1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቦረናው ድርቅ ለተጎዱ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ድርጅቶች እርዳታ

ዓርብ፣ መጋቢት 1 2015

የኢትዮጵያውያን ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍና በአሜሪካ የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በቦረና ዞኑ ድርቅ ለተጎዱ የሚውል ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ ናቸው።ድርጅቶቹ "የቦረና ወገኖቻችንን ማትረፍ የዛሬ ዓድዋችን ነው" በሚል መሪ ቃል በጀመሩት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር እስካሁን አራት ሚሊዮን ብር የሚደርስ አስቸኳይ የዕርዳታ ገንዘብ አሰባስበዋል።

https://p.dw.com/p/4OVQi
Äthiopien | Dürre in Borena
ምስል Firaol Wako/PHD

በቦረናው ድርቅ ለተጎዱ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ድርጅቶች እርዳታ

ድርቅ፣ርሃብና ስደት አሁንም የኢትዮጵያ አሳዛኝ እውነታዎች ሆነው ቀጥለዋል። በቦረና ዞን ያለው ድርቅ አስከፊነት፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና የቤት እንሰሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ሲሆን "ድር ቢያብር አንበሳ ያስር"እንዲሉ ለተጎዎጂዎቹ መርጃ የሚውል ድጋፍ በመሰባሰብ ላይ ይገኛል። የኢትዮጵያውያን ካናዳውያን ኔትዎርክ ለማህበራዊ ድጋፍና በአሜሪካ የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በጋራ ያዘጋጁትን የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር "የቦረና ወገኖቻችን ማትረፍ የዛሬ ዓድዋችን ነው"በሚል መሪ ቃል ከባለፈው ቅዳሜ ጀምረው እያካኼዱ ነው።

ስለሰብዓዊ ድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብሩ ዶይቼ ቨለ ያነጋገራቸዉ የኢትዮጵያውያን ካናዳውያን ኔትወርከ ለማኅበራዊ ድጋፍ ሊቀመንበር ዶክተር ትሁት አስፋው፣የመርሐ ግብሩ አስተባባሪ ናቸው።

" የዛሬዉን ፕሮግራማችን እንግዲህ በቦረና ለሚገኙ ወገኖቻችን በድርቅ ለተጎዱትና እንሰሶቻቸውም እየሞቱ እንደነበርና አሁን ደግሞ በሰዎቹም ላይ ጉዳት እየደረሰ የሞቱም እንዳሉ ስንሰማ፣ ምን እናድርግ ብለን ተነጋገርን ሰዎች ለሰዎች ከሚባለው ድርጅት ጋር በመነጋገር፣በጋራ ሆነን ብንጀምርና ለህዝባችን ብንደርስ በሚል ዐሳብ ነው።እንግዲህ ኢክናስ ከዚህ ቀደምም እንደሚታወቀው ካለፉት ሁለት ዓመታት በላይ ወደ አምስት ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።ኢትዮጵያ ላሉ፣ በተለያዩ በተለይም ደግሞ በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖቻችን እና ያሁኑ መርሐግብር ደግሞ ዐድዋን ለወገኖቻችን በማለት ነው እና የዛሬው ዐድዋችን በቦረና ለሚገኙ ወገኖቻችን ላሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ መድረስ ነው በሚል ነው።"

Logo  Ethio-Canadian Network for Advocacy and Support
የኢትዮጵያውያን ካናዳውያን ኔትወርክ ለማኅበራዊ ድጋፍ ዓርማ ምስል Dr.Tihut Asfaw

የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በአሜሪካ መስራችና ዋና ሰራ አስፈጻሚ ዶክተር እናውጋዉ መሐሪ በበኩላቸው ወገንነት የሚፈተነው በችግር ጊዜ እንደሆነ አስገንዝበው፣የተቸገሩትን ለመርዳት በአንድነት መቆም እንደሚገባ ተናገረዋል።

" በጣም አንዱ ልቤን የነካው ነገር ምንድነው በሚድያ ያየኹት፣ቦረና ውስጥ በሣር የተሰራ ቤታቸውን ሰውየው ቤቱ ላይ ቁጭ ብሎ ሣር ቤቱን እያፈረሰ ከብቶቹን ይመግባል።ለእዛ ሰውዬ የተሰራችው ከቆርቆሮ አይደለም ከሣር ነው፤እና ከብቱ መሬት ላይ ነው እሱ እዛ ቤቱ ላይ ሆኖ ሣር እየመዘዘ ነው የሚመግበው።ምናልባት ሁለቱም አልተረፉም ይሆናል። ስለዚህ ለእንደዚህ ወገን መድረስ የሞራልም የወገንነት ብቻ ሳይሆን የሞራልም ጥያቄ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያን ስንል ኢትዮጵያን ሁላችንም እንወዳለን።እዛ ሄዶ ሰርግ ማድረግን እንወዳለን፤ደስ ብሎን መሄድ እንወዳለን።ያ አንዱ ክፍል ነው።እንደዛ የሚደረገውም ሃገር ሲኖር ነው።ስለዚህ ወገናችን በሚሰቃይበት ጊዜ ወገንነታችንን የምናረጋግጠው፣ ለችግራቸው ስንደርስ ነው።"

ይህንኑ ለተቸገሩ ወገኖች እንድረስ ተማጽኖ፣ዶክተር ትሁትም በማጠናከር፣የሚከተለውን ጥሪ አስተላልፈዋል።

"ለመላው ኢትዮጵያውያን ነው።ለቦረና ሕዝብ እንድረስ።ሁሌም እንደምናደርገው፣ከራሳችን ብዙ ሰው ስላለው ብሎ አይደለም እያደረገ ያለው ከሌለው ላይ በካርድ ብድርም በምንም እያደረገ ሲረዳ ሕዝቡን ሃገራችንን ስንረዳ ነበር።እና አሁንም ይህንን ህብረታችንን ዐድዋን ስናስብ ከመጣብን ከዚህ ድርቅ የወገኖቻችንን ሕይወት እየቀጠፈ ካለው ከዚህ አደጋ ለመታደግ አንድ ሆነን እንቁም የሚል መልዕክት ነው ያለኝ።"

ድርጅቶቹ፣በጀመሩት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር፣እስካሁን አራት ሚሊዮን ብር የሚደርስ የሰብዓዊ ዕርዳታ ገንዘብ ማሰባሰባቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ታሪኩ ኃይሉ

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ