1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአንድ ቀን 500 ሚሊየን ችግኝ ተከላ

ሰኞ፣ ሐምሌ 10 2015

በኢትዮጵያ በአንድ ቀን 500 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ያለመ ዘመቻ ዛሬ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሲካሄድ ውሏል።

https://p.dw.com/p/4U0Qx
Äthiopien Pflanzung von 500 Millionen Setzlingen
ምስል Shewangizaw wegayoh/DW

የችግኝ ተከላ ዘመቻ

በኢትዮጵያ በአንድ ቀን 500 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል ዘመቻ ዛሬ በተለያዩ ክልሎች ሲካሄድ ውሏል። የዚሁ ዘመቻ አካል በሆነው በሲዳማ ክልልም 25 ሚሊየን ችግኝ የመትከል መርሃ ግብር ከማለዳው ጀምሮ ሲከናወን ነው የዋለው። በሀዋሳ ከተማ በሚገኘው የሚሊኒየም መናፈሻ በተካሄደው የችግኝ ተከላ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ በርከት ያሉ የኅብረሰብ ክፍሎች ተሳትፈውበታል። የችግኝ ተከላው ቀደም ሲል የተመናመኑ የደን ሀብቶችን መልሶ ለመተካት ያስችላል የሚል እምነት እንዳላቸው የተናገሩት የመረሃ ግብሩ ተሳታፊዎች አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ችግኞችን በመትከል በዘመቻው መሳተፋቸውን ለዶቼ ቬለ DW ገልጸዋል።

አቶ ዘላለም ታደለ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶ ገነት የደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ የደን ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ናቸው።  አቶ ዘላለም መንግሥት አረንጓዴ አሻራ በሚል ከአራት ዓመታት በፊት የጀመረው የችግኝ ተከላ ዘመቻ በዝናብ ላይ ጥገኛ የሆነ የእርሻ ኢኮኖሚ ላላት ኢትዮጵያ አማራጭ የሌለው  እርምጃ  እንደሆነ ይናገራሉ። አሁን ተተክለዋል የተባሉ ችግኞችን አሃዛዊ መረጃ በሚመለከት ጥርጣሬ እንዳላቸው የጠቀሱት የደን ሳይንስ መምህርና ተመራማሪው ቁጥሩን ተአማኒነት ባለው ቀመር ማረጋገጥ እስካልተቻለ ድረስ ትንሽ የተጋነነ መስሎ ይሰማኛል ብለዋል።

Äthiopien Pflanzung von 500 Millionen Setzlingen
ምስል Shewangizaw wegayoh/DW

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከአገሪቱ ከግማሽ በላይ የሚሆነው መሬት በተለያዩ ደረጃዎች ጉዳት የደረሰበት ነው የሚሉት አቶ ዘላለም «ይህን ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚደረገው መነሳሳት የሚበረታታ ነው። ግን ተተክለዋል የተባሉት ችግኞች አሃዝ ትንሽ የተጋነነ ይመስላል። ምክንያቱም ካለው የአንድ ቀን ጊዜ አንጻርና ይህን ያህል መጠን ያለው ችግኝ ማዘጋጀት ይቻላል ወይ የሚለው አከራካሪ ሊሆን ይችላል። ግን ደግሞ ሁሉም ልክ አይደለም ማለት አይደለም። ህዝቡን በማነሳሳት የተጀመረው ዘመቻም በጎ አስተዋጽኦዎ ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ» ብለዋል።

መንግሥት በየዓመቱ በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ደኖችን ለማልማት የሚያደርገው ጥረት አሳሳቢ እየሆነ የሚገኘውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው የጠቀሱት የደን ሳይንስ መምህርና ተመራማሪው «ከችግኝ ተከላው ጋር በተያያዘ ምን አይነት ችግኞች ለምን አይነት ዓላማ እንደምንተክል ግንዛቤው ሊኖረን ይገባል። ለዚህ ደግሞ የዘመቻ ንቅናቄው እንዳለ የደን ሳይንሳዊ ዘዴዎችን ጥቅም ላይ መዋል ይኖርባቸዋል» ብለዋል።

 ሸዋንግዛው ወጋየሁ 

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር