1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት

ማክሰኞ፣ መጋቢት 12 2015

በትግራይ የሚገኙ ባንኮች በጥሬ ገንዘብ እጥረት ምክንያት ሙሉ አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑ ተገለፀ። አንዳንዶ ባንኮች ለደበኞቻቸው በቀን 2 ሺህ ብር ብቻ ወጪ እንዲያደርጉ የሚፈቅዱ ሲሆን ሌሎች ጥሬ ገንዘብ ስሌላቸው ተዘግተዋል። ምሁራን ችግሩ የተፈጠረው በቂ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ባለመኖሩ እና ህዝቡ በባንኮች ያለው እምነት በመጥፋቱ ነው ይላሉ።

https://p.dw.com/p/4P1mJ
Äthiopien Tigray Bankschließung
ምስል Million Haileselasie/DW

በትግራይ የሚገኙ ባንኮች በጥሬ ገንዘብ እጥረት ምክንያት ሙሉ አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑ ተገለፀ። አንዳንዶ ባንኮች ለደበኞቻቸው በቀን 2 ሺህ ብር ብቻ ወጪ እንዲያደርጉ የሚፈቅዱ ሲሆን ሌሎች ጥሬ ገንዘብ ስሌላቸው ተዘግተዋል። የኢኮኖሚ ምሁራን ችግሩ የተፈጠረው በቂ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ባለመኖሩ እና ህዝቡ በባንኮች ያለው እምነት በመጥፋቱ ነው ይላሉ።

ከረዥም ግዜ በኃላ በትግራይ የተከፈቱ ባንኮች በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት እጦት ምክንያት አሁንም በቂ አገልገሎት ለሕብረተሰቡ እየሰጡ አይደሉም። ያነጋገርናቸው በክልሉ ያሉ የተለያዩ ባንኮች ደንበኞች ገንዘባቸው ወጪ ለማድረግ ወደ ባንክ ሲሄዱ ገንዘብ የለም በሚል ምክንያት ያስቀመጡት ገንዘብ ማውጣት እንዳልቻሉ ገልፀውልናል።
የመቐለ ነዋሪው ዮናስ ይግዛው ካስቀመጠው የቁጠባ ሒሳብ ገንዘብ ወጪ ለማድረግ ቢሞክርም፣ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ገፈ"ገንዘብ የለንም" እንዳሉት በአንዳንዶቹ ደግሞ ረዥም ሰልፍ ተሰልፎ ሁለት ሺህ ብር ብቻ ማግኘት እንደሚቻል መመልከቱ ገልፆልናል። "ግማሽ ቀን ተሰልፌ የተፈቀደው ሁለት ሺህ ብር ወጪ አድርጌያለሁ" የሚለው ዮናስ፣ በትግራይ ያሉ ባንኮች አሁንም በቂ አገልግሎት ባለመስጠታቸው እሱን መሰል የክልሉ ነዋሪ ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጡ መሆኑ ጠቁሟል። ከሽረ ከተማ ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው፥ ባለፈው ሳምንት በከተማዋ የነበሩ ሁሉም ባንኮች ተዘግተው እንደነበረ፣ በቅርብ ቀናት ግን ከአንድ እስከ ሁለት ሺህ ብር ለደንበኞቻቸው እየከፈሉ ስለመሆኑ ነግረውናል።

Äthiopien Tigray Bankschließung
ምስል Million Haileselasie/DW

በትግራይ ባንኮች ለደንበኞቻቸው በቂ ገንዘብ ማቅረብ ባለመቻላቸው ምክንያት መደበኛ የፋይናንስ ስርዓት ሊመለስ አለመቻሉ አስተያየት ሰጪዎች ይገልፃሉ። በመቐለ እንደታዘብነው የቤት እና የመኪና ሽያጭ ጨምሮ የተለያዩ ውድ ንብረቶች ግብይት በአብዛኛው በጥሬ ገንዘብ ይከወናል። ሻጭና አገልግሎት ሰጪዎች ለተመሳሳይ አገልግሎት እና ንብረት በአከፋፈል መንገድ ላይ መሰረት በማድረግ የዋጋ ልዩነት የሚያሳዩ ሲሆን ጥሬ ገንዘብ ለሚያቀርብ ቅናሽ አላቸው።

በመቐለ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚ መምህሩ ዶክተር ሙዑዝ ሓዱሽ እንደሚሉት በትግራይ ያሉ ባንኮች በቂ ጥሬ ገንዘብ ለደንበኞቻቸው ማቅረብ ባለመቻላቸው እና ደንበኞች በባንኮች ላይ ያላቸው እምነት በመሸርሸሩ ሰፊ ችግሮች እየተስተዋሉ ነው ይላሉ። የኢኮኖሚ ምሁሩ እንደሚሉት የዋጋ ውድነት፣ ተደራራቢ ብድር እንዲሁም ሕጋዊ ያልሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መበራከት የጥሬ ገንዘብ ፍላጎቱ እንዲጨምር ምክንያት ሆንዋል ባይ ናቸው። 

Äthiopien Tigray Bankschließung
ምስል Million Haileselasie/DW

እንደ ዶክተር ሙዑዝ ገለፃ፣ ይህ ለመፍታት በመቐለ ብቻ ከ12 ቢልዮን ብር በአጠቃላይ ትግራይ ደግሞ ከ35 ቢልዮን በላይ ተጨማሪ ገንዘብ በባንኮች በኩል ወደ ገበያ ማስገባት እንደሚጠበቅ ከነባራዊ ሁኔታ ተነስተው ማስላታቸው ለዶቼቬለ ገልፀዋል። ከፍተኛ መጠን ያለው ብር ከማቅረብ በተጨማሪ መንግስት በሕብረተሰቡ ላይ የተፈጠረ ጥርጣሬ ለመቅረፍ መስራት እንደሚጠበቅበት ሙሁሩ ጨምረው ተናግረዋል።

ከሰላም ስምምነቱ በኃላ በትግራይ ዳግም የባንክ አገልግሎት ለማስጀመር ወደ ክልሉ ተላከ የተባለ ገንዘብ በአጭር ግዜ ወጪ ተደርጎ ማለቁ የባንክ ቤቶች ምንጮች ጠቁመውናል። በጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ በባንኮች አገልግሎት መስተጓጎል እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ከተለያዩ ባንኮች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለግዜው አልተሳካም።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ 

አዜብ ታደሰ 

እሸቱ በቀለ