1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ ክልል ይቋቋማል የተባለው ጊዜያዊ አስተዳደር ጉዳይ

ሰኞ፣ መጋቢት 4 2015

በትግራይ ይቋቋማል የተባለው ጊዜያዊ አስተዳደር እስካሁን ድረስ እውን ባለመሆኑ የአስተዳደር ክፍተት መፈጠሩ እና ህዝቡ ለችግር መዳረጉ ተገለፀ። ተቃዋሚው ዓረና ትግራይ ፓርቲ በትግራይ ጊዜያዊ የሽግግር አስተዳደር በአፋጣኝ እንዳይቋቋም በማደናቀፍ ህወሓትን ከሷል።

https://p.dw.com/p/4OcSi
Civil society in Tigray, Ethiopia, 18.08.2022
ምስል Million Hailesilassie/DW

«የጊዜያዊ አስተዳደር ምሥረታው እውን አለመሆን»

 

በትግራይ ይቋቋማል የተባለው ጊዜያዊ አስተዳደር እስካሁን ድረስ እውን ባለመሆኑ የአስተዳደር ክፍተት መፈጠሩ እና ህዝቡ ለችግር መዳረጉ ተገለፀ። ተቃዋሚው ዓረና ትግራይ ፓርቲ በትግራይ ጊዜያዊ የሽግግር አስተዳደር በአፋጣኝ እንዳይቋቋም በማደናቀፍ ህወሓትን ከሷል። በፌደራሉ መንግሥት እና ህወሓት መካከል በፕሪቶሪያ ስምምነት ከተደረሰ አራት ወራት ቢያልፉም በስምምነቱ መሠረት በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለመቋቋሙ በትግራይ ክልል የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች የሚገባቸውን ደሞዝ እያገኙ አለመሆኑ፣ ትምህርትን ጨምሮ የተለያዩ የህዝብ አገልግሎቶችም አለመጀመራቸው እንዲሁም ሌሎች በርካታ ችግሮች እየተከሰቱ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ጠቁመዋል።

በፌደራሉ መንግሥት እና ህወሓት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በትግራይ ይቋቋማል የተባለው ጊዜያዊ የሽግግር አስተዳደር እስካሁን ባለመመስረቱ በክልሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እየተከሰተ መሆኑ ይገለፃል። በትግራይ ያሉ የመንግሥት ሠራተኞች እስካሁን ደሞዝ እያገኙ አይደለም፣ የጤናና ትምህርት የመሳሰሉ ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶች በአብዛኛው የሉም አልያም የተቋራረጠ ሆንዋል። የፀጥታ ሁኔታ ደግሞ አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል። ከስምምነቱ አራት ወራት በኋላም ቢሆን በትግራይ ያለው ችግር መቀጠሉን ፖለቲከኞች እና ምሁራን ይገልፃሉ። 

በመቐለ ዩኒቨርስቲ የሕግና ስነመንግሥት ኮሌጅ መምህሩ አፅብሃ ተኽለ በትግራይ የሕጋዊ አስተዳደር ክፍተት በመፈጠሩ ምክንያት እጅግ በጣም አስፈላጊው የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት ሥራ እንኳን እየተደነቃቀፈ መሆኑ ይገልፃሉ። «በትግራይ የተኩስ ድምፅ ቆመ እንጂ ችግሮች አሁንም ቀጥለዋል» የሚሉት ምሁሩ «አሁን በትግራይ አስተዳደር የለም፣ አገልግሎት የለም፣ የፀጥታ ሁኔታ አስጊ ነው፣ ሌላው ይቅርና ሕይወት አድን እርዳታ የማዳረስ ተግባር የሚከታተል የለም» ብለዋል።

ወቅታዊውን ጉዳይ አስመልክተን ያነጋገርናቸው የተቃዋሚው ዓረና ትግራይ ከፍተኛ አመራር አቶ ዓምዶም ገብረሥላሴ በበኩላቸው በትግራይ ጊዜያዊ የሽግግር አስተዳደር በአፋጣኝ ባለመመስረቱ በርካታ ችግሮች እየተከሰቱ መሆናቸውን በመጥቀስ ለዚህም ዋነኛው ተጠያቂ ህወሓት ነው ይላሉ። አቶ ዓምዶም «ከስምምነቱ በኋላ በፌደራሉ መንግሥት በትግራይ የተወሰኑ ሥራዎች ተሰርተዋል። ይሁንና አሁንም ችግሮች እየቀጠሉ ነው» የሚሉት ሲሆን «ችግሮች እየቀጠሉ ያሉት ህወሓት በስምምነቱ መሰረት አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ለመመስረት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ነው» ሲሉ አክለዋ።

በትግራይ ቅቡልነት ያለው እና ሕጋዊ የሽግግር አስተዳደር ሳይመሰረት በተራዘመ ቁጥር የህዝቡ ስቃይ ይቀጥላል የሚሉት ያነጋገርናቸው የመቐለ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪው አፅብሃ ተኽለ፣ በፕሪቶሪያ የተደረሰው ስምምነት በአፋጣኝ እና ሙሉ በሙሉ ሊተገበር ይገባል ባይ ናቸው። «አሁን ያለው ሁኔታ የሚያሳዝን ነው፣ የሆነ ፕሮፖዛል ተይዞ ከዚህ ወደ አዲስ አበባ ይሄዳል (ህወሓት)፣ አዲስ አበባ ያለው መንግሥት ሳይስማማ ሲቀር እንደገና ሌላ ሰብሰባ እዚህ ይሰበሰባሉ። እንደዚህ እያለ አንድ በአንድ ማለቃችን ነው» የሚሉት አቶ አፅብሃ ከሥልጣን ይልቅ ህዝብን ማዳን ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲሠራ ለህወሓት ጥሪ አቅርበዋል።

ዓረና ትግራይ በትግራይ ሊቋቋም ከታሰበው ጊዜያዊ አስተዳደር ሂደት ውጭ መሆኑን የጠቆሙት የፓርቲው አመራር አቶ ዓምዶም ገብረሥላሴ በበኩላቸው ይኽን በማስተካከል፣ ሁሉን አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር በአፋጣኝ በትግራይ ሊቋቋም ይገባል ብለዋል።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ