1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአፍሪቃ ቀንድ ለሚደጋገመው ድርቅ መፍትሄ

ማክሰኞ፣ የካቲት 28 2015

በአፍሪቃው ቀንድ አካባቢ የሚደጋገመው ድርቅ ባለፉት ሦስት ዓመታት ደግሞ ተጠናክሮ በሰውም በእንስሳትም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ቀጥሏል። ቆላማውን አካባቢ በተቀናጀ ስልት በድርቅ ተደጋግሞ ከመጎዳት መከላከል እንደሚቻል የደን እና የተፈጥሮ አካባቢ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/4OLVI
Kenia Dürre l Leben im Dorf Parapul
ምስል Simon Maina/AFP

ጤና እና አካባቢ

በአፍሪቃው ቀንድ አካባቢ የሚደጋገመው ድርቅ ባለፉት ሦስት ዓመታት ደግሞ ተጠናክሮ በሰውም በእንስሳትም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ቀጥሏል። በተጠቀሰው አካባቢ ድርቅ ለመደጋገሙ ባለሙያዎች የቦታው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ጋር መዳመሩን በምክንያትነት ያነሳሉ።

ከሰሞኑ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሳበው በቦረና ያስከተለው ጉዳት ቢሆንም ድርቁ ግን በደቡብ ኦሞ ዞን ስር በምትገኘው ሐመር ወረዳ፤ እንዲሁም በሶማሌ ክልልም አርብቶ አደሩ ሕዝብ ለከባድ ችግር አጋልጧል። ኢትዮጵያ ውስጥ በየጊዜው ለድርቅ የሚጋለጠው ቆላማ አካባቢ እንደሆነ እና የሀገሪቱ 60 እና 70 በመቶ የሚሆነው ክፍልም ወደቆላማነት እየተሸጋገረ መሆኑን ነው የደን እና የአካባቢ ተፈጥሮ ምርምር ባለሙያው ዶክተር አደፍርስ ወርቁ የሚናገሩት። አሁን በድርቅ ለተጎዳው ወገን እርዳታ ለማቅረብ እርብርቡ ቀጥሏል። ለጊዜ ችግሩ በእርዳታ ቢታገስም እንኳ ድርቁ እንደልማዱ ዓመትም ሁለት ዓመትም ቆይቶ መከሰቱ እንደማይቀር ነው ያለፈው ልምድ የሚያመላክተው። ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ አይኖረውም? ዶክተር አደፍርስ ቆላማውን አካባቢ በድርቅ ከመጎዳት ሊያድነው የሚችለው በከብት እርባታ ላይ ብቻ ያተኮረውን አካባቢ የተቀናጀ የግብርና ስልት እንዲከተል መንገድ ማሳየት ቀዳሚ እርምጃ መሆን ይገባዋል ይላሉ። «እነዚህ ቆላማ አካባቢዎች ድርቅ መታቸው ብለን ልንተዋቸው አንችልም። የኢትዮጵያን ትልቁን መሬት የያዙት እነዚህ አካባቢዎች ናቸው፤ 60 በመቶ 70 በመቶ የሀገሪቱ መሬት ቆላማ እየሆነ ነው።» አሁን ሰዎች እንዳይሞቱ የሚደረገው ርብርብ እንዳለ ሆኖ ምን እናድርግ የሚለው ፌደራል መንግሥትን፣ የክልል መንግሥታትንም ሆነ ባለሙያዎችን ሊያሳስብ ይገባልም ነው ያሉት።  

Somalia | Menschen leiden unter der Dürre
በድርቅ የተጎዳችው ሶማሊያምስል Mahelder Haileselassie/ActionAid/AP/picture alliance

በሌላ አካባቢ ያለውን ተሞክሮ በመነሻነት የጠቀሱት የደን ምርምር ባለሙያው እንደቦረባ ባለው ቆላማ አካባቢ ከሰልን ማክሰል በራሱ የገቢ ምንጭ ሊሆን እንደሚችልም አንስተዋል።

የኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪቃው ቀንድ ሃገራት ቆላማ አካባቢዎች የደን ይዞታን በማሻሻል ለድርቅ የመጋለጡን አጋጣሚና የተፈጥሮን ሚዛን ለመጠበቅ እንደሚቻል የደን ምርምር ባለሙያው ዶክተር ይታገሱ ተክሌም ይናገራሉ።

«ኢትዮጵያም ላይ ያለው ቦረና፣ ኬንያም ሶማሊያ ችግራቸው ተመሳሳይ ነው እዚህ ደረጃ የደረስንበት። በመሆኑም የመጀመሪያው ርምጃ ብዝሃህይወትን መመለስ አለብን።»

በተጎዳው አካባቢ ዛፎችን መትከል እና የተዛባውን ብዝሃህይወት መመለስ አስፈላጊ ነው የሚሉት የደን ምርምር ባለሙያው ተከላው ግን በዘፈቀደ መሆን የለበትም ባይ ናቸው። በአርብቶ አደሩ አካባቢ በሚኖረው የእርሻ ሥራ ደግሞ የጥምር ግብርና ስልትን ማለትም እህልን ብቻ ሳይሆን ፍራፍሬ የሚሰጡ ዛፎችን በየማሳው ላይ መትከል ዘላቂነት ያለው መፍትሄ እንደሆነም ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ነባሩን የማኅበረሰቡን የተፈጥሮ ሀብት ሚዛናዊ ክፍፍል እና አጠቃቀም እየመራ የኖረውን የገዳ ስልት አሁንም ኅብረተሰቡ በባህላዊው መንገድ እንዲጠቀምበት ማስቻልም አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለው ዶክተር ይታገሱ ጠቁመዋል።

የአፍሪቃው ቀንድ አካባቢን ድርቅ ያባባሰው የአየር ንብረት ለውጥ መሆኑን አጽንኦት የሚሰጡት ዶክተር አደፍርስ በበኩላቸው ለውጡን ለመቋቋም የሚቻልበት መንገድ አለ ነው የሚሉት። «የአየር ንብረት ለውጥን እንዳይለወጥ ማድረግ ይቻላል፤ እኛው ነን ያበላሸነው።»

Kenya Dürre
በድርቅ የጎዳው የኬንያ አካባቢ ምስል Brian Inganga/AP Photo/picture alliance

የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን ድርቅንም ሆነ ጎርፍን በተመለከተ ሲወሳ ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ ዐበይት ጉዳዮች አንዱ የአካባቢው ማኅበረሰብ በመሠረተ ልማትም ሆነ በተቋማት ደረጃ እንዲሁም በተማረ የሰው ኃይል ያለው አቅም ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለበትም ነው ያመለከቱት። በድርቅ በተጎዱት አካባቢዎች የሚኖረው ማኅበረሰብ የሚከተለው የኑሮ ዘይቤ ለጉዳት የተጋለጠና አንድ ወጥ መሆኑም በራሱ ችግሩን እንዳከበደው፤ ከዚህ ይልቅ የተቀላቀለ የኑሮ ስልት በአካባቢው እንዲለመድ መደገፍ እና መንገድ ማመላከትም በዘላቂነት መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል ምክረ ሃሳባቸውን አካፍለዋል።

በነገራችን ላይ አድማጮች በአሁኑ ወቅት ከቦረና አካባቢ በተጨማሪ ለከፋ ድርቅ ለተጋለጡት የሶማሌ ክልል አካባቢዎች እንዲሁም ከደቡብ ኦሞ ሐመር ዞን እና አካባቢው ነዋሪዎች የሕይወት አንድ ሰብአዊ እርዳታ ጥሪ እየቀረበ ነው። ለድርቅ መጋለጥን ለመቀነስ ከሚያስችሉ ዘላቂ መፍትሄዎች መሠረታዊ ያሏቸውን ምክረ ሃሳቦች ያካፈሉንን የደን ምርምር ባለሙያዎች እናመሰግናለን።

 ሸዋዬ ለገሠ