1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮምያ ክልል ለዓመታት ለዘለቀው ግጭትና ግድያ ኃላፊነቱን ማን ይወሰድ?

ዓርብ፣ መስከረም 11 2016

በኦሮሚያ ክልል እልባት የራቀው ግጭት አሁንም ለንጹሃን ሞትና አለመረጋጋት መንስኤ ሆኖ እንደቀጠለ መሆኑ ተመለከተ፡፡ በክልሉ ከፍርድ ውጪ ግድያዎችን ጨምሮ ንጹሃን ላይ የሚደርሱ የእለት ተእለት ጥቃቶች በአሳሳቢነት መቀጠሉም ነው የሚነገረው፡፡ ለችግሩ መንግስት ታጣቂዎችን ሲከስ፤ ተቃዋሚ ድርጅቶች በፊናቸው መንግስትን ተወቃሽ ያደርጋሉ፡፡

https://p.dw.com/p/4WhUW
Äthiopien | Oromiya Region
ምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

በተለያዩ አቅጣጫዎች ስጋት ጥቃቶች መቀጠላቸዉ ነዋሪዎች ላይ ስጋት አሳድሯል

በኦሮሚያ ክልል እልባት የራቀው ግጭት አሁንም ለንጹሃን ሞትና አለመረጋጋት መንስኤ ሆኖ እንደቀጠለ መሆኑ ተመለከተ፡፡ በክልሉ ከፍርድ ውጪ ግድያዎችን ጨምሮ ንጹሃን ላይ የሚደርሱ የእለት ተእለት ጥቃቶች በአሳሳቢነት መቀጠሉም ነው የሚነገረው፡፡

ለችግሩ መወሳሰብ መንግስት ታጣቂዎችን ሲከስ፤ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በፊናቸው መንግስትን ተወቃሽ ያደርጋሉ፡፡ አስተያየታቸውን የሰጡን ተንታኝ ግን ባህሉ ያልተቀየረ የቀነጨረ ያሉት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከችግሮቹ ሁሉ ጀርባ ያለው እውነታ ነው ብለዋል፡፡

ካማሺ ከተማ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል
ካማሺ ከተማ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምስል Negassa Dessalegn/DW

ከአምስት ዓመታት በፊት በምዕራብ ኦሮሚያ እና በደቡባዊ የክልሉ አከባቢዎች ከመነሻውም መረጋጋት ርቆት የተነሳው የኦሮሚያው ግጭት ስብስ እንጂ ስረግብ አይስተዋልም፡፡ በወቅቱ በነዚህ አከባቢዎች ብቻ ተወስኖ የቆየው የክልሉ አለመረጋጋት የክልሉ መዓከላዊ ዞኖችን ጨምሮ በተለያዩ አቅጣጫዎች ስጋት የሚያጭሩ ጥቃቶች መስፋፋታቸውን ነዋሪዎችም በተለያዩ ጊዜያት ይግልጻሉ፡፡የፀጥታ እጦት ችግር እሮሮ በኦሮሚያ

የክልሉ ጸጥታ መታወክ ደግሞ ማህበረሰቡን ለከፋ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ከመዳረጉም  በላይ ግድያዎች እንዲፈጸሙም ምክንያት ስለመሆኑ ይገልጻል፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ፤ ይህ የክልሉን አለመረጋጋት ተከትሎ መንግስት ከህግ ውጪ የሆኑ የተለያዩ ግድያዎችን ይፈጽማል ሲል ከሷል፡፡ ፓርቲው በይፋዊ መግለጫው “መንግስት የሚፈጽማቸውን ግድያዎች በክልሉ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ያሳብባል” ሲልም ወቀሳቀውን ሰንዝሯል፡፡

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ዑርጌሳ ከዚሁ ጋር አያይዘው ለዶቼ ቬለ በሰጡት ቃለምልልስ ቋጠረው ሲጠብቅ እንጂ ሲፈታ ለማይስተዋለው ለኦሮሚያው ግጭት አለመረጋጋት መሰረታዊው ምክኒያት ነው ያሉትን ሲያብራሩ፤ “በኛ አመለካከት ኦነግ ከመንግስት ጋር በአስመራ የገባው ስምምነት በውል አለመከበሩ ለችግሮች መወሳሰብ ዋናው ምክኒያት ነው፡፡ አሁንም ብሆን ግጭቱን ለማስቀረት ቁልፉ ያለው የመንግስት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ጋ ነው፡፡ መንግስት ታጣቂዎችን እጅ ሰጥታችሁ በሰላም ገብታችሁ ታገሉ ከማለት ባሻገር ፖለቲካዊ ፍላጎቱን በጠረጴዛ ዙሪያ አቅርቦ መነጋጋር ይኖርበታል” ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራር አቶ ሙላቱ ገመቹ በፊናቸው መብቴን አስከብራለሁ ባሉት ታጣቂ ቡድኖች እና መንግስት መካከል የሚደረግ ሰላማዊ ያልሆነ ፍልሚያ ህብረተሰቡን ከፈተነው ግጭት ጀርባ ያለው እውነታ ነው ባይ ናቸው፡፡ “ታጣቂዎቹ ለመብታችን ነው የምንታገለው ሲሉ መንግስት አገርን ሰላም የሚነሱ ሽብርተኞች ሲል ነው የሚጠራቸው፡፡ ነገሩ በሁለቱም ወገኖች በኩል ፍላጎቱ ብታከል በንግግር የሚያልቅ ነበር፡፡”ምዕራብ ወለጋ፤ በፀጥታ ችግር የተዘጋዉ መንገድ ዳግም ሥራ ጀመረ

አሁን አሁን በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎች መበራከታቸውን ነዋሪዎች ያነሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም መሰል ጥቆማዎች እንደሚደርሱት የመለክታል፡፡ ዶቼ ቬለ በዚሁ ላይ ያነጋገራቸው አንድ የኮሚሽኑ ባለስልጣንም ከፍርድ ውጪ የሆኑ ግድያዎች በኦሮሚያ መበራከታቸውን ጠቁመው፤ በዚሁ ላይ የሚያጠነጥንና ምናልባትም በሚቀጥለው ሳምንት ይፋ የሚሆን ሪፖርት በኮሚሽኑ እየተጠናቀረ ነው ብለውናል፡፡

የኦሮምያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ
የኦሮምያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ምስል Seyoum Getu/DW

ዶይቼ ቬለ በክልሉ ይፈጸማሉ ስለተባሉ ግድያዎች እና ስለ እልባት አልባው ግጭት መፍትሄ አስተያየትና ማብራሪያ ለመጠየቅ ለኦሮሚያ ክልል እና ለፌዴራል መንግስት የኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣናት ብደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡ ይሁንና የመንግስት ባለስልጣናት ከዚህ በፊት በሰጠጡ መግለጫ በኦሮሚያው ግጭት፤ በተለይም በአዋሳን አከባቢዎች ለችግሩ መወሳሰብ “ጽንፈኛ” የሚሏቸው ከኦሮሞ እና አማራ ማህበረሰቦች ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላትን ይከሳል፡፡

ፖለቲከኛ ሙላቱ ገመቹ መንስኤው ምንም ይሁን ምን የችግሩ ሁለ ገፈት ቀማሽ ንጹህ ማህበረሰብ ሆኖ እየተስተዋለ ነው ባይ ናቸው፡፡ “ዋናው የችግሩ ተጠቂ ህዝብ ሆኗል፡፡ ለዚህም ነው ከዚህም ከዚያም ችግሮቻችሁን ተቀምጣችሁ ፍቱ እያልን አቤት የምንለው፡ ”በኦሮሚያ ክልል ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ድጋፍ ተጠየቀ

ሌላኛውን ፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳን፤ በኦሮሚያ ውስጥ የሚፈጸሙት የንጹሃን ግድያ በማን የሚከወኑ ናቸው፤ ተጠያቂነቱንስ ማን ሊወስድ ይገባል ብለን ጠየቅናቸው፡፡ “ሃላፊነቱማ የሚወድቀው አገሪቱን የመምራት ኃላፊነት በወሰደው አካል በመንግስት እጅ ላይ ነው፡፡ ግን መንግስት ችግሩን በዘላቂነት በመፍታት ይህን ኃላፊነቱን ሲወጣ አይታይም፡፡ እኛ በምናገኛቸው መረጃዎች በተለያዩ አከባቢዎች በሚፈጸሙ ግድያዎች የመንግስት እጅ አለ፡፡ መንግስት ግጭቶቹን በዘላቂነት መፍታት እየቻለ ለምን ቀጠሉ የሚለው ጥያቄን ያጭራል” ሲሉ መልሰዋል፡፡

የአገሪቱን ፖለቲካ በቅርበት ሚከታተሉት የህግ ባለሙያው አቶ ቸርነት ሆርዶፋ ግን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግር አንድ ወይም ሁለት ተብሎ የሚጠቀስ ቀላል ችግር አለመሆኑ የችግሩንም እልባት ሆነ ሊጠየቅ የሚገባውን አካል ቀላል አያደርግም ባይ ናቸው፡፡ “የቀነጨረው የፖለቲካ ሂደት ብሎም የአገር ጥቅምና ዘጋውን የሚጎዳውን ከመሰረቱ አለመረዳት ሰላም ያራቀው ግጭት ውስጥ አቆይቶናል፡፡ ከችግሩን የምንወጣው ደህነትን በመቀነስ የዜጎችን ንቃተ ህሊና በማዳበር ጥቅመኛ ፖለቲከኞችን ከህዝብ በመለየት ይሆናል” ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡

በኦሮሚያ አምስት ዓመታትን የደፈነው ግጭት ባለፈው ዓመት በታንዛንያው የሰላም ድርድር ለመፍታት የተደረገው ጥረት ተጨባጭ መፍትሄ አለማምጣቱ የሚታወስ ነው፡፡

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ