1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኒሻንጉል ክልል ታስረዉ የነበሩ ተቃዋሚዎች ተፈቱ

ዓርብ፣ መጋቢት 8 2015

በፓርቲው ስም ሲንቀሰቃሱ የነበሩ ወደ 3 ሺ የሚደርሱ ታጣቂዎችም ከክልሉ መንግስት ጋር ስምምነት ላይ ከተደረሰ ወዲህ ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸውን የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ግራኝ ጉደታ ተናግረዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4Oqrj
Äthiopien Benishangul Region, Stadt  Metekel
ምስል Negassa Dessakegen/DW

46 የጉህዴን አባላት ተፈቱ፣ ሌሎች እንደታሰሩ ነዉ


በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀሰዉ የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) የክልሉ መንግስት አስሯቸዉ  የነበሩ 46 አባላቱ መፈታታቸውን  አስታወቀ፡፡ በክልሉ ውስጥ በነበረው ግጭት ተጠርጥረዉ አባላቱን ጨምሮ ከታስሩት መካከል የ463ቱ ሰዎች ክስ ተቋርጠዋል ቢባልም እስካሁን አለመፈታታቸውን የፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ ግራኝ ጉዴታ ተናግረዋል፡፡ፓርቲዉ ከክልሉ መንግስት ጋር  የዛሬ ስድስት ወር ገደማ  በተፈራረመዉ የሰላም ስምምነት መሰረት የታሰሩ የድርጅቱ አባላት በሙሉ መፈታት ነበረባቸዉ፡

በመተከል ዞን እና ካማሺ ዞን በ2013 ዓ.ም ተከስቶ በነበረው ግጭት ጋር ተያይዞ የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አባላትን ጨምሮ  በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው ሲታይ ቆይተዋል፡፡ በፓርቲው ስም ሲንቀሰቃሱ የነበሩ ወደ 3 ሺ የሚደርሱ ታጣቂዎችም ከክልሉ መንግስት ጋር ስምምነት ላይ ከተደረሰ ወዲህ ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸውን የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ግራኝ ጉደታ ተናግረዋል፡፡ ፓርቲው  በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ከመንግስት ጋር ስምምነት ላይ ከደረሰ ስድስት ወራት ቢያስቆጥርም የታሰሩ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከእስር አለመፈታታቸውን አቶ ግራኝ ጉደታ አመልክተዋል፡፡ በመተከል እና ካማሺ ዞኖች የታሰሩ የድርጀቱ አባላት እስካሁን አለመፈታታቸውን አክለዋል፡፡
በፓርቲው ስም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ፣ በፓርቲው ስም የታሰሩ ሰዎችም እንዲፈቱ በጥቅምት ወር ከክልሉ መንግስት  ጋር በስምምነት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወጣቶች በክልሉ በወርቅ፣በእምነበረድ እና የተለያዩ የስራ ዘርፎችም እንዲሰማሩ እድል እንዲመቻችላቸውም በሰላም ስምምነቱ መጠቀሱን የፓርቲው ሊቀመንበር ተናግረዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀሩን ዑመር በበኩላቸው መንግስትና የፖለቲካ ፓርቲው ስምምነት ላይ ከደረሱ ወዲህ በርካታ የድርጅቱ አባላት መፈታታቸውን ገልጸዋል፡፡ ምን ያህሉ  እንደተፈቱ ግን በቁጥር አልገለጹም፡፡  በህይወት ማጥፋት ወንጀል ተጠርጥሮ ከታሰሩት ውጭ ሰሞኑን ሁሉም እንደሚፈቱ ኮሚሽነሩ አመልክተዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ከ2013 ዓ.ም አንስቶ በተከሰቱት የጸጥታ ችግሮች ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቀለዋል፡፡ በጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ስም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በክልሉ ሁለት ዞኖች ውስጥ በነበረው ግጭት ጉዳት ማድረሳቸው ሲገለጽ ቆይተዋል፡፡ ፓርቲው በወቅቱ ጠቅላላ ጉባኤውን ባለማካሄዱ በምርጫ ቦርድ ተሰዘርዞ  የነበረ ሲሆን ዘንድሮ በምርጫ ቦርድ ዳግም ዕውቅና አግኝተዋል፡፡ 

ነጋሳ ደሳለኝ

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ