በኦሮሚያ እና አማራ ክልል አዋሳኝ ለዳግም መፈናቀል የዳረገ ግጭት
ሐሙስ፣ ሰኔ 6 2016በኦሮሚያ እና አማራ ክልል አዋሳኝ የሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ከሰሞኑ ዳግም ተፈጽሟል በተባለ የታጣቂዎች ጥቃት ማኅበረሰቡ ለዳግም መፈናቀሉን ነዋሪዎች ገለጡ ። በወረዳው ሰሙኢላሙ በተባለ በአባይ ወንዝ ዙሪያ በጎጃም በኩል የደብረኤሊያስ ወረዳን አዋስኖ ይገኛል በተባለው አከባቢው ነዋሪዎቹ «የታጠቁ ጽንፈኛ ኃይሎች» ባሏቸው አካላት ማክሰኞ እና ትናት ረቡዕ ንጋት ጥቃት ደርሶብናል ሲሉ ተናግረዋል ። ተፈናቃዮቹ ለዓመታት ወደ አከባቢው ከተሞች አፈናቅሎ ያቆያቸው ግጭት የተረጋጋ መስሎ ወደ ቀዬያቸው ቢመለሱም አሁንም ተረጋግተው ኑሮያቸውን መምራት አለመቻላቸውን ገልጠዋል ።
የአዲሱ ግጭት መልክ እና የደረሰው ጉዳት
ከሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ሳሙኢላሙ ቀበሌ ደውለው አሰርተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ ነዋሪ በአከባቢው ማኅበረሰብ ላይ ይደርሳል ያሉት ከፀጥታ እጦት ጋር ተያይዞ ያልተቋረጠው ችግር ለትንሽ ጊዜ የተሻሻለ መስሎ አሁንም ግን እንዳገረሸበት ቀጥሏል፡፡ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ በዚህ ወረዳ በተባባሰው ግጭት ሀብት ቀዬያቸውን ጥለው አገምሳ ወደ ምባል ከተማ ተፈናቅለው ከቆዩት በርካታ የአከባቢው ማህበረሰብ መካከል መሆናቸውን የገለጹት እኚህ አስተያየት ሰጪ በቅርቡ የአከባቢው ፀጥታ ይዞታ ተሻሽሏል በሚል ወደ ገጠር ቀዬያቸው ተመልሰው እርሻ ቢጀምሩም አሁንም ተመልሶ ባገረሸው የታጣቂዎች ጥቃት ለዳግም መፈናቀል መዳረጋቸውን አመልክተዋልም፡፡
"መንግስት በዚህ በወረዳችን ሰላም ነው አሁን ግቡ ብሎን ምንም እራሱን የምከላከልበት መሣሪያ የሌለውን ማኅበረሰብ ወደ ገጠር ቀዬያችን መለሰን፡፡ አገር ሰላም ብለን ወደ ቀዬያችን ተመልሰን ኑሮውን ለማቃናት በቻልነው መጠን ወደ ግብርናው ገብተን የዘራነውም በቅሎ ነበር፡፡ ግን አሁን ትናንት እና ከትናንት ወዲያ በዚህ በጎጃም ደብረኤሊያስ ወረዳ በኩል የታጠቁ ጽንፈኞች ገብተውብን በርካታ ንብረት ወስደውብናል፡፡ ለአሙሩ ወረዳ ከብት ስንዘረፍ፣ ሰውም ስሞትብን በተደጋጋሚ አቤት ብለን ሰሚ አጣን፡፡ አሁን ከወራት በፊት ነበር እርቅ ወርዷል በሚል ሁለቱን ማህበረሰብ እንደማስማማት አድርገው ወደ ቀዬያችን የመለሱን፡፡ ይሁንና አሁንም ዘረፋ ሲበረታብን ይሄው ብዙ ሰው ወደ አገምሳ ከተማ እየተመለሰ ነው” ብለዋል፡፡
በጥቃቱ የደረሰው ጉዳት
አስተያየት ሰጪው በአሁኑ ተፈጠረ ያሉት የታጣቂዎች ጥቃት ማክሰኞ ጠዋትና ማክሰኞ ሌሊት ለረቡዕ አጥቢያ የተከሰተ ነው፡፡ ከ2013 ዓ.ም. ነሃሴ ወር ጀምሮ በአከባቢው ያሉ የስምንት ቀበሌዎች ነዋሪዎች በሙሉ ቀዬያቸውን ጥለው ወደዚሁ አገምሳ ከተማ ተፈናቅለው መቆየታቸውን በማስታወስም አሁንም አነጣጥሮብናል ያሉት የታጣቂዎቹ ጥቃት ዳግም ከቀዬያቸው እያፈናቀላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
"ለመንግስት ፀጥታውን እንዲያስከብርልን እና እኛም ወደ ኑሮያችን እንድንመለስ በተደጋጋሚ ጩኸናል፡፡ ግን የሰማን አካል አልተገኘም፡፡ በቃ አሁን ልጆች ተሸክመን የቀረንን ከብት እየነዳን አሁን ቄየያችን ጥለን ወደ አገምሳ ከተማ እየተመለስን ነው፡፡ ወደ ቄዬያችን ከተመለስን በኋላ የዘራነው እያሸተ ነበር፡፡ ግን እሱንም ተቀምጠን ለመብላት አልታደልንም አሁን የሚጠብቀን የርሃብ ጦር ያስፈራናል፡፡ በዚህ አከባቢችን ብቻ ለጊዜው የሞተ ሰው ባይኖርም በታጣቂዎቹ 15 ከብቶች ነው የተዘረፈው” ብለዋል፡፡
ሌላም የአከባቢው ነዋሪ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት "እኛ እንደውም በአባይ ወንዝ ዳርቻ ላይ ነው የምንኖረው፡፡ ከደብረኤሊያስ የተሻገሩብን ታጣቂዎች ናቸው ትናንት አምስት ዛሬ ደግሞ አስር ከብቶች የዘረፉብን፡፡ በዚህ ተማረን ይሄው አሁን ልጆቻችንን ይዘን ወደ አገምሳ ከተማ እያመራን ነው፡፡ በጥሩ ሁኔታ በቅሎልን የነበረው የዘራነው በቆሎ ጥለን ከእንግዲህ የሚጠብቀን ሞት ነው በሚል ስጋት ዳግም ተፈናቅለን እየተሰደድን ነው፡፡ በርግጥ እስካሁን የጠፋ ህይወት የለም፡፡ ንብረት ዘረፋ ላይ ብቻ ነው ያተኮሩት፡፡ ለዳግም መፈናቀል ነው ተዳረግነው፡፡ ከዚህ በፊት እርቅ ወርዷል ተብለን ወደ ቀዬያችን ስንመለስ በትልቅ ደስታ ነበር ከተማውን ለቅቀን ወደ ቀዬያችን መጥተን እህል የዘራነው፡፡ አሁን ግን ከምንሞት ብለን ዳግም ለመፈናቀል ተዳርገናል” ይላሉ፡፡
የዳግም መፈናቀል መዘዝና ፈተናው
ለዳግም መፈናቀል መዳረጋቸውን የሚገልጹት የአከባቢው ተፈናቃይ ዜጎቹ የማህበረሰቡን ደህንነት የሚጠብቅ ሚሊሻ ኆነ ምንም አይነት የመንግስት ታጣቂዎች እንደሌሉም ያስረዳሉ፡፡ ለዓመታት ተፈናቅለው በከተማ ላይ መቆየታቸውን የሚገልጹት አስተያየት ሰጪዎቹ የሚያርሱበት በሬ እንኳ ስለሌላቸው በጋራ እየሆኑ በተስፋ እርሻን ጀምረው እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ አሁን ለዳግም መፈናቀል መዳረጋቸውም ከስራ ውጪ ስለሚያደርጋቸው የልጆቻው ሁኔታ በእጅጉ ያሳስባቸዋል፡፡
ስለነዋሪዎቹ አቤቱታ እና በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማከል ለአከባቢው ባለስልጣናት እና ለሆሮሩጉዱሩ ወለጋ ዞን አስተዳደር ደውለን መረጃውን ለማጥራት ያደረግነው ጥረት ለዛሬ አልሰመረልንም፡፡
ከሦት ዓመታት ገደማ በፊት በሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በአገምሳ ከተማ ዙሪያ ያሉ ስምንት የገጠር ቀበሌያት ነዋሪዎች በአከባቢው በከፋው ግጭት ሀብት ቄዬያቸውን ጥለው ወደከተማ እንደተሰደዱና ለከፍተኛ የእርዳታ አቅርቦት ችግርም ተዳርገው እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል፡፡
በቅርቡ ለተወሰኑ ጊዜያት መረጋጋት ታይቶበት ነበር የተባለው አከባቢ ከሰሞኑ በዚሁ ዞን በአቤዶንጎሮ እና ጃርዴጋ ጃርቴ ወረዳዎች የታጠቁ "ፋኖ” የተባሉ ታጣቂዎችን ለማስፈታት ተከፍቷል በተባለው ዘመቻ ሰበብ በአከባቢው አለመረጋጋት ነግሶ እንደነበርም መዘጋባችን አይዘነጋም፡፡
ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሠ