1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአህጉራዊ የቴክኖሎጅ ውድድር ለፍፃሜ የደረሱት ሁለቱ ሀገር በቀል የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች

ረቡዕ፣ ግንቦት 23 2015

በቅርቡ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በሰባት ምድቦች በተካሄደው የዘንድሮው የምስራቅ አፍሪቃ የቴክኖሎጅ ውድድር ኦሚሽቱ ጆይ የተባለው የቴክኖሎጂ ኩባንያ በአመቱ ምርጥ የጀማሪ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ዘርፍ ለፍፃሜ ሲደርስ ፤አሪፍ ፔይ የተባለው ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያ ደግሞ በገንዘብ ነክ ቴክኖሎጅ/Fintech/ዘርፍ የ2023 አሸናፊ ለመሆን በቅቷል።

https://p.dw.com/p/4S1xx
Äthiopien | Fintech-Innovation des Jahres - Arifpay Financial Technology
ምስል Melka Girma @privat

 
የዘንድሮው የምስራቅ አፍሪቃ የቴክኖሎጅ ውድድር በተለያዩ ዘርፎች አሸናፊዎችን ይፋ አድርጓል።የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅትም  በውድድሩ አሸናፊ  በሆኑ እና ለፍፃሜ በደረሱ  ሁለት ሀገር በቀል ጀማሪ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ ያተኩራል። 
በየዓመቱ በሚዘጋጀው ምስራቅ አፍሪቃ ኮም በተባለው የጀማሪ ቴክኖሎጅዎች ውድድር ለፍፃሜ ከደረሱት መካከል ሁለቱ ከኢትዮጵያ ናቸው። በቅርቡ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በሰባት ምድቦች በተካሄደው በዚህ ውድድር ለፍፃሜ የደረሱት ኦሚሽቱ ጆይ እና አሪፍ ፔይ የተባሉ ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች ሲሆኑ፤ አሪፍ ፔይ  በገንዘብ ነክ ቴክኖሎጅ/Fintech/ዘርፍ ከፍፃሜ አልፎ የ2023 አሸናፊ ለመሆን በቅቷል። የኩባንያው የግብይት እና የሽርክና ዳይሬክተር አቶ መልካ ግርማ እንደሚገልፁት አሪፍፔይ (Arifpay) ዲጂታል የክፍያ ዘዴዎችን ለማቅረብ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የተሰጠው የመጀመሪያው ተቋም ሲሆን፤ይህ የቴክኖሎጅ ኩባንያ በዘርፉ ከተወዳደሩት መካከል እንዲመረጥ ያደረገውም  በዘርፉ ለማህበረሰቡ ሊያበረክት የሚችለውን አስተዋፅኦ ታሳቢ በማድረግ ነው።
ታህሳስ  2015 ዓ/ም በይፋ ሥራ የጀመረው አሪፍፔይ /Arifpay/ የቴክኖሎጂ ኩባንያ፤  በሁለት መንገድ የክፍያ ስርዓቱን ለማዘመን ይሰራል።በአንድ በኩል  ዲጅታል የክፍያ ማሽኖችን ወይም Arif POS/Point of Sale / ለተጠቃሚዎች በማቅረብ በሌላ በኩል በበይነመረብ ክፍያ መፈፀም የሚያስችል «አሪፍ ጌት ወይ»/Arif Gateway/  የተባለ ዲጅታል መድረክ አዘጋጅቷል።ለዚህ ዲጅታል የክፍያ ዘዴ መነሻው አቶ መልካ እንደሚሉት በዘርፉ የሚታየው ክፍተት ነው።
አቶ መልካ እንደሚሉት ዲጅታል የክፍያ ማሽኖች ወይም/Arif Point of Sale/ ለተጠቃሚዎች የሚቀርቡት  በተለያዩ የንግድ ቦታዎች በማስቀመጥ ሲሆን፤ይህም ሰዎች በአካል በመሄድ ያለ ጥሬ ገንዘብ በካርድ ብቻ ክፍያ እንዲፈፅሙ የሚያደርግ ነው። 
ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ተገንብቶ ለኢትዮጵያውያን መቅረቡ የተገለፀው የአሪፍፔይ /Arifpay/ በበይነመረብ ዲጂታል የክፍያ ዘዴው ደግሞ ደንበኞች የባንክ ካርዶቻቸውን በመጠቀም ያለ ጥሬ ገንዘብ ዲጅታል በሆነ መንገድ ባሉበት ሆነው  ደህንነቱ የተጠበቀ ግብይት እንዲፈፅሙ ያስችላል።ለዚህም የሁሉንም ባንኮች  የዴቪት ካርዶች ወይም በተለምዶ የ ATM  የሚባሉትን ካርዶች ለመጠቀም ዕድል ይሰጣል።ይህም ጥሬ ገንዘብ በማውጣት ብቻ  የታጠረውን የካርዶቹን አገልግሎት ክፍያ እና ግብይትን ወደ መፈፀም ያሳድጋል። 
በዚህ መልኩ ይህ ዲጂታል መፍትሄ ተጠቃሚዎች ፈጣን እና ቀላል የግብይት አገልግሎቶችን በአነስተኛ  ዋጋ እንዲያገኙ በማድረግ፤ ጤናማ የገንዘብ ፍሰት ለመፍጠር ፣ቁጠባን ለማሳደግ፣ ድህነትን ለመቀነስ እንዲሁም ሥራ ፈጣሪነትንና የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትን ለማሳደግ ሀላፊው እንደሚሉት የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል።
በሌላ በኩል በግብርና ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚሰራው ኦሚሽቱ ጆይ በመባል የሚጠራው ጀማሪ  የቴክኖሎጅ ኩባንያ ፤በዘንድሮው የምስራቅ አፍሪቃ የቴክኖሎጅ ውድድር  የዓመቱ ምርጥ የቴክኖሎጅ ኩባንያ ዘርፍ  የመጨረሻ ዕጩ በመሆን ለፍፃሜ  የደረሰ የቴክኖሎጅ ኩባንያ ነው።ምንም እንኳ በውድድሩ አሸናፊ ባይሆንም የኩባንያው  ምክትል ማኔጅግ ዳይሬክተር አቶ ጥጋቡ አብርሃም እንደሚሉት ለመጨረሻ ዙር መድረሳቸው  የበለጠ እንዲሰሩ መነሳሳትን የሚፈጥር ነው።
ይህ ኩባንያ ከዚህ ቀደም  ግሎባል ኢንዴክስ ኢንሹራንስ ፋሲሊቲ (GIIF) በተሰኘው የዓለም ባንክ መርሃ ግብር የ2022 አሸናፊ የነበረ ሲሆን፤ ለሽልማት ያበቃውም በግብርና ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል የአፈር መመርመሪያ መሳሪያ /Device/ በመስራቱ ነው።ይህ መሳሪያ  የአንድን የእርሻ መሬት አሲዳማነት፣የንጥረ ነገር ይዘት፣ የእርጥበት እና የሙቀት መጠን በተመለካት መሬቱ  ለየትኞቹ አዝርዕቶች ተስማሚ ነው የሚለውን በመለየት፤ የደረሰበትን ውጤት  በስማርት ስልኮች አማካኝነት በጥቂት ደቂቃዎች ወደ ተገልጋዩ ይልካል።
አቶ ጥጋቡ እንደሚሉት ቴክኖሎጂው በዚህ ሁኔታ  የገበሬውን  የማዳበሪያ አጠቃቀም ለመመጠን እንዲሁም ተስማሚውን የማዳበሪያ አይነት ለመምረጥ ዕድል ይሰጣል። ይህም የገበሬውን  የማዳበሪያ አጠቃቀም በማዘመን  የእርሻ ምርቶችን ከጉዳት በመታደግ  ምርታማነትን ያሳድጋል።
አቶ አማኑኤል ጌታሁን ይህንን ቴክኖሎጅ ከሚጠቀሙት መካከል አንዱ ናቸው።እሳቸው እንደሚሉት ላለፉት ስምንት ወራት በቀድሞው በአዲስ አበባ ዙሪያ በአሁኑ ሸገር ከተማ ቡራዩ አካባቢ ለሚያካሂዱት የከተማ ግብርና ቴክኖሎጂውን ተጠቅመው በስራቸው ለውጥ አይተውበታል።
እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ሀገራት የሰዎችን ኑሮ ለማሻሻል ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች የሚጫወቱት ሚና ቀላል አይደለም።ከዚህ አንፃር አሪፍ ፔይም ሆነ ኦሚሽቱ ጆይ ለህብረተሰቡ የሚሰጡት አገልግሎት የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል። 
ያም ሆኖ ዲጅታል ቴክኖለጅዎችን ለማስፋፋት የበይነመረብ ተደራሽነት ማነስ እና መቆራረጥ እንዲሁም በዋጋ ደረጃ ክፍያው ከፍተኛ መሆን በሌላ በኩል አገልግሎቱን ለመጠቀም የዲጅታል ክህሎት ማነስ በኢትዮጵያ ተግዳሮቶች ናቸው።
ነገር ግን ከነባሩ የቴሌኮም አገልግሎት ውጭ በዘርፉ ሌሎች የቴሌኮም አቅራቢዎች እንዲሳተፉ የማድረጉ ጅምር አሪፍ ፔይም ሆነ ኦሚሽቱ ጆይን የመሳሰሉ አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት እድል የሚፈጥር መሆኑን ባለሙያዎቹ ገልፀዋል።
 

Äthiopien Co founder und CEO of Omishtu-joy Tigabu Abrham
ምስል Privat
Äthiopien | Omishtu-joy Startup gewinnt Preis in Kenia
ምስል privat
Äthiopien | Fintech-Innovation des Jahres - Arifpay Financial Technology
ምስል Melka Girma @privat
Äthiopien | Fintech-Innovation des Jahres - Arifpay Financial Technology
ምስል Melka Girma @privat

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድጡ።


ፀሀይ ጫኔ

ማንተጋፍቶት ስለሺ