1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያመጣው ውሳኔ

ሰኞ፣ ጥቅምት 7 2015

መንግስት ውሳኔውን የዓለም አቀፉ ምጣኔ ሀብት ቀውስ በአገሪቱ ላይ እየፈጠረ ያለው ጫና እና የዋጋ ግሽበት በሕዝቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ችግር ለመፍታት የተወሰደ እርምጃ ነው ብሎታል፡፡

https://p.dw.com/p/4IHtv
Äthiopien Addis Abeba | Nationalbank
ምስል DW/H. Melesse

በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያመጣው ውሳኔ

ከዛሬ ሰኞ ጥቅምት 07 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ እንዳይሰጡ ክልከላ የተጣለባቸው ከውጭ ወደ አገሪቱ የሚገቡ 38 አይነት ሸቀጦች እና ምርቶች የከረሜላ፣ ብስኩት፣ ለስላሳ መጠጦች፣ ዊስኪ፣ ወይን፣ ቢራ፣ የተገጣጠሙ የቤት አውቶሞቢሎች እና ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች፣ ሰው ሰራሽ ፀጉር፣ የውበት እቃዎችን ያካትታል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር የእቃዎቹን ዝርዝር በማውጣት የውጭ ምንዛሬ እንዳይፈቅድላቸው ያሳለፈውን ውሳኔ ብሔራዊ ባንክ ተግባራዊ እንዲያደርግ ባዘዘበት ደብዳቤ ውሳኔው የዓለም አቀፉ ምጣኔ ሀብት ቀውስ በአገሪቱ ላይ እየፈጠረ ያለው ጫና እና የዋጋ ግሽበት በሕዝቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ችግር ለመፍታት የተወሰደ እርምጃ ነው ብሎታል፡፡
የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኝ የሆኑት አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን መንግስትን  ያስተላለፈውን ውሳኔ በአዎንታዊም በአሉታዊም ጎኑ ተመልክተውታል፡፡ “ውሳኔው አገሪቱ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገባቸው ምርቶች እና ሸቀጦች ቅድሚያ እንድትሰጥ የሚያደርግ ቢሆንም አስቀድሞ ግን አማራጮች ላይ መታሰብ ነበረበት” ሲሉም አብራርተዋል፡፡ 
ሌላው በእንግሊዝ አገር በኢንቨስትመንት ኩባንያ ውስጥ ባለሙያ ሆነው የሚያገለግሉት የምጣኔ ሃብት ተንታኝ ዶ/ር አብዱልመናን መሃመድ፤ መንግስት ውሳኔውን ያስተላለፈው ሌሎች አማራጭ ከማጣት ይመስላል ባይ ናቸው፡፡ “ለዓመታት ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች ይልቅ ወደ አገር ውስጥ የምታስገባቸው ሸቀጦች ሚዛን ለሚደፋባት አገር ይህ ውሳኔ ላይ መደረሱ የአማራጭ ማጣት ጉዳይ መሆኑ ግልጽ ነው” ብለዋል፡፡
አስተያየታቸውን ያጋሩን ባለሙያዎቹ አገሪቱ አሁን ለደረሰችበት የከፋ ያሉት የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ መነሻ ችግር በአገሪቱ የሰነበተና ዋል አደር ያለ ነው፡፡ ይህም አገሪቱ ከምትከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚመነጭ ነው ይሉታል፡፡ 
ብሔራዊ ባንክ በሰሞነኛው ውሳኔው የውጭ ምንዛሬን ለመሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች፣ ለመድኃኒቶች እና የህክምና መሳሪያዎች ብሎም እሴት ለሚጨመርባቸው የካፒታል እቃዎች ለማዋል ያልማል፡፡ ብሔራዊ ባንኩ 38ቱ የውጭ ምንዛሪ የማይፈቀድላቸው ምርቶቹ ከሕገ-ወጥ የውጭ ምንዛሪ ዝውውር ጋር ቁርኝት እንዳላቸው በጥናት የተለዩ እና መሠረታዊ ቁሳቁስ ያልሆኑ ናቸውም ብሏል፡፡
በቅርቡም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እየተባባሰ የመጣውን የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ወሰድኩ ባለው እርምጃ፤ 391 የሚደርሱ በህገወጥ የገንዘብ ማዘዋወር ወይም ሀዋላ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች የባንክ ሂሳብ መዘጋቱን ማሳወቁ ይታወሳል፡፡
ስዩም ጌቱ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ኂሩት መለሰ