1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአዲሱ የጉጂ አባገዳ የተላለፈው የሰላም ጥሪ

ሐሙስ፣ የካቲት 14 2016

በተለያዩ አካባቢዎች የደፈረሰ ሰላም ጠርቶ የጥይት ድምጽ የማይሰማበት ዘመን እንዲመጣ ማገዝን ቀዳሚ ሥራቸው እንደሚደርጉ አዲሱ የጉጂ አባገዳ አስታወቁ። ትናንት በተጠናቀቀው የገዳ ሥርዓት የሥልጣን ሽግግር 75ኛው የጉጂ አባገዳ ሆነው የተመረጡት አባገዳ ጃርሶ ዱጎ፤ በሥልጣን ዘመናቸው ከሰላም በፊት ትኩረት የሚሰጡት ጉዳይ አለመኖሩንም አስረድተዋል።

https://p.dw.com/p/4ckwb
የጉጂ የሀገር ሽማግሌዎች
የጉጂ የሀገር ሽማግሌዎችምስል Seyoum Getu/DW

የጉጂ አባዳ

የጉጂ አባገዳ የሥልጣን ሽግግር

የጉጂ ገዳ ስርዓት የሥልጣን ርክክብ በተለያዩ የሥልጣን ሽግግሩ ሂደቶች ለወራት ዝግጅት እና በርካታ ስነሥርዓቶች ሲከወኑ ቆይተው በትናንትናው ዕለት ሜኤ ቦኩ በተባለች የጂላ ስርኣት ስፍራ 74ኛው የጉጂ አባገዳ ጂሎ ማንኦ ለአዲሱ 75ኛው የጉጂ አባገዳጃርሶ ዱጎ ሥልጣኑን አስተላልፈዋል። የገዳ ሥርዓት ፍጹም ዴሞክራሲያዊነት ማሳያ የሚባልለት መሰል በየስምንት ዓመቱ ሥልጣን የሚሸጋገርበት ሂደትም በሰፊው መከወን የሚገባቸው የውይይት እና የሥርዓቱ ሂደቶች ከተፈጸሙ በኋላ ነው ተብሏል።

ትናንት 75ኛው የጉጂ አባገዳበመሆን ለቀጣይ ስምንት ዓመታት ኃላፊነቱን የተረከቡት ጃርሶ ዱጎ በሥልጣን ዘመናቸው መጀመሪያ ሥራቸው አድርገው የሚያተኩረበት አሁን የጠፋውን ሰላም መመለስ የሚቻልበት መንገድ ላይ ነው ብለዋል።

የአዲሱ አባገዳ የሰላም ጥሪ

«ለተሰጠኝ ኃላፊነት ደስተኛ ነኝ። ከገዳ ሥልጣኑ ጎን ለጎን የተሰጠኝ ኃላፊነት ቀላል አይደለም። ገዳ ደግሞ ሰላም ነው። ከችግር እና መከራ መውጫ መንገድም ጭምር። ባለፈው የገዳ ሃርሙፋ የሥልጣን ዘመን ቀዳዳዎች ነበሩ። ሰው መግባባት ተሳነው። ሰው ተቀምጦ ማረስ ህይወቱን መምራት አለበት። ለዚህ ደግሞ ሰላም መሰረት ነው። ሰላም ማስፈን ከቻልን ጉጂ በሰላም ያድራል። ኦሮሞ ሁሉ ሰላም ይሆናል። የተሰጠንን ኃላፊነት ይዘን ይህን ህዝብ ማስተዳደር እንዲቻለን በሰላም ላይ ነው በአጽንኦት መሥራት ያለብን» ብለዋል።

የጉጂ የሀገር ሽማግሌዎች
የጉጂ የሀገር ሽማግሌዎችምስል Seyoum Getu/DW

አሁን የደፈረሰው ሰላም መርጋት አለበት ያሉት አዲሱ የጉጂ አባገዳ ለዚህም ምክክር እንደሚያስፈልግ ነው የጠቆሙት። «ሰላም መውረድ አለበት። ተመካክረን ሰላም ማምጣት የግድ ነው። ጦርነት መልካም ነገር አይደለም። ሰው በእሳት አይተዳደርም። ተደማምጠን ይህን ገዳ ሮባሌን የጥጋብና የሰላም ማድረግ አለብን። በዚህ ሥርዓታችን ላይ ከተለያየ አካባቢ ለመጣ የኦሮሞ ህዝብ እንኳ እንደ ምሳሌ ብንወስድ ሰላም የሆነው እርስ በርሳችን በመደማመጣችን ነው። በዚህ ገዳ አገዛዝ ውስጥ ምንም አይነት የጥይት ድምጽ እንዳይሰማ ገዳ ጦርነት ሳይሆን ሰላም ያውጃል» ብለዋልም።

 

የገዳ ሥርዓት መከወና ስፍራውን የማልማት ውጥን

የዘንድሮው የጉጂ ኦሮሞ የገዳ ሥርዓቱ የሥልጣን ሽግግር ከወትሮ ለየት ባለና ደማቅ በሚባል ስርዓት ነው የተከናወነው። የሥልጣን መሸጋገሪያ እና የስርዓቱ መከወኛ ስፍራ ሜኤ ቦኮም በትናንቱ ሥነ ሥርዓት ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ተሳታፊዎች ተጨናንቆ ነው የተስተዋለው። ከወትሮ በተለየ የክልሉ መንግሥትም ለሥርዓቱ ትኩረት ሰጥቶ ሥነ ሥርኣቱ እንዲደምቅ አስተዋጽኦ ስለማድረጉ ተነግሯል።  የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ትናንት በስፍራው ተገኝተው ሥርዓቱን በተከታተሉበት ወቅት ያረጋገጡትም ይህንኑን ነው።

የጉጂ የሀገር ሽማግሌ
የጉጂ የሀገር ሽማግሌ ምስል Seyoum Getu/DW

«የገዳ ሥርዓት ህዝባችን ዛሬም ድረስ እየተዳደረበት ያለው ሥርዓት መሆኑን ነው የተመለከትነው። ገዳ ከዴሞክራሲም በላይ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያለው የሁሉም ተፈጥሮ ሕግ ያለው ነው። ይህን ሥርዓት ሰፊ ጭቆናን ተቋቁማችሁ እዚህ ላደረሳችሁ ምስጋና ይገባችኋል። ይህን ትልቅ ሥርዓት የምንከውንበትን ስፍራ ማልማት አለብን። ለቀጣዩ 76ኛ የሥልጣን ሽግግር የጉጂ ባህል የሚጎላበት ማዕከል እንደምንገነባ በዚሁ ቃል መግባት እፈልጋለሁ። ይህን በየስምንት ዓመቱ እየመጣን ብቻ የምንታይበት ሳይሆን ጎብኚዎች መጥተው ጥናትና ምርምር ጭምር የሚደረግበት እንዲሆን እንፈልጋለን» ብለዋል። የገዳ ስርዓት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በቅርስነት ከተመዘገቡ የኢትዮጵያ መስህቦች አንዱ በመሆን ይታወቃል።

 ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ