1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ ግጭት በተባባሰባቸው አከባቢዎች የተፈተነው የጤና አገልግሎት

ማክሰኞ፣ ጥር 9 2015

በኦሮሚያ ክልል ግጭት ተባብሶ በቀጠለባቸው አከባቢዎች ህብረተሰቡ የጤና አገልግሎት ከናካቴው ማግኘት አዳጋች እንደሆነባቸው ተገልጿል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ከጤና አገልግሎት በተጨማሪ፤ ወደ ሌላ አከባቢ እንኳ ተንቀሳቅሰው አገለግሎቱን ማግኘት ፈተናው ብርቱ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/4MIw3
Äthiopien  World Disability day celebration in Dire Dawa | Dr. Liya Tadesse,
ምስል Mesay Tekilu/DW

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ የአገምሳ ከተማ የጤና ተቋማትላይ ችግር ከደረሰ ዓመት አስቆጠረ።

በኦሮሚያ ክልል ግጭት ተባብሶ በቀጠለባቸው አከባቢዎች ህብረተሰቡ የጤና አገልግሎት ከናካቴው ማግኘት አዳጋች እንደሆነባቸው ተገልጿል፡፡ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ በግጭት አከባቢዎቹ የሚኖሩ ነዋሪዎች እንዳሉት ምንም አይነት ህክምና እና መድሃኒት ማግኘትም የማይታሰብ እየሆነ መጥቷል ብለዋል፡፡ የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ በግጭት የተጎዱ የክልሉ አከባቢዎች ትኩረት ውስጥ ገብቶ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እቅድ ነድፌ እየተንቀሳቀስኩ ነው ይላል፡፡ “ሱቅ የለም፣ መድሃኒት አይገኝም፣ ሃኪም በአከባቢው የለም፤ ወላድ እናቶች በየቀኑም እሞቱ ነው፡፡”

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ የአገምሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑትና መሰረታዊ የጤና አገለግልት ጋር ሆድና ጀርባ ከሆኑ መንፈቀ ኣመት መቆጠሩን ጠቅሰው የተናገሩት ነው፡፡ እኚህ ነዋሪ እንደሚሉት በአከባቢው ካጡት የጤና አገልግሎት በተጨማሪ፤ ወደ ሌላ አከባቢ እንኳ ተንቀሳቅሰው አገለግሎቱን ማግኘት ፈተናው ብርቱ መሆኑን ጭምር አንስተው አብራርተዋል፡፡ “በአሙሩ ወረዳ ከአገምሳ እና የወረዳው ከተማ ውጭ የትም መንቀሳቀስ ከባድ ስለሆነ ህመም የበረታበትን ሰው እንኳ የትም መውሰድ ከባድ ሆኗል” ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡

Äthiopien | Wahlen | Oromia
ምዕራብ ሸዋ፤ ኦሮምያ

በክልሉ የሰሜን ሸዋ ዞን ያያ ጉሌሌ ወረዳ ነዋሪነታቸውን ያደረጉት ቶሎሳ ፉፋ የተባሉት ሌላው ነዋሪ በሰጡን አስተያየት፤ ለመዲናዋ አዲስ አበባ እጅግ በቀረበ በዚህ ስፍራ ነዋሪዎች የጤና አገልግሎትን ጨምሮ የትኛውም መሰረታዊ አገልግሎቶች ከተቋረጡ ሁለት ዓመታት መቆጠራቸውን ያነሳሉ፡፡ “በሙገር ሸለቆ በመሸጉ የኦሮሞ ታጣቂዎች እና መንግስት መካከል በሚደረገው ፊልሚያ የጤና አገልግሎት ማግኘት ካቆምን ሁለት ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ በዚህን ወቅት ታጣቂዎች ከተቆጣጠሩት ቀበሌያት ወጥቶ ወደ ከተማ በመሄድ የጤና አገልግሎት የሚያገኝ የለም፡፡ ከመንግስት ሰራተኛም ወደነዚያ አከባቢዎች በመሄድ አገልግሎቱን ለመስጠት ፈቃደኛ የሚሆን አካል የለም” በማለት የችግሩን ስፋት አንስተዋል፡፡

Äthiopien | Wahlen | Oromia
ምዕራብ ሸዋ፤ ኦሮምያ

የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ከዚህ ቀደም ግጭት በተስፋፋባቸው የክልሉ አከባቢዎች የጤና መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት መድረሱ መሰረታዊ ክትባቶችን ጨምሮ በቀላሉ ተላላፊ ሆኑ በሽታዎችን መከላከል ፈታኝ መሆኑን አሳውቆ ነበር፡፡

ዶቼ ቬለ በእነዚህ አከባቢዎች እንደመፍትሄ ስለተቀመጠው አቅጣጫ ለጤና ሚኒስቴር ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ጥያቄ አቅርቦ ተከታዩን ምላሽ አግኝቷል፡፡ “ፀጥታው አስቸጋሪ በሆኑባቸው አከባቢዎች በተለይም ከወደ ወለጋ ያጋጠመውን የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ችግር ለመፍታት፤ በተለይም የህክምና ግብዓቶችን ለማድረስ በተለያየ መንገድ እየሰራን ነው፡፡ ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋርም በመተባበር ነቀምቴ በሚገኘው የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት በኩል እና በቅርንጫፎቹም በኩል ተደራሽ መሆን ያለባቸውን መሰረታዊ የህክምና ቁሳቁሶችን ተደራሽ እያደረግን ነው፡፡ ተደራስ ማድረግ ከባድ የሆነብንን ደግሞ በዓለማቀፍ ቀይ መስቀል እና ቀይጨረቃ (ICRC) በኩል አስቸጋሪ ወረዳዎች ላይ ተደራሽ እየሆኑ ነው፡፡ በወረዳዎችም የሎጂስቲክ ተደራሽነት ተመቻችቶ እንዲዳረሱ እየታርን ነው” ብለዋል፡፡

ኦሮሚያ ክልል በተለይም በምዕራብ እና ደቡብ የክልሉ አከባቢዎች በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክኒያት የማህበረሰብ ኑሮ በተለያዩ መንገዶች ክፉኛ እየተናጉ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ