1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ የቱሪዝም ዘርፍ እና ተግዳሮቱ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 29 2015

በ2015 የበጀት ዓመት 9.5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን እና 235 ሺሕ የውጭ አገር ዜጎች የኦሮሚያ ክልልን መጎብኘታቸውን የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን በዚህ ሣምንት አስታውቋል። የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ በዘርፉ ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ የኮሚሽኑ ኃላፊዎች ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/4UoLq
Äthiopien Lelise Duga - Oromia Tourism Commission
ምስል Seyoum Getu/DW

በኦሮሚያ የቱሪዝም ዘርፍ እና ተግዳሮቱ

እንደ የዓለም አቀፍ የቱሪዝም ድርጅት ትርጓሜ አንድ ሰው ከመኖሪያ ቀዬው ርቆ የ24 ሰኣታት ቆይታን ሲያደርግ እንደ ቱሪስት ሊቆጠር ይችላል፡፡ ከዚህ ትርጓሜ አንጻር በኦሮሚያ በ2015 የበጀት ዓመት የሃይማኖት በዓላት፣ የቢዝነስ እና የተለያዩ እቅስቃሴዎችን አስታከው ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው በጎብኚነት የተጠቀሱት የአገር ውስጥ ጎብኚ ፍሰት 9.5 ሚሊየን መድረሱ ተነግራል፡፡ ክልሉን የጎበኙ ዓለማቀፍ ተጓዦች ደግሞ 235 ሺኅ ናቸው፡፡ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ከምስረታው ጀምሮ ያለፉት ሶስት ዓመታት ጉዞውን በቃኘበት ሪፖርት እንዳለው በነዚህ ጊዜያት 28 የቱሪዝም መዳረሻዎችም ተፈጥረው 15 ቢሊየን ብር ገቢ ማመንጨትም ተችሏል፡፡ ወ/ሮ ላሊሴ ዱጋ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ናቸው፡፡ “የቱሪዝም መዳረሻዎቻችን ቁጥር ከመጨመር ባለፈ በመዳረሻዎቹ ላይ እሴት የመጨመር ስራን ሰርተናል፡፡ ከተሞቻችንም ገጽታቸውን ከቱሪዝም ጋር አስተሳስረው ከመንገዶቻቸው ጀምሮ በትኩረት እንዲሰሩ ለማድረግ ከፌዴራል እስከ ክልል ካሉ መዋቅሮች ጋር እየሰራን ነው፡፡”

ኮሚሽኑ ባለፉት ሶስት ዓመታት በቀጥታ ለ30 ሺህ ሰዎች የስራ እድል መፍጠሩንና 200 ሺህ ገደማ ስራዎችን ቀጥተኛ ባልሆነም መንገድ መፍጠሩንም በበጎ እምርታነት አንስቷል፡፡ ዘርፉን በዲጂታል አማራጭ ማስተዋወቅና መምራትም ላይ ፈጠራ የታከለበት በጎ ሊባሉ የሚችሉ ጅምሮች መኖራቸው የተገለጸው፡፡ ውስን በሆነው በ45 የሰው ሃይል ብቻ እንደሚሰራ የተነገረው ተቋሙ ለቱሪዝም መዳረሻ ልማት እንዲውል የ250 ሚሊየን ብር ማመንጨት መቻሉም ተብራርቷል፡፡ 
ይሁንና ዘርፉን ከፉኛ ከጎዱ ያለፉት ዓመታት ክስተቶች ኮቪድ እና በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የኣለማቀፍ ጎብኚዎችን እንቅስቃሴ የገታው ግጭት ትልቁ ተግዳሮት በሚል ተነስቷል፡፡ “በሀገር ውስጥ የነበረው ግጭት በተለይም የዓለማቀፍ ተጓዦችን እንቅስቃሴ ገትቶት ቆይቷል፡፡ አሁንም ድረስ እንደ አገር ያንን ገጽታ የመቀየር ፈተና ገጥሞናል፡፡ በክልላችንም ግጭቶች አሉ፡፡ ግን ደግሞ በተጨባጭ ካለው ግጭት በላይ የተሳሳቱ መረጃዎችን በግነት የማጉላቱ ነገርም አለ፡፡ ይሁንና ለአገር ውስጥም ሆነ ለዓለማቀፍ ጎብኚዎች ሰላማዊ ኮሪደሮች መኖራቸውን በእርግጠንነት መናገር ይቻላል፡፡”

Äthiopien | Tourismus Woche
ወንጪ ኃይቅምስል Ethiopian Tourist Office

ይሁንና አሁንም ድረስ የክልሉ በተለያዩ አከባቢዎች በጸጥታ ስጋት መዋጥ ኮሽታን የማይወድ ዘርፉን አልፈተነም ወይ በሚል ከዶይቼ ቬለ ጥያቄ የቀረበላቸው ወ/ሮ ላሊሴ ዱጋ፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት ክልሉ ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ ቢሆን አሁን ከተሰራው በብዙ እጥፍ ማሳካት እንደሚቻል በመግለጽ ተጽእኖውን ሳይሸሽጉ ከነመፍትሄው አብራርተዋል፡፡ “በርካታ አስፈሪ ወሬዎች እየተወራም አሁንም በኦሮሚያ እንቅስቃሴ አለ፡፡ ችግሮችም እያሉ አዳዲስ ነገሮች መጥተዋል፡፡ ኦሮሚያም ሆነ መላው አገር ሰላም ሆኖ ሰው አድንሻው የምንቀሳቀስበትን ጊዜ ግን እንናፍቃለን፡፡ የተጀመረው የሰላም ድርድርም እንድፋጠን እንሻለን፡፡ አገራትን ትልቅ ተስፋ እና አቅም አላትና ወደዛ ነው መጓዝ ያለብን፡፡”

የቱሪዝም ዘርፍን ካለው እምቅ አቅም አንጻር ስኬታማ ለማድርግ ቅንጅታዊ አሰራርን እንደሚያስፈልግ ያነሱት ደግሞ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ ናቸው፡፡ “ቱሪዝም ድንጉጥ ኢንደስትሪ ነው፡፡ መረጋጋትን ይፈልጋል፡፡ በመሆኑም ከዚህ አንጻር የተጋነኑ መረበሽን የሚያስተጋቡ ስሜቶች እንዳይፈጠሩ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡”

የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን በአዲስ መልክ ጀመርኩ ባለው አሰራርም ቱሪዝም ካውንሲል በሚል በተቋቋመው ምክር ቤት በኩል እስከታችኛው ያሉ በርካታ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ዘርፉን የማሳለጥ ስራ ይከወናል ብሏል፡፡ የመዳረሻ ችግሮችንም ለመፍታት በሚቀጥሉት 5 ዓመታት 100 ሆቴሎችን ለመገንባት ማቀዱን አስታውቋል፡፡ 

በኦሮሚያ ክልል በ2015 በጀት ዓመት ከቱሪዝም ዘርፍ ከ9 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ከሰሞኑ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

ሥዩም ጌቱ 

እሸቴ በቀለ