1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ እየደረሰ ያለዉ ስርቆት በምስራቅ አማራ እየጨመረ መጥቷል

ኢሳያስ ገላው
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 22 2017

በምሥራቅ አማራ አካባቢ ለኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ የተተከሉ ታወሮች እና ትራንስፈርመሮች በተደጋጋሚ እየተሰረቁ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የአካባቢው ኃላፊዎች ተናገሩ። ስርቆቱ የኃይል መቆራረጥ በማስከተሉ በሥራ ላይ ጫና አሳድሯል። ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ሰሜን ወሎ አካባቢዎች የኃይል መሠረተ ልማቶች ከሚሰረቅባቸው አካባቢዎች መካከል ይገኙበታል

https://p.dw.com/p/4oi0G
የወደቀ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ አማራ ክልል
በምሥራቅ አማራ ለኤሌትሪክ ማስተላለፊያ የተተከሉ ታወሮች እና ትራንስፈርመሮች በተደጋጋሚ እየተሰረቁ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የአካባቢው ኃላፊዎች ተናገሩ። ምስል Esayas Gelaw/DW

በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ እየደረሰ ያለዉ ስርቆት በምስራቅ አማራ እየጨመረ መጥቷል

በኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ሀይል አገልግሎት ለኤሌትሪክ ማስተላለፊያ የተተከሉ ታወሮችእና ትራንስፈርመሮች በሌቦች ተደጋጋሚ የሆነ ስርቆት እየደረሰባቸዉ ሲሆን ስርቆቱ የሀይል መቆራረጥ በማስከተሉ በአካባቢዉ ማህበረሰብ የስራ እንቅስቃሴ ላይም ጫና ማሳደሩ ተነግሯል

በኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል አገልግሎት የደሴ ሪጂን ዳይሬክተር አቶ ሀብቱ አበበ እንደሚገልፁት በተደጋጋሚ እየተከወነ ያለዉ የመብራት ማስተላለፊያ ታወሮችን መስረቅ አሁን ላይ ከሪጂኑ አቅም በላይ ሆኗል ይላሉ

ምዕራብ ወለጋ አንዳንድ ወረዳዎች ኤሌክትሪክ እንደተቋረጠ ነው

በኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል አገልግሎት የተሠሩ የመብራት መሠረተ ልማቶች በየአካባቢዉ ያሉ አስተዳደሮች እንዲጠብቋቸዉ በአዋጅ ቢደነገግም ያ እየሆነ አይደለም የሚሉት በኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል አገልግሎት የወልድያ ሪጂን ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ወልደ ሰማያት አሁናዊዉ የአካባቢዉ የሰላም ሁኔታ መደፍረስም ስርቆቱ እንዲበራከት አድርጓል ይላሉ

የኢትዮጵያ ኤሌክሪክ ኃይል ቢሮ ደሴ
በአማራ ክልል ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ሰሜን ወሎ አካባቢዎች የኃይል መሠረተ ልማቶች በተደጋጋሚ ከሚሰረቅባቸው አካባቢዎች መካከል እንደሚገኙበት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ የወልዲያ ሪጅን ዳይሬክተር ተናግረዋል።ምስል Esayas Gelaw/DW

2006  ዓመተ ምህረት የወጣዉ የኢነርጂ አዋጂ የኤሌትሪክ መሰረተ ልማት ላይ የሚፈፀሙ ጉዳቶች ከ5 እስከ 15 አመት እስራት ያስከትላል ቢልም ወንጀሉን እጂ ከፈንጂ ሲፈፅሙ የተያዙም ሆነ ተቀባዮች በቀላል ዋስ እየተለቀቁ ነዉ ይላሉ አቶ ሀብቱ አበበ ይህም የፍትህ አካሉ ለጉዳዮ የሠጠዉ ትኩረት አናሳ መሆንን ያሳያልም ነዉ ያሉት

የመብራት ተሸካሚ ታወር በተደጋጋሚ የሚሰረቅበት የኮምቦልቻ ከተማና አካባባዉ ሲሆን ስርቆት ፈፅመዉ  ተይዘዉ ወደ ፍርድቤት የተላኩ መዝገቦች መዘግየትና ተገቢ ፍትህ አለማገኘት ለምን ይከሰታል ስንል የጠየቅናቸዉ የኮምቦልቻ ከተማ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ተሾመ በላይ በኛ በኩል ያልተሰጠ ፍትህ የለም ጉዳዮን ፖሊስና አቃቤ ህግ ጋር በጋራ የሚሰራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ  ክፍተት ሊኖር ይችላል ብለዋል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አግልግሎት የታሪፍ ጭማሪ በአዲስ ዓመት

አሁን ላይ በተለይም በሰሜን ወሎ በመንግስትና በፋኖ ሀይሎች መካከል የሚከወነዉን ጦርነት እንደ መልካም አጋጣሚ የተጠቀሙ ዘራፊዎች በመርሳ: ራያ :ገረገራ: ፍላቂትና ሌሎች ቦታዎች ስርቆት እየፈፀሙ መሆኑን የወልድያ ሪጂን ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ወልደ ሰማያት ይናገራሉ

ኢሳያስ ገላው

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ