1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ጉዳት አደረሰ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 16 2016

በአማራ ክልል ሁለት ዞኖች ጎርፍና የመሬት መንሸራተት በሰብልና በመኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ማድረሱን የየዞኖቹ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤቶች አስታውቀዋል፡፡ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በ8 ወረዳዎች የመሬት መንሸራት ሲከሰት በዚሁ ዞን በ4 ወራዳዎች ደግሞ ጎረፍ ጉዳት አድርሷል ።

https://p.dw.com/p/4jms9
Äthiopien | Erdrutsch in der Amhara Region
ምስል North Shewa and Waghemra Communication Departments.

በአማራ ክልል ጎርፍ ያስከተለው የመሬት መንሸራተት በዕጽዋት ላይ ጉዳት አድርሷል

ጎርፍና የመሬት ናዳ በአማራ ክልል
በአማራ ክልል ሁለት ዞኖች ጎርፍና የመሬት መንሸራተት በሰብልና በመኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ማድረሱን የየዞኖቹ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤቶች አስታውቀዋል፡፡ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በ8 ወረዳዎች የመሬት መንሸራት ሲከሰት በዚሁ ዞን በ4 ወራዳዎች ደግሞ ጎረፍ ጉዳት አድርሷል ተብሏል፡፡

ለጎፋ የአደጋ ሰለባ ቤተሰቦች የሚደረገው የርዳታ ሁኔታ
የዘንድሮ የዝናብ ሁኔታ
በዚህ ዓመት እየጣለ ያለውን ከፍተኛ ዝናብ ተከትሎ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ጎርፍና የመሬት ናዳ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ ይህ የተጥሮ አደጋ ካጠቃቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ የአማራ ክልል መሆኑን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ፕሮግራሞች ኮሚሽን ኃላፊ ዲያቆን ተስፋው ባታብል ተናግረዋል፣ የአየር ትንበያ ባለሙያዎችን ጠቅሰው ኃላፊው እንዳሉት፣ በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ወሎ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በምዕራብ ጎጃም፣ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደርና በሌሎችም አንዳንድ አካባቢዎች ጎርፍና ናዳ የሚያስከትል ዝናብ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ይኖራል፡፡

ዝናብና ጎርፍ በሰሜን ሸዋ ያስከተለው ጉዳት
ጎርፍ በሰሜን ሸዋ ያደረሰው ጉዳት
በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን በ4 ወረዳዎች ጎርፍ፣ በ8 ወረዳዎች ደግሞ የተለያየ መጠን ያላቸው የመሬት መንሸራተት አደጋዎች እንደደረሰባቸው የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት መምሪያ ኃላፊ አቶ አበባው መለስ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡ በጎርፍ ከፍተኛ አደጋ የደረሰባቸው ወረዳዎች ቀወት፣ መንዝ ቀያ፣ ኤፍራታና ግድምና  አንፀኪያ ወረዳዎች ናቸው ነው ያሉት፡፡ በነኚህ ወራደዎች በሚገኙ 5 ቀበሌዎች ከፍተኛ መጥለቅለቅ ደርሷል ብለዋል፡፡

ካንድ ቤት 14 የገደለው መሬት መንሸራተት

በ113 ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ሰብል በሙሉ መውደሙን፣ 7 መኖሪያ ቤቶች በጎርፍ መጥለቅለቃቸውን፣ ቁጥራቸው ያልታወቁ እንስሳት መሞታቸውን፣ ግምቱ 3 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ለተክል የተዘጋጀ  የሽንኩርት ፍል ከጥቅም ውጪ መሆኑንና  ከ640 በላይ  አባዎራዎችም  በጎርፉ ቀጥተኛ ጉዳት የደረሰባቸው እንደሆኑ ነው አቶ አበባው ያስረዱት፡፡         
ከዚህ ቀደም ሲል ከ7 ሚሊዠዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የጎርፍ መቀልበሻ ቦይ ተገንብቶ የነበረቢ ሆንም በሚጥለው ከባድ ዝናብ ምክንያት የተገነባው መቀልበሻ ጎርፉን መከላከል ባለመቻሉ በዚህ ሳምንት ብቻ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ተጨማሪ ስራዎችን መስራት ቢቻልም ጎርፉ ከአቅም በላይ በመሆኑ ጉዳት ማስከተሉን አመልክተዋል፡፡ አሁንም ቢሆን በነኚህ 4 ወረዳዎች በሚገኙ 15 ቀበሌዎች የሚኖሩ ከ19ሺህ በላይ ነዋሪዎች በጎርፍ ስጋት ላይ ናቸው ነው ያሉት፡፡

የመሬት መንሸራተት አደጋ በሰሜን ሸዋ ጉዳት አድርሷል
በጎርፍ ከፍተኛ አደጋ የደረሰባቸው ወረዳዎች ቀወት፣ መንዝ ቀያ፣ ኤፍራታና ግድምና  አንፀኪያ ወረዳዎች ናቸውምስል North Shewa and Waghemra Communication Departments.

የመሬት መንሸራረት መንስኤና መፍትሄው
ናዳ በሰሜን ሸዋ ያደረሰው ጉዳት
በ8 ወረዳዎች የተከሰተው የመሬት መንሸራተት ደግሞ ሌለው ክስተት እንደሆነ አቶ አበባው አስረድታል፡፡  በቀወት፣ በመንዝ ማማ፣  በመንዝ ቀያ፣ በአንኮበር፣ በኤፍራታና ግድም፣ በአንጎለላና ጣራ፣ በባሶና በጣርማ በር ወረዳዎች ካለፉት  10 ቀናት ጀምሮ እየጣለ ባለው ዝናብ ምክንያት ደረጃቸው ተለያየ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ተከስተዋል፡፡ በዚህም ከ264 ሄክታር ማሳ ላይ የነበረ ሰብል ወድሟል፣ 166 ቤቶች ፈርሰዋል፣  5 ሄክተር የግጦሽ መሬት፣ የውሀ ተቋማትና መንገዶች ለብልሽት መዳረጋቸውን አብራርተዋል፡፡
በመሬት መንሸራተት አደጋ ስለደረሰባቸውን ሰዎች የተጠቃለለ መረጃ ለማግኘት ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት እንዳልተቻለ አመልክተው  በኤፍራታና ጣምራ በር ወረዳዎች ግን 218 የቤተሰብ አባወራዎች በከፍተኛ ችግር ላይ እንደሆኑ መረጋገጡን አስረድተዋል፡፡

በመገባደድ ላይ ባለው በ2016 ዓም የክረምቱ ዝናብ ባስከተለው የተፍጥሮ አደጋ ከ275 ሰዎች ሞተዋል
ጎርፍና ናዳ በዋግኽምራ ያደረሰው ጉዳት
በተመሳሳይ ዜና በዚሁ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ባለፉት 3 ቀናት የጣለው ከባድ ዝንብ  ባስከተለው ናዳ ዳህና ወረዳን ከሰቆጣ የሚያገናኘው ዋና ጎዳና በናዳ ምክንያት አገልግሎት ማቋረጡንና በሰብልና መኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ማድረሱን የብሔረሰብ አስተዳደሩ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት መምሪያ ኃላፊ አቶ ምህረት መላኩ አመልክተዋል፡፡
በሰዎች ላይ እስካሁን የሞት ጉዳት እንዳልደረሰ ያመለከቱት አቶ ምህረት፣ 80 እንስሳት በናዳው ሞተዋል ነው ያሉት፣ 93 ሰዎች ደግሞ ከአካባቢው እንዲለቅቁ መደረጋቸውንና 14 ቤቶች ደግሞ በናዳው መፈራረሳቸውን ገልጠዋል፣ እንደ አቶ ምህረት በ2700 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ ሰብል ወድሟል፡፡፡

የጎፋው ዘግናኝ የተፈጥሮ አደጋ
የአየር ትንበያ ማስጠንቀቂያ
በኢትዮጵያ ባለፈው የሰኔ እና የሐምሌ ወራት አስቀድሞ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ሲጥልባቸው በነበሩ የደቡብ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ፣ የኦሮሚያ ፣  የሲዳማ  እና የአማራ ክልሎች  የመሬት መንሸራተት አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ተቋም በቅርቡ ለዶቼ ቬሌ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል ፡፡ በእነኝህ አካባቢዎች እስከ መጪው መስከረም ወራት ከመደበኛ በላይ ዝናብ ስለሚኖር ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲደረግ ተቋሙ ማሳሰቡ ይታወቃል ፡፡
ዓለምነው መኮንን
ታምራት ዲንሳ 
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር