን የጣሰም ነው ብሏል ይህ ሪፖርት፡፡ ከዚህ ጋር አያይዞም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከአንድ ዓመት በፊት ፖለቲከኞቹ ያለህግ አግባብ ታስረው እንደሚገኙ ሪፖርት ማውጣቱን አስታውሷል፡፡ የኦሮሚያ ባለስልጣናት እስረኞቹን እንዲለቁ፤ የፍትህ ሚኒስቴርም በአገሪቱ የህግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ በዚህ ሪፖርት ወትውቷል፡፡ 
ሂዩማን ራይትስ ዎች የኦነግ አመራሮችን አስመልክቶ ያወጣው በዚህ መግለጫ ላይ ከኦሮሚያ ክልል መንግስት አስተያየት ለማካተት ለክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ደጋግመን ብንደውልም፤ ስልካቸው ባለመነሳቱ አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለመም፡፡ በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ አቃቤ ህግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ለሆኑት ለአቶ ፍቃዱ ፀጋም ጥያቄውን አቅርበን ምላሻቸውን ግን ማግኘት አልቻልንም፡፡
ሥዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ

Human Rights Watch Logo Flash-Galerie
ምስል Human Rights Watch