1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

በአሜሪካ የምክትል ፕሬዚዳንቷን ፕሬዚዳንታዊ ሽግግር ለመምራት የተሾሙት አምባሳደር ዮሐንስ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 22 2016

አምባሳደር ዮሐንስ አብርሃም፣ ለዴሞክራቲክ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ካማላ ሃሪስ የታቀደውን የፕሬዚዳንታዊ ሽግግር እንዲመሩ መመረጣቸው ተገለጸ። በቨርጂኒያ ግዛት ከኢትዮጵያውያን ወላጆች የተወለዱት አምባሳደር ዮሐንስ፣ ከዚህ ቀደም የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን በመሆን በተለያዩ ኃላፊነቶች ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

https://p.dw.com/p/4k0yr
ነጩ ቤተመንግሥት
ዋሽንግተን ዲሲ የአሜሪካ ነጬ ቤተመንግሥት ፎቶ ከማኅደርምስል Olin Dozier/NurPhoto/picture alliance

በአሜሪካ የምክትል ፕሬዚዳንቷን ፕሬዚዳንታዊ ሽግግር ለመምራት የተሾሙት አምባሳደር ዮሐንስ አብርሃም

የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባል የሆኑት ዮሐንስ አብርሃም፣ በአሁኑ ወቅት፣ በደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች ማኀበር በምህፃረ ቃሉ Asean የአሜሪካ አምባሳደር ሲሆኑ፣ መቀመጫቸው ኢንዶኔዥያ ጃካርታ ነው።

የትምህርት ዝግጅት ኃላፊነት

አምባሳደሩ በትምህር ዝግጅታቸው በሃርቫርድና ዬል ዩኒቨርሲቲዎች፣ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪ ማግኘታቸው ታውቋል። ቀደም ሲል በፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን አስተዳደር፣ በብሔራዊ ደህንነት አስተዳደር ምክር ቤት በዋና ጸሐፊነት፣ እንዲሁም የባይድን ፕሬዚደንታዊ ሽግግር ዋና ዳይሬክተር በመሆንም አገልግለዋል።

በባራክ ኦባማ አስተዳደር ወቅትም፣ በነጩ ቤተመንግሥት የሕዝብ ተሳትፎና በይነ መንግሥታት ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የመካከለኛ ደረጃ ሠራተኛ የነበሩት አምባሳደር ዮሐንስ፣ የኦባማ ከፍተኛ አማካሪ ቫለሪ ጃኔት ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ኃላፊም ነበሩ።

የሽግግር ቡድን መሪ

እኚሁ የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ በአዲሱ ሹመታቸው፣ የምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ ፕሬዚደንታዊ የሽግግር ዕቅድ ቡድናቸውን ይመራሉ። አምባሳደር አብረሃም በአዲሱ የሥራ ቦታቸው፣ ከፌደራል መንግሥቱ የተለያዩ ኤጀንሲዎች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር የሚሠሩ ሲሆን፣ ካማላ ሃሪስ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን ካሸነፉ ተግባራዊ የሚሆነውን የሠራተኞችና የፖሊሲ እቅዶችን ሂደት ይመራሉ ተብሏል።

ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው ብሔራዊ የፕሬስ ክለብ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ መስፍን መኮንን፣የአምባሳደር ዮሐንስ ሹመት ትልቅ ትርጉም እንዳለው ለዶይቸ ቨለ በሰጡት አስተያየት አመልክተዋል።

«ነገሩ ጥሩ ነው በኢትዮጵያዊነት እንደዚህ ዓይነት ደረጃ ላይ ተቀምጦ፣ የአስተዳደሩን የተለያየ ክፍል ለመርዳትና ለማዋቀር እዚህ ላይ በመሳተፉ በጣም ትልቅ ነገር ነው በኢትዮጵያዊነት።»

እንደ ጎርጎርዮሳውያኑ ጊዜ አቆጣጠር በ 2002 አምባሳደር ዮሐንስ፣ የባይደን ሽግግር ቡድን ዳይሬክተር በነበሩበት ጊዜ፣ ከምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ ጋር በቅርብ ይሠሩ ነበር ብሏል ኤንቢሲ በዘገባው።

ካማላ ሃሪስ በቺካጎ
ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሃሪስ በቺካጎ ምስል Mike Blake/REUTERS

ከምርጫ ዘመቻ ወደ አስተዳደር ዕቅድ

በነጩ ቤተመንግሥት የኤንቢሲ ዘጋቢ አሮን ጊልክረስት እንደሚለው፣ የሃሪስ የምርጫ ቡድን አሁን ዮሐንስ አብርሃምን መሾሙ፣ የምርጫ ዘመቻቸው ከቅስቀሳ ወደ ተጨባጭ ሀገር ማስተዳደር የሚያካሂደው ሂደት አካል ነው።

አሜሪካ በደቡብ ምሥራቅ እስያ ከሚገኙ ሃገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር፣ ለሁለት ዓመታት ያህል በኢንዶኔዥያ የቆዩት አምባሳደር አብርሃም ፣በሚቀጥሉት ቀናት በጃካርታ የነበራቸውን የሥልጣን ዘመን እንደሚያጠናቀቁ አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን አረጋግጠዋል።

ታሪኩ ኃይሉ

ሸዋየ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ