1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአፍሪቃ የጨመረው የወጣቶች ተቃውሞ

ዓርብ፣ ሐምሌ 26 2016

ኬንያ እና ናይጄሪያ አፍሪቃ ውስጥ ከሰሞኑ የፖለቲካ ተቃውሞ ማዕበል የሚያስተናግዱ ግንባር ቀደም ሀገራት ናቸው። ባለው የኑሮ ሁኔታ ደስተኛ ያልሆኑ፣ በተለይም ወጣቶች ተቃውሟቸውን ለመግለፅ አደባባይ ወጥተዋል።

https://p.dw.com/p/4j14H
 በናይሮቢ ኬንያ ተቃውሞ ሰልፍ ወጣቶች አስለቃሽ ጢስ ሲሰሹ
ተቃውሞ ሰልፍ በናይሮቢ ኬንያምስል Daniel Irungu/EPA

በአፍሪቃ እየጨመረ ያለው የወጣቶች ተቃውሞ

ኬንያ ለሳምንታት የሕዝብ ተቃውሞ ካስተናገደች በኋላ አሁን ደግሞ በአፍሪቃ በሕዝብ ብዛት የምትታወቀው ናይጄሪያ ተከትላለች።  ህዝቡ በተለይም ወጣቱ ወደ ጎዳና ወጥቶ ተቃውሞዉን እንዲገልጽ የገፋፉው ምክንያት ተመሳሳይ ነው።  የዋጋ ግሽበት። በናይጄሪያ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት በሚል ከአንድ ዓመት በፊት ፕሬዚደንት ቦላ አህመድ ቲኒቡ ካስተዋወቁዋቸው ማሻሻያዎች በኋላ ሀገሪቱ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ገጥሟታል። የሀገሪቱ ገንዘብ ናይራ ዋጋ አጥቷል።  የምግብ ዋጋ 40 በመቶ ያህል ፣ የነዳጅ ዋጋ ደግሞ በሦስት እጥፍ ጨምሯል።  

«ትዕግስት ከቁብ ያልተቆጠረበት ሀገር»

#EndbadGovernanceinNigeria  ወይም መጥፎ አስተዳደር በናይጄሪያ ያብቃ በሚል ሀሽታግ ስር ህዝባዊ ተቃውሞው ወጥሏል። ትናንት ሀሙስ በሀገሪቱ ከሌጎስ እስከ አቡጃ  በኑሮ ውድነት ላይ ሀገር አቀፍ ተቃውሞ ጠርተዋል፣ ተካሂዷልም። አስተባባሪዎቹ ልክ እንደ ኬንያ ወጣቶች ናቸው።  «ለተቃውሞ አደባባይ እንድወጣ የገፋፋኝ ርሃብ ነው» ይላል ከሀገሪቱ 2ኛዋ ትልቅ ከተማ በሆነችው ካኖ በተካሄደው ሰልፍ ላይ የተካፈለው የ24 ዓመት ወጣት አሳማዑ ለፈረንሳይ ዜና ምንጭ የገለፀው።  በሰልፉ ዋዜማ የናይጄሪያ ባለስልጣናት ህዝቡ በትግዕስት እንዲጠብቅ እና ለተቃውሞ እንዳይወጣ አሳስበዋል። በዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ተንታኝ እና መምህር የሆኑት ኢብራሂም ባባ እንደሚሉት « በዓለም ላይ የሰዎች ትዕግስት ከቁብ ያልተቆጠረበት ሀገር ካለ ናይጄሪያ ቀዳሚዉ ነዉ»  ሲሉ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። 

ተቃውሞ ሰልፍ በናይጄሪያ
ተቃውሞ ሰልፍ በናይጄሪያምስል Adekunle Ajayi/IMAGO/NurPhoto

 

«የፖለቲካ እና የገዥ ልሂቃን ስልጣናቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ ሲሉ ለዓመታት በህዝቡ መካከል በብሔር፣ በኃይማኖት ፣ በአካባቢ እና ሌሎችም ማህበራዊ መከፋፈልን ፈጥረዋል።ይህም ህዝቡን በቁጥጥራቸው ስር ለማዋል ነው» ይላሉ ኢብራሂም ባባ።  ናይጄሪያ ውስጥ ከጎርጎሮስያኑ 2020 በኋላ ትልቅ የተቃውሞ ሰልፍ ሲካሄድ የአሁኑ የመጀመሪያው ነው። ያኔ የፖሊስ ጥቃትን በመቃወም #ENDSars የተሰኘ ንቅናቄ በአገር አቀፍ ደረጃ ተካሂዶ ነበር።  እንደዛም ሆኖ በሀገሪቱ የተለያዩ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ባለፉት ወራት ተካሂደዋል። ከእነዚህ መካከል በረራን ያስተጓጎለ እና የመብራት መቆራረጥ ያስከተለው የሰራተኛ ማህበራት የስራ ማቆም አድማ አንዱ ነው። የናይጄሪያ መንግስት ለረጅም ጊዜ ሲሰጥ የነበረውን የነዳጅ ድጎማ መሰረዙ ብዙዎችን ያስቆጣ ለውጥ ነው። የዚህ መቅረት ከፍተኛ የኑሮ ውድነት አስከትሏል።  ብዙዎች ደግሞ ለአሁኑ ስቃያቸው ተጠያቂ የሚያደርጉት ባለፈው ዓመት ፕሬዚዳንቱ ይፋ ያደረጉት የማሻሻያ ለውጥን ነው።
የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪ ዳንኤል ሲልከ ለዶይቸ ቬለ እንደተናገሩት መንግሥት የወጣቶች ጥያቄ ሲነሳ በቃ ብሎ መስማት ይኖርበታል።« እንዲሁም ከራሳቸው ጠባብ የፖለቲካ ፓርቲ ፍላጎት ይልቅ የአገራቸውን እና የወጣቱን ጥቅም ማስቀደም አለባቸው ። በብዙ አጋጣሚዎች የቢሮ ቁልፉን እንደያዙ የኋላ ኪሳቸውን ለመሙላት ነው የሚያስቡት።» ይሁንና የናይጄሪያ መንግሥትም የወጣቱን ተቃውሞ ከመስማት ይልቅ ለማሸማቀቅ ሞክሯል። በአቡጃ እና ካኖ ከተማ፤ ፖሊስ ሰልፈኞች ላይ አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞችን ሊበትን ሞክሯል። 

Nigeria Bola Ahmed Tinubu
ምስል Kola Sulaimon/AFP

የኬንያ ተቃውሞ እና ተሳታፊ ወጣቶች

በኬንያ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ይፋ እንዳደረገው ከሰኔ አጋማሽ አንስቶ ከ50 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ ወደ 700 የሚጠጉ ሰዎች በዘፈቀደ ታስረዋል።  59 ታፍነዋል ወይም የደረሱበት አይታወቅም። 
ኬንያዊት ሻኪራ በኬንያ ተቃውሞ ፊቷ በማህበራዊ ሚዲያ ጎልቶ የወጣ ወጣት ናት።  ይህም የኬንያ ፖሊስ የትም አይወስደኝም በማለት «ለመብቴ እቆማለሁ» ስትል በመከራከሯ ነው። «ይህ የሆነው በተቃውሞው ሁለተኛ ቀን ነው። በመጀመሪያው ዕለት ታስሬ ነበር።   ታስሬ ለማለት ግን ይከብደኛል። ፊታቸው በተሸፈነ ወታደሮች ጥቃት ደርሶብኛል ብል ይቀላል።  እየደበደቡ እና ጉዳት እያደረሱብኝ ገፍትረው ወደ መኪናቸው አስገቡኝ እና ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱኝ። እዛም እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ከሌሎች ሰልፈኞች ጋር ቆየሁ። እና ለሰዎች ጥያቄ ምላሹ እንደዚህ አይነት የኃይል ርምጃ መሆኑ ለምን እንደሆነ አልገባኝም። ይህ ፍፁም አይገባንም።  ብቻ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ዳግም ከተፈጠረ  ለራሴ መሟገት አለብኝ ብዬ ነበር። በአጋጣሚ ሰዎች ስለነበሩ ሁኔታውን በቪዲዮ ቀረፁ።  እውነቱን ለመናገር ፈርቼ ነበር » ይሁንና ንዴቴ ፍርሀቴን አሸነፈው ትላለች። ሌላው ዶይቼ ቬለ ያነጋገረው ኬንያዊ ጋዜጠኛ ሙሀመድ ይባላል። ኬንያ ውስጥ ከዚህ ቀደምም መንግሥትን የሚቃወሙ ተቃውሞዎች ተካሂደው የሚያውቁ ቢሆንም የአሁን ግን የተለየ ነው ይላል። « የአሁን ለየት የሚያደርገው ሰውን ታከተው። ሁል ጊዜ እዚች ሀገር ላይ የውጥ በተፈለገ ጊዜ ፖለቲከኞች ይመጡ እና እንቅስቃሴውን ወደሚፈልጉት አቅጣጫ ይመሩታል። ከዛ ዞሮው እዛው ነበር። የአሁኑ ግን በቃ የሚል ነው»

የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ
የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶምስል Thomas Mukoya/REUTERS

ኬንያውያን መጀመሪያ ላይ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡት የኬንያ መንግሥት ያስተዋወቀውን የግብር ጭማሪ በመቃወም ነበር።  ነገር ግን ሰልፉ መልኩን እየቀየረ ሄደ። ምንም እንኳን ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ወጣቱ “ዴሞክራሲያዊ ኃላፊነቱን ተወጥቷል” ቢሉም ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ወጣቶች ህንፃዎችን በማቃጠል፣ የንግድ ሱቆችን በመዝረፍ እና ወንጀል በመፈፀም ተወንጅለዋል።  በተቃውሞ ስትሳተፍ የመጀመሪያዋ የሆነው ኢቪ የተቃውሞው ድባብ መጀመሪያ ላይ ሰላማዊ ነበር ትላለች። «ጎዳና ላይ የድግስ ድባብ ነበር። ሰዎች የቲክቶክ ቪዲዮ እየቀረፁ ነበር። ውኃ፣ መረጃ እና መፈክር ይለዋወጡ ነበር። የጋዝ ማስክ የሚሸጡ ሰዎች ነበሩ።  በብዛት ሰላማዊ ነበር።» 
ቻርለስ ኦዊኖ የቀድሞ የፖሊስ ቃል አቀባይ ናቸው።  እሳቸው እንደሚሉት በእንደዚህ አይነት ወቅት ፖሊስ አጣብቂኝ ውስጥ ይገባል።

ፖሊስ ቅድሚያ የሚሰጠው ለማን ነው? 

« ፖሊስ ሀገርን ከግምት ውስጥ የሚያስገባው። እያንዳንዳችሁን። እሷ ለምሳሌ ነጋዴ ናት እንበል። ሱቋ ቢዘረፍ፣ ካሳ የሚከፍላት ኢንሹራንስ ባይኖራት ምን ትሆናለች።  ፖሊስ ጠላታችን ነው ካልን ጥሩ ግን የሰው ንብረት አንዝረፍ። እኔ ለማንም ወግኜ መከራከል አልፈልግም። ግን ህጉን መከተል እንችላለን? »
ፍሬደሪክ ግን በቀድሞው ፖሊስ ባልደረባ ሀሳብ አይስማማም። ሀኪ አፍሪካ የተሰኘው እና መቀመጫውን ሞምባሳ ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተማጋች ድርጅት አባል ናቸው። 
« ከፖሊስ የምናገኘውን መረጃ ትክክለኛነት ለማጣራት እንሞክራለን። ለምሳሌ ሁለት በጥይት ተመተው የተገደሉ ሰዎች ነበሩ። ፖሊስ የመዘገባቸው ግን በአደጋው ሰለባ የሆኑ ሰዎች እንደሆኑ አድርጎ ነው። ስለዚህ የፖሊስን ስህተት ወይም ወንጀል የሚመረምረው ራሱ ፖሊስ ሊሆን አይገባም።»

 በናይሮቢ ኬንያ ተቃውሞ ሰልፍ ወጣቶች አስለቃሽ ጢስ ሲሰሹ
በናይሮቢ ኬንያ ተቃውሞ ሰልፍምስል Boniface Muthoni/SOPA/IMAGO

የቀድሞ የፖሊስ ቃል አቀባይ ቻርለስ ኦዊኖ የመብት ተቋርቋሪዎችም ሆኑ የተቃውሞ ተሳታፊዎች እንዲህ ፖሊስን ሲወነጅሉ በምክንያት እንደሆነ ማመን ግድ ብሏቸዋል።  
«አንዳንድ ፖሊሶች አይሳሳቱም ብል ስህተት ነው የሚሆነው። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሰልፍ ሰላማዊ መሆን የለበትም ፤ መሳሪያ መታጠቅ አለብን የሚል ካለ ይህም ስህተት ነው የሚሆነው  »የኬንያው ተቃውሞ ማብቂያው የት ነው?
የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ የሕዝባቸውን ድምፅ በመስማት በሚል ከሦስት ሚኒስትሮቻቸው በቀር ጠቅላላ ካቢናቸውን በትነው አዲስ ሾመዋል።   ይህ ለተቃውሞ ጥያቄ ምላሽ ይሆን? ወጣት ሜሪ «አይ አይመስለኝም» ትላለች። « ቦታ ቀያየሩ እንጂ ሌላ ነገር አላደረጉም። ለውጥ አደረኩን ለማለት እና በሰው አዕምሮ ለመጫወት ብቻ ነው። እኔ ለምሳሌ እንደ ነጋዴ ይህ ተቃውሞ ዋጋ አስከፍሎኛል።  በዛ የተቃውሞ ማክሰኞ ዕለት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ሰዓታት ንብረታችን ተዘርፏል። ግን አንድም ፖሊስ አልነበረም። » 
በኬንያ የተደረጉት ሰልፎች ለጊዜው ጋብ ቢሉም ወጣቱ ግን ዘላቂ መፍትሔ አላገኘም።በሐሙሱ የናይጄሪያ ታላቅ ሀገር አቀፍ ተቃውሞ ደግሞ የብዙ ሰዎች ህይወት አልፏል። ተቃውሞውም ይቀጥላል ተብሏል። ይህ  ወዴት እንደሚያመራ ከጊዜ ጋር የሚታይ ይሆናል። 

ኦኬሪ ንጉትጂናዞ / ኤዲት ኪማኒ

ልደት አበበ 

አዜብ ታደሰ