1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሽብርተኝነትአፍሪቃ

በአፍሪቃ የጸረ- ሺብር ትግል ላይ የመከረ ከፍተኛ ስብሰባ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 18 2016

በአፍሪቃ እየተስፋፋና እየተጠናከረ ነው የተባለውን የአሸባሪዎች ጥቃት ለመክላከል ብሎም ለማጥፋት በሚቻልበት ሁኔታ የመከረ የአፍርቃ የጸረ ሽብርና ደህንነት ከፍተኛ ጉባኤ በዚህ ሳምንት ሰኞና ማክሰኞ በናይጀሪያ ዋና ከተማ አቡጃ ተካሂዷል።

https://p.dw.com/p/4fEfP
የናይጀሪያ ዋና ከተማ አቡጃ
የናይጀሪያ ዋና ከተማ አቡጃምስል Ute Grabowsky/photothek/picture alliance

በአፍሪቃ የጸረ- ሽብር ከፍተኛ ጉባኤ

 

በአፍሪቃ እየተስፋፋና እየተጠናከረ ነው የተባለውን የአሸባሪዎች ጥቃት ለመክላከል ብሎም ለማጥፋት በሚቻልበት ሁኔታ የመከረ የአፍርቃ የጸረ ሽብርና ደህንነት ከፍተኛ ጉባኤ በዚህ ሳምንት ሰኞና ማክሰኞ በናይጀሪያ ዋና ከተማ አቡጃ ተካሂዷል። በጉባኤው በመቶዎች የሚቆጠሩ አራት መሪዎችን ጨምሮ የ29 የአፍርቃ ሃገራት ተወካዮችና ሚኒስትሮቸ፣ የመንግሥታቱ ድርጅትና የአፍርቃ ሕብረት፤ የዓለም አማቀፍና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች መሳተፋቸው ተገልጿል። የጉባኤው አስተናጋጅ ናይጀሪያ ጉባኤውን የጠራቸው ከመንግሥታቱ ድርጅት ጋር በመተባበር መሆኑ ታውቋል።

የበለጠ የአሸባሪዎች እንቅስቅሴ የሚታይባቸው ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊና ኒጀር ግን መፈቅለ መንግሥት የተክሄደባቸው በመሆኑ ምክንያት ከአህጉራዊም ሆነ ቀጠናዊ ስብስቦች የተገለለሉ በመሆናቸው በዚህ ጉባኤም አልትሳተፉም።

ለአፍሪቃ ጸረ-ሽብር ትግል የቀረበ ጥሪ

የጉባኤው ሰብስቢና የአስተናጋጇ አገር ናይጀሪያ ፕሬዝዳንት ሚስተር ቦላ ቲኑቡ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ አሸባሪነት የበለጸገና ነጻ ማኅበረሰብ የመፍጠር ህልማችንን እየነጠቀን ነው በማለት፤ በአሁኑ ወቅት አህጉሩ የተጋረጠበትን ስጋት አውስተዋል። አሸባሪዎች ገበሬዎችን ከማሳቸው፤ ተማሪዎችን ከትምህርት ቤታቸውና ነጋዴውንም ከንግዱ የሚነጥሉ በመሆናቸው፤ በተቀናጀ ዓለም አቀፋዊ ትግል ልንዋጋቸው ይገባል በማለትም ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ይህን ጸረ አሸባሪነት ትግል የመርዳት የሞራልና የሕግ ግዴታ ያለበት መሆኑን አስገንዝበዋል።

ፎቶ ከማኅደር፤ ኒዠር ከተማ
«አፍሪቃ በአሁኑ ወቅት ቦኩ ሃራምና አልሸባብን ከመሳሰሉት የሽብር ድርጅቶች በተጨማሪ እራሱን እስላማዊ መንግሥት የሚለው አይሲስ እና አልካይዳ ጭምር የሚንቀሳቀሱበትና ከፍተኛ ጥቃት እየፈጸሙበት ያለ አህጉር መሆኑ እየተገለጸ ነው።»ፎቶ ከማኅደር፤ ኒዠር ከተማ ምስል Ludovic Marin/AFP/Getty Images

በአፍሪቃ የተለያዩ ቦታዎች የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖችና እያደረሱ ያለው ጉዳት

አፍሪቃ በአሁኑ ወቅት ቦኩ ሃራምናአልሸባብን ከመሳሰሉት የሽብር ድርጅቶች በተጨማሪ እራሱን እስላማዊ መንግሥት የሚለው አይሲስ እና አልካይዳ ጭምር የሚንቀሳቀሱበትና ከፍተኛ ጥቃት እየፈጸሙበት ያለ አህጉር መሆኑ እየተገለጸ ነው። የአፍሪቃ የሽብር ጥናትና ምርምር ማዕከል በእንግሊኛ ምህጻሩ ACSRT ይፋ እንዳደረገውና በጉባኤው እንደተነገረው፤ ዛሬ በአፍሪቃ በቀን ስምንት የሽብር ጥቃቶች ይደርሳሉ፤ 44 ግድያዎችም ይፈጸማሉ። ባለፈው ዓመት ብቻም 7,000 ስላማዊ ሰዎችና 4,000 ወታደሮች በአሸባሪዎች ተገድለዋል። አሸባሪዎች በአህጉሩ ጥቃት የሚያደርሱትና የሚንቀስቀሱት በሁሉም ማለት፤ በምሥራቅ፤ ሰሜንና፤ ደቡብ  ቀጣናዎች ቢሆንም፤ የክራይሲስ ግሩፑ ተመራማሪ ሚስተር ሙሪቲ ሙቲጋ ሲናገር እንደተሰማው ግን፤ በአፍሪቃ ዋናው የሽብር ማዕከል የሳህል አክባቢ ነው። «ዛሬ ሳህል በዓላማችን ዋናው የሽብር ዕምብርት ነው። ቀደም ሲል በሳህል አካባቢ የሚፈጸመው የአሻባሪዎች ጥቃት ከጠቅላላው የሽብር ጥቃት ሦስት ከመቶ የነበር ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ግን 50 ከመቶውን ይዟል» በማለት አፍሪቃ በተለይ ግን የሳህል አካባቢ አደገኛ የሽብር ቀጣና መሆኑን ገልጿል። በምሥራቅ አፍሪቃ የሚንቀሳቀሰውን የሽብር ቡድን አልሸባብንም በመጥቀስ ጭምር።

ያልተሳካው የአፍሪቃ የጸረ ሽብር ዘመቻ

የዓለም አቀፉ የጸረ ሽብር ትግል አካል የሆነው የአፍሪቃ ጸረ ሽብር ዘመቻ ምንም ያህል የብሔራዊም ይሁን ዓለም አቀፍ ሀይሎች ቢሳተፉበትም፤ ውጤቱ ግን የተፈለገውን ያህል አለመሆኑ በጉባኤው በሰፊው ተወስቷል። የመንግሥታቱ ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና ሙሀመድ ባሰሙት ንግግርም፤ የአፍርቃ ጸረ ሽብር ዘመቻ ያልተሳካ መሆኑን ነው የገለጹት፤ «ዛሬ በሚያሳዝን ሁኔታ አሸባሪዎች የሚንቀሳቀሱብቸው ቦታዎች ተበራክተው ይታያሉ። ብዙ የተባለለት የጸረ ሽብር ዘመቻው የተፈለገውን ውጤት ሊያስገኝ አልቻለም» በማለት ሌላ አዲስና የተሻለ የትግል ስልት መንደፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የአፍሪቃ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሚስተር ሙሳ ፋኪ
የአፍሪቃ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሚስተር ሙሳ ፋኪምስል John Thys/AFP

የአፍሪቃ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሚስተር ሙሳ ፋኪም በበኩላቸው፤ የዓለም አቀፉ ማኅበረስብ ለአፍሪቃ ጸረ ሽብር ዘመቻ የሚያደርገው አስተዋጾ ከዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ነው በጉባኤው የተናገሩት፤ «የጸረ ሽብርትግል የሚያካሂዱ አገሮች የገንዘብ እጥረት እያለባቸው፤ የመንግሥታቱ ድርጅት የረባ ውጤት ለማይገኝበት ዘመቻ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ማፍሰሱ አይገባንም» በማለትም የገንዘብ ችግር አንዱ ለዘመቻው ያለመሳካት ምክንያት መሆኑን አስታወቀዋል።

የጉባኤው ማጠቃለያ ሀሳቦች

በጉባኤው ሽብርተኘነትን ለመዋጋት አዲስ አይነት አደርጃጀትና ተንሳሽነት እንደሚያስፈልግ የታመነበት ሲሆን፤ ችግሩ ዓለም አቀፍዊ በመሆኑም ከአህጉሩ ውጭ ያሉ ሀይሎችም ለዚህ ዘመቻ ትኩረት ሊስጡና ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጥሪ ተላልፉል። ባጠቃላይም አፍሪቃ መር የሆነ የጸረ ሽብር ስትራቴጂ መንደፍና የመረጃ መለዋወጫ መረብ መዘርጋት አስፈላጊ ስለመሆኑም በጉባኤው እንደታመነበት ተገልጿል።

ለጸረ ሽብር ዘመቻ ስኬት ተጨማሪ ግብአቶች

አሸባሪነትን ለማስወገድ ወታደራዊ እርምጃ አስፈላጊ ቢሆንም ብቻውን ግን በቂ እንዳልሆነ ነው ባለሙያዎች የሚያስገነዝቡት። የክራይሲስ ግሩፑ ሚስተር ሙሪቲ እንደሚለው በአንዳንድ ሁኒታ ክወታደራዊ ዘመቻ ጎን የውይይትና ድርድር በሮችን መክፈት ተገቢ ነው። ከሁሉም በላይ ግን መንግሥታት ለተቃውሞና አመጽ ምክንያት ሊሆኑ በሚችሉ አጀንዳዎች ላይ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ያለባቸው ሲሆን፤ ብዙዎቹ ግን ይህን ስለማያደርጉ እምነት የሚጣልባቸው እንዳልሆኑ ነው ሚስተር ሙሪቲ የሚናገረው፤ «መንግሥታት ለሕዝቦች ጥያቄና ብሶት መልስ ስለማይሰጡ፣ ሕጋዊነትና ቅቡልነት አጥተዋል፤ በተለይ በገጠሩ አካባቢ» በማለት ለጸረ ሽብር ዘመቻዎች ስምረት ከወታደራዊ እርምጃዎች ጎን የኅብረተሰቡን አጠቃይ ችግሮች ለመፍታት ጥረት ማድረግና ቅቡልነት ማግኘት ወሳኝ መሆኑን ባለሙያው አስገንዝበዋል።

ገበያው ንጉሤ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ