1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ በወባ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በ60 በመቶ መጨመሩ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 29 2016

በትግራይ በወባ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በ60 በመቶ መጨመሩን የክልሉ የጤና ቢሮ አስታወቀ። በ20 ገደማ ወረዳዎች ወባ በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋቱን የገለጹት በትግራይ ጤና ቢሮ የበሽታዎች ቁጥጥር እና መከላከል ዘርፍ ኃላፊ አቶ አረጋይ ገብረመድህን አስር የሚሆኑት ወረዳዎች “በወረርሽኝ ደረጃ የሚታይባቸው” መሆናቸውን ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/4hxqn
በትግራይ እንዳባጉና በሚገኝ ጤና ጣቢያ አገልግሎት የሚጠባበቁ ታካሚዎች
የትግራይ ጤና ቢሮ የበሽታዎች ቁጥጥር እና መከላከል ዘርፍ ኃላፊ አቶ አረጋይ ገብረመድህን አስር በሚሆኑት ወረዳዎች ወባ “በወረርሽኝ ደረጃ የሚታይባቸው” መሆናቸውን ገልጸዋል። ምስል Million Haileselasie/DW

በትግራይ ክልል በወባ በሽታ የሚለከፉ ሰዎች ቁጥር በስልሳ በመቶ መጨመሩ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ። በክልሉ የአጎበር ተደራሽነት መጠን መቀነስ፣ የመድሃኒቶች ውሱንነት እና ሌሎች የበሽታው ስርጭት እንዲጨምር እንዳደረገው ተነግሯል። በሌላ በኩል የህፃናት ክትባት በክልሉ ላሉ ሁሉም ህፃናት ለማዳረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተመልክቷል።

ጦርነቱ ተከትሎ በትግራይ የጤና ስርዓቱ በመፍረሱ እንዲሁም በሌሎች ተደራራቢ ችግር ምክንያት በክልሉ ወባ ጨምሮ የተለያዩ በሽታዎች እየተንሰራፉ፥ የስርጭት መጠናቸው እየጨመረ መሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ እንደሚለው በትግራይ ሰሜን ምዕራብ ዞን፣ ማእከላዊ ዞን ወርዒ አካባቢ እና ራያ ዓዘቦ በአጠቃላይ 18 ወረዳዎች የወባ በሽታ በስፋት እየታየ መሆኑ የሚገልፅ ሲሆን በተለይም በአስር ወረዳዎች በሽታው በወረርሽኝ ደረጃ እየተንሰራፋ መሆኑ አመልክቷል።

በትግራዩ ጦርነት ሱዳን የተሰደዱ ዜጎች ጥሪ

በትግራይ ጤና ቢሮ የበሽታዎች ቁጥጥርና መከላከል ዘርፍ ሐላፊ አቶ አረጋይ ገብረመድህን "ከ18 እስከ 20 በሚሆኑ ወረዳዎች ከፍተኛ የወባ በሽታ ዝርጋታ የሚታይባቸው ናቸው። ከእነዚህ መካከል አስር በሚሆኑት ወረዳዎች የወባ በሽታ በወረርሽኝ ደረጃ የሚታይባቸው ናቸው" ብለዋል።

በተለይም በያዝነው ግንቦት እና ሰኔ ወራት የወባ በሽታ ስርጭት በትግራይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ሐላፊው ጨምረው የሚገልፁ ሲሆን አስቀድሞ የነበረው በሳምንት የሚመዘገብ አራት ሺህ ገደማ የወባ በሽታ ተጠቂዎች መጠን አሁን ላይ ወደ ሰባት ሺህ ማደጉ አመልክተዋል።

አይደር ሪፈራል ሆስፒታል አገልግሎት ለማግኘት የሚጠባበቁ ታካሚዎች
የትግራይ ጤና ቢሮ ሐላፊ ዶክተር አማኑኤል ሃይለ ክትባት ያላገኙ ወይም ያቋረጡ በትግራይ ያሉ ህፃናት ለመለየት ዘመቻ መጀመሩ ተናግረዋል።ምስል Million Haileselasie/DW

ኃላፊው "አሁን ባለው የግንቦት እና ሰኔ የወባ በሽታ ስርጭት መጠን ስንመለከተው፥ ካለፈው ግዜ ጋር ሲነፃፀር 60 በመቶ በሚሆን ነው የጨመረው። በሳምንት በወባ የሚለከፉ ሰዎች ቁጥር ከአራት ሺህ ወደ ሰባት ሺህ የጨመረ በመሆኑ፥ 60 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ማለት ነው" ሲሉ አክለዋል።

በክልሉ የወባ አምጪ እንስሳ መከላከያ አጎበር እጥረት ማጋጠሙ የሚገልፀው የትግራይ ጤና ቢሮ መዳረስ ከሚገባው አጠቃላይ የአጎበር መጠን እስካሁን የተገኘው እና የተሰራጨው 50 በመቶ ብቻ መሆኑ ይገልፃል። በመድሃኒት በኩልም ቢሆን እጥረት ቢኖርም ከፌዴራሉ መንግስት ይህ ለማገዝ እየተሰራ መሆኑ ተመልክቷል።

የትግራይ ጦርነት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸዉ መመለስ ጀመሩ

በሌላ በኩል በትግራይ በጦርነቱ ምክንያት በተደጋጋሚ ሲስተጓገል የነበረ የህፃናት ክትባት ሙሉ በሙሉ ለማዳረስ ጥረቶች መቀጠላቸው የክልሉ ጤና ቢሮ ይገልፃል። የትግራይ ጤና ቢሮ ሐላፊ ዶክተር አማኑኤል ሃይለ ክትባት ያላገኙ ወይም ያቋረጡ በትግራይ ያሉ ህፃናት ለመለየት ዘመቻ መጀመሩ ተናግረዋል።

ዶክተር አማኑኤል "ክትባት ፈፅሞ ያልወሰዱ አልያም ያልጀመሩ፣ ጀምረው ያቋረጡ ህፃናት፣ ዕድሜያቸው ደግሞ ከአምስት አመት በታች የሆኑት፥ ቤት ለቤት በሚደረግ ዳሰሳ ለይተን ልናውቃቸው፥ አውቀን ደግሞ ልንከትባቸው የምንጀምረው ዘመቻ ነው" ብለዋል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

እሸቴ በቀለ