1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትኢትዮጵያ

በአዲስ አበባ ተማሪዎች ምዝገባ ካጠናቀቁ በኋላ ይፈርሳል የተባለው ት/ቤት

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 23 2016

«ትምሕርት ቤትን ማፍረስ ትውልድን ማፍረስ ነው» የሚል ጽሑፍ ጽፈው ቢማጸኑም የተለወጠ ነገር የለም ። ከ1300 በላይ ተማሪዎች ያሉት እና ለ20 ዓመታት የቆየው ትምሕርት ቤት ይፈርሳል ተብሏል ። ቦሌ ዓለማቀፍ አየር ማረፊያ አከባቢ የሚገኘው «አዲስ ግሎባል» ትምህርት ቤት በኮሪደር ልማት ምክንያት እንደሚፈርስ ተገልጧል ።

https://p.dw.com/p/4ivMX
Äthiopien | Durchführung eines Modernisierungsprogramms in Adis Abeba
ምስል Seyoum Getu/DW

ትምህር ቤቱን የማፍረስ ውሳኔ ዘግይቶ የመጣ ነው ተብሏል

«ትምሕርት ቤትን ማፍረስ ትውልድን ማፍረስ ነው» የሚል ጽሑፍ ጽፈው ቢማጸኑም የተለወጠ ነገር የለም ። ከ1300 በላይ ተማሪዎች ያሉት እና ለ20 ዓመታት የቆየው ትምሕርት ቤት ይፈርሳል ተብሏል ። በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ዓለማቀፍ አየር ማረፊያ አከባቢ የሚገኘው «አዲስ ግሎባል» የተሰኘው ትምህርት ቤት በኮሪደር ልማት ምክንያት እንደሚፈርስ ዘግይቶ በመነገሩ ልጆቻችንን የምናስተምርበት ስፍራ አስጨንቆናል ሲሉ ወላጆች ተናግረዋል ። የተማሪ የደንብ ልብስ ተሰፍቶ ምዝገባ ካለቀ በኋላ አፍርሱ መባላችን ግራ አጋብቶናል ብለዋል ወላጆች ።  

አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የተማሪዎች ወላጆች ትምህርት ቤቱን የማፍረስ ውሳኔ  ይፋ የተደረገው ትምህርት ቤቱ ለሚቀጥለው 2017 የትምህርት ዘመን ምዝገባ አጠናቆ ዝግጅት ካደረገ በኋላ ነው ብለዋል ።

አሁን ላይ በከተማው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ሐምሌ 15 ቀን፣ 2016 ዓ.ም. የምዝገባ መርሃ ግብር በማጠናቀቃቸው ተጨማሪ ተማሪዎችን ለመቀበል ቦታ እንደማይኖራቸውም እየገለጹላቸው በመሆኑ ወላጆች አስቸጋሪ ያሉት ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ትምህር ቤቱን የማፍረስ ውሳኔ

አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ አንድ የተማሪ ወላጅ እንደ ወትሮው በ2017 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን አዲስ ግሎባል አካዳሚ ልጆቻቸውን ለማስተማር ከመንግስት በወረደው መመሪያ የተማሪዎች ምዝገባ ሃምሌ 15 ድረስ እንዲጠናቀቅ በተባለው መሰረት ልጆቻቸውን ማስመዝገባቸውን በማስረዳት አስተያየታቸውን ጀምረዋል፡፡ ይሁንና ይህ አዲስ አበባ ውስጥ በቦሌ ዓለማቀፍ አየር ማረፊያ አከባቢ ላለፉት 20 ዓመታት የመማር- ማስተማር አገልግሎት ስሰጥ የቆየው ትምህርት ቤት የተማሪዎች ምዝገባ ከተጠናቀቀ በኋላ ድንገት ትምህርት ቤቱ ይፈርሳል የሚለው ዜና እንደደረሳቸው አመልክተዋል፡፡

ከ1300 በላይ ተማሪዎች ያሉት እና ለ20 ዓመታት የቆየው ትምሕርት ቤት ይፈርሳል ተብሏል
ከ1300 በላይ ተማሪዎች ያሉት እና ለ20 ዓመታት የቆየው ትምሕርት ቤት ይፈርሳል ተብሏልምስል Seyoum Getu/DW

የአዲስ አበባ የፒያሳው የአራዳ ሕንፃ ሱቆች መፍረስ የተማሪ ወላጁ በአስተያየታቸው "እንደውም በመጀመሪያ በትምህርት ቤቱ ከፍተኛ የሆነ የ150 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎብን ብትምህርት ቤቱና በወላጆች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት የቦሌ ክፍለ ከተማ ትምህርት መምሪያ ጣልቃ ገብቶ ጭማሪው ወደ 65 በመቶ ዝቅ እንዲልልን የበኩሉን አስተዋጽኦ ካበረከተና ምዝገባውን አጠናቀን ለትምህርት ዘመኑ ዝግጅት ካደረግን በኋላ ነው ትምህርት ቤቱ ፈርሳል የተባልነው” ብለዋል፡፡ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ውስጥ የሚገኘው ትምህርት ቤቱ እንደሚፈርስ የተነገረም ምዝገባው በተጠናቀቀበት በሶስት ቀናት ውስጥ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪው የተማሮዎች ወላጆች ከመንግስት የሚመለከታቸው አካላትና ከትምህርት ቤቱ አስተዳደር ጋር የተደረገው ውይይትም ምፍትሄ አልባ ሆኗል ብለዋል፡፡

የውሳኔው ዘግይቶ መምጣት

ወላጆቹ ትምህርት ቤቶች ምዝገባ በጨረሱበት ትምህርት ቤቱን የማፍረስ ውሳኔ መተላለፉ  በቀጣይ በትምህርት ቤቱ ከመዋእለ ህጻናት እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ከ1300 በላይ ተማሪዎች እድል ላይ መወሰን ነው ሲሉም አማረው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሌላም አስተያየት ሰጪ ወላጅ በቅሬታቸው፤ "መንግስት እስከ ሐምሌ 15 ቀን ምዝገባ ይጠናቀቅ ባለው መሰረት ልጆቻችንን አስመዝግበን ዩኒፎርም አሰፍተን ዝግጅት አጠናቀናል፡፡ አስቀድሞ ብነገረን አስፈላጊውን ዝግጅት እናደርግ ነበርም” ብለዋል፡፡

መንግስት እስከ ሐምሌ 15 ቀን ምዝገባ ይጠናቀቅ ባለው መሰረት ልጆቻችንን አስመዝግበን ዩኒፎርም አሰፍተን ዝግጅት አጠናቀናል
መንግስት እስከ ሐምሌ 15 ቀን ምዝገባ ይጠናቀቅ ባለው መሰረት ልጆቻችንን አስመዝግበን ዩኒፎርም አሰፍተን ዝግጅት አጠናቀናል ። ወላጆችምስል Seyoum Getu/DW

ወላጆቹ በየመዋቅሩ ካሉት ከመንግስት አካላት ጋር ባደረጉት ውይይትም የተሰጣቸው መፍትሄ ተማሪዎቹን በተለያዩ ትምህርት ቤት መበተን ብቻ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡  "ልጆቻቸውን በፈለጋችሁ ትምህርት ቤት ማስመዝገብ ትችላላችሁ የሚል የምፍትሄ አቅጣጫ ነው የተሰጠን” ያሉት እንደኛው አስተያየት ሰጪ ወላጅ አሁንም ድረስ እስከ ከተማው ከንቲባ በመሄድ ቅሬታቸውን ለማመልከት እየጣሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሌሎች አማራጭ ትምህርት ቤቶች መሙላት

ሌላው አስተያየት ሰጪ ወለጅ ደግሞ እንደ መፍትሄ የቀረበውን በሌሎች ትምህርት ቤቶች ልጆቻቸውን ለማስመዝገብ ብጠሩም ትምርት ቤቶች ቦታ የለም ሞልቷል የሚል ምላሽ እንደሰጡአቸው አስረድተዋል፡፡ "የመንግስት አካላት እንደ መፍትሄ የሰጡን ተማሪዎቻችሁን ወደ ሌሎች ትምህርት ቤቶች መበተንና ማስመዝገብ ነው ውሳኔው አይቀለበስም የሚል ነው፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ዞረን ምዝገባ በመጠናቀቁ ቦታ የለንም ሞልቷል የሚል ምላሽ እተሰተን አስጨንቆናል” ነው ያሉት፡፡

ማንነታቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የትምህርት ቤቱ መምህርም ከ200 በላይ የትምህርት ቤቱ ሰራተኞች እጣም አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

ዶይቼ ቬለ ስለጉዳዩ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ለቦሌ ክፍለ ከተማ ትምህርት መምሪያኃላፊ አቶ መስፈን ታደሰ እንዲሁም ለአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡ 

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ