1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩናይትድ ስቴትስና የአውሮጳ ኅብረት ጥሪ

ሐሙስ፣ ሰኔ 3 2013

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ዕያየን ነው ያሉት አምባሳደር ቶማስ ግሪንፊልድ ኢትዮጵያ እንድትራብ አናደርግም፤ አሁኑኑ መንቀሳቀስ አለብን ሲሉ አሳስበዋል።የአውሮጳ ኅብረት የቀውስ መቆጣጠሪያ ኮሚሽነር ያኔዝ ሌናርኪክ ሰብዓዊ ቀውሱን ለማስቀረት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በመላ በቀጥተኛና በተዘዋዋሪ መንገድ በአስቸኳይ እንዲንቀሳቀስ ጠይቀዋል።

https://p.dw.com/p/3uj2N
USA I US Botschafterin Linda Thomas-Greenfield I UN
ምስል Luiz Rampelotto/EuropaNewswire/picture alliance

ዩናይትድ ስቴትስና የአውሮጳ ኅብረት በትግራይ ክልል ሊከሰት የሚችለውን ረሃብ ለማስቀረት ትልቅ ዓለም አቀፍ ርብርብ እንዲደረግ ተማጸኑ። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት የጠቀሳቸው በተመድ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ዛሬ ብራሰልስ ውስጥ በተካሄደ ስብሰባ ላይ በአንዳንድ አካባቢዎች ረሃብ ሳይገባ እንዳልቀረ ገልጸዋል። በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ዕያየን ነው ያሉት አምባሳደር ቶማስ ግሪንፊልድ ኢትዮጵያ እንድትራብ አናደርግም፤ አሁኑኑ መንቀሳቀስ አለብን ሲሉ አሳስበዋል። በኢትዮጵያ የሚታየውን የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታም ሰው ሠራሽ ብለውታል። የአውሮጳ ኅብረት የቀውስ መቆጣጠሪያ ኮሚሽነር ያኔዝ ሌናርኪክ ሰብዓዊ ቀውሱን ለማስቀረት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በመላ በቀጥተኛና በተዘዋዋሪ መንገድ በአስቸኳይና በተጠናከረ ሁኔታ እንዲንቀሳቀስ ጠይቀዋል።ሌናርኪስ እንዳሉት በግጭቱ የተጎዱትን ሰዎች ለመደገፍ ለሰብዓዊ ርዳታ የሚሰጠው ገንዘብ ከፍ ማለት አለበት። የተመድ እንደሚለው ከትግራይ ህዝብ ከአምስት ሚሊዮን የሚበልጠው ማለትም ከ90 በመቶው በላይ አስቸኳይ የምግብ ርዳታ  ያስፈልገዋል። ለዚህም ድርጅቱ ለርዳታ የሚውል ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ እንዲሰጠው ጠይቋል። ዩናይትድ ስቴትስ በትግራይ ለሕይወት አድን ምግቦች፣ ለእርሻ ግብዓቶች፣ ለንጹህ የመጠጥ ውኃ መጠለያ እና ለጤና አጠባበቅ የሚውል 181 ሚሊዮን ዶላር እንደምትሰጥ አስታውቃለች። ይሁንና ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች በትግራይ ክልል በሚገኙ አካባቢዎች በሙሉ መግባት አልቻልንም ሲሉ እያማረሩ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የርዳታ ድርጅቶች ድጋፍቸውን በትግራይ ክልል እንዲያደርሱ የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ በተደጋጋሚ ጊዜያት ይገልጣል። የሰብዓዊ ርዳታ አቅርቦቱም፦ «ቅንጅታዊ አሰራሮች የበለጠ ለማሻሻል የሚቻልባቸው መንገዶች እንዲታዩ፣ በክልሉ ግብርና ትኩረት እንደሚሻም»  በኢትዮ-አውሮፓ ህብረት የጋራ ምክክር ወቅት መጠቀሱ ተዘግቧል።

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ