በአማራ እና ትግራይ ክልሎች ድርቅ ያስከተለው ጉዳት
ማክሰኞ፣ ጥር 21 2016
በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የሰዎችን እና እንስሳትን ሕይወት እየቀጠፈ ያለው ችግር ድርቅ ወይም ረሃብ መሆኑ ላይ የብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ምክር ቤት ብያኔ እንዲሰጥ ተጠየቀ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም በሁለቱ ክልሎች የተከሰተውን ድርቅ አስመልከቶ በድርቁ የደረሰውን ሰብአዊ ጉዳት እና ለተጎጂዎች እየተደረገ ያለው ምላሽ ላይ ጥናት አድርጓል።
በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በትግራይ ክልል 351 ሰዎች መሞታቸውን፣ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን 21 ሰዎች በረሃብ ምክንያት መሞታቸውን እና በዚሁ ዞን በአልሚ ምግብ እጥረት ሳቢያ 23 ሕፃናት ሞተው መወለዳቸውንም ተቋሙ አመልክቷል። «በድርቁ ምክንያት ከ4 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርት አቋርጠዋል»
ድርቁ በትግራይ ክልል 15 ሺህ 565 ሰዎችን አፈናቅሏል ያለው የእምባ ጠባቂ የባለሙያዎች ቡድን በአማራ ክልል በጦርነት ምክንያት በቦታው ተገኝቶ መመርመር ባይችልም በስልክ ተደርጓል ባለው ማጣራት ድርቁ 31 ሺህ ሰዎችን ማፈናቀሉን አስታውቋል።
ግኝቱ ምን ያሳያል ?
የኢትዮጵያ ሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም በአማራ ክልል በዘጠኝ ዞኖች በሚገኙ 43 ወረዳዎች ውስጥ 1.8 ሚሊዮን ዜጎች የድርቅ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸውን ፣ በትግራይ ክልል ደግሞ በ አምስት ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 35 ወረዳዎች የክልሉ መንግሥት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ጨምሮ 4.2 ሚሊየን ዜጎች የድርቅ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸውን መግለጹን ሆኖም የፌዴራል መንግሥቱ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ጨምሮ 2.2 ሚሊዮን ዜጎች የድርቅ ተጎጂ መሆናቸውን እንደሚገልጽና የመረጃ ክፍተት መኖሩን ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። ይህ የቁጥር ልዩነት ለተጎጂዎች ተገቢ እርዳታ ለማቅረብ እንቅፋት ከመሆኑ ባሻገር የተከሰተው ችግር ድርቅ ነው ወይስ ረሃብ የሚለው በሚመለከተው አካል ብያኔ አለማግኘቱ የእርዳታ አሰጣጡ ላይ ተጽእኖ እንዳለው ገልፀዋል። በትግራይ ለተከሰተዉ ረሃብ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ተጠየቀ
ድርቁ ምክንያት የሰዎች እና የእንስሳት ሞት ተከስቷል
በሁለቱ ክልሎች በተከሰተው የድርቅ አደጋ ምክንያት ሰዎችም እንስሳትም መሞታቸው ተገልጿል።
በትግራይ ክልል 351 ሰዎች መሞታቸውን እና 15 ሺህ 565 ሰዎች መፈናቀላቸውን ፣ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን 21 ሰዎች በረሃብ ምክንያት መሞታቸውን እና በዚሁ ዞን በአልሚ ምግብ እጥረት ሳቢያ 23 ሕፃናት ሞተው መወለዳቸውንም እንዲሁም ድርቁ 31 ሺህ ሰዎችን ማፈናቀሉን እንባ ጠባቂ አስታውቋል።ፌድራል መንግሥት የኮምዩንኬሽን አገልግሎት የሰጠውን መግለጫ እንዲያርም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጠየቀ
ድርቅ ወደ ረሃብ አልተቀየረም- መንግሥት
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደሩ እስከፊ ረሃብ መከሰቱን አስታውቋል። የብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም ጥር 9 ቀን 2016 ዓ. ም ለሀገር ውስጥ ብዙኃን መገናኛዎች በሰጡት መግለጫ "ድርቁ ወደ ረሃብ እየተቀየረ ነው የሚለው ሀሳብ የተሳሳተ ድምዳሜ ነው" ስለማለታቸው ከተቋሙ ድረገጽ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ሰለሞን ሙጬ
ታምራት ዲንሳ
አዜብ ታደሰ