1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቡርኪናፋሶ ውኃን እንደ ጦር መሣሪያ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 27 2014

ውኃ ቡርኪናፋሶ ውስጥ እንደ ጦር መሣሪያ እየዋለ ነው። የርዳታ ለጋሽ ድርጅቶች ከምዕራብ አፍሪቃዊቷ ቡርኪና ፋሶ በኩል የማስጠንቀቂያ ደውል እያሰሙ ነው ይለናል የARDው ዘጋቢ ዱንያ ሣዳቂ ከሞሮኮ ራባት በላከልን ዘገባው። ቡርኪና ፋሶ ውስጥ ከሩብ ሚሊዮን የሚልቅ ሕዝብ የ«ውኃ ጦርነት» በተሰኘ ግጭት ሰለባ መኾኑ ተዘግቧል።

https://p.dw.com/p/4CGkB
Burkina Faso Stadt Djibo Luftaufnahme
ምስል Sam Mednick/AP/picture alliance

የውኃ መሠረተ-ልማቶች ላይ የሚሰነዘሩ አሻጥሮች

የርዳታ ለጋሽ ድርጅቶች ከምዕራብ አፍሪቃዊቷ ቡርኪና ፋሶ በኩል የማስጠንቀቂያ ደውል እያሰሙ ነው ይለናል የARDው ዘጋቢ ዱንያ ሣዳቂ ከሞሮኮ ራባት በላከልን ዘገባው። ቡርኪና ፋሶ ውስጥ ከሩብ ሚሊዮን የሚልቅ ሕዝብ የ«ውኃ ጦርነት» በተሰኘ ግጭት ሰለባ መኾኑ ተዘግቧል። እስካሁን ማንነታቸው በውል ያልታወቁ ጥቃት አድራሾች የውኃ መሠረተ-ልማቶች ላይ አሻጥሮችን ሰንዝረዋል፤ የውኃ ማጣሪያዎች እና ማጓጓዣዎች ላይ እያነጣጠሩ ጥቃት አድርሰዋል።  ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 32 ያህል የውኃ አቅርቦት ሥፍራዎች ወድመዋል። ወትሮም በሽብር ጥቃቶች፣ ብርቱ ድርቅ እና የምግብ እጥረት ሥጋት ለተጋረጠባቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች የውኃ አቅርቦቶች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች «በእንቅርት ላይ ጆሮ ገድፍ» ኾኖባቸዋል። 

Burkina Faso schlechte Wasserversorgung
ምስል OLYMPIA DE MAISMONT/AFP/Getty Images

ጂቦ፦ በቡርኪና ፋሶ ሰሜናዊ ክፍል የምትገኝ ከተማ ናት። እዚህች ከተማ ውስጥ በተለይ የውኃ ጉድጓዶች እና የውኃ መምጠጪያዎች የጥቃት ዒላማ ተደርገዋል። ዓሚናታ ለፈረንሳይ የመገናኛ አውታር (France 24)እንደተናገሩት ከኾነ ከዋና ከተማዪቱ ዋጋዱጉ ሸሽተው ጂቦ ከተማ የመጡት አሸባሪዎችን ፍራቻ ነው። 

«ወደ ጎረቤቶቻችን መጥተው በ24 ሰአት ውስጥ መኼድ እንዳለብን ነገሩን። በአሁኑ ወቅት ቤተሰቦቼ የት እንዳሉ ዐላውቅም። የማውቀው ጥለው መኼዳቸውን እና በህይወት መኖራቸውን ብቻ ነው። እዚህ ዋጋዱዱ ውስጥ መቆየት አልችልም። ቤተሰቦቼ በሙሉ ባለቤቴ፤ ልጆቼ፤ እናቴ ያሉት ጂቦ ውስጥ ነው።»

በጂቦ ከተማም ቢሆን ኹኔታዎች ከምን ጊዜውም በላይ አሳሳቢ ደረጃ ደርሰዋል ይላሉ ማሪን ኦሊቬሲ። ቡርኪና ፋሶ ውስጥ ስደተኞችን በማማከር የሚረዳው የኖርዌይ ተቋም ቃል አቀባዪት ናቸው ማሪን። በጂቦ ከተማ በጥቃቱ የተነሳ ነዋሪው ለሕይወቱ ዋስትና አስፈላጊ የኾኑት የውኃ አቅርቦቶች በተደጋጋሚ እጅግ መጎዳታቸው በብርቱ አሳስቧቸዋል። 

«ጂቦ ውስጥ ነዋሪው በየካቲት ወር ጥቃቱ ከመጀመሩ በፊት ለአንድ ሰው ለአንድ ቀን ከ3 እስከ 6 ሊትር ገደማ ውኃ ነበረው። አሁን ኹኔታው እጅግ አሳሳቢ ነው። እንደ የዓለም ጤና ድርጅት ከኾነ አንድ ሰው በሕይወት ለመቆየት ቢያንስ 7 ሊትር ውኃ ያስፈልገዋል። ጥቃቱ ከመጀመሩ በፊትም ቢሆን ቢበዛ በ6 ሊትር ነበር የተወሰንነው። ከጥቃቱ ጀምሮ ሰዉ መጠቀም የቻለው ካለው ውኃ ግማሽ ያህሉን ነው። ያ ማለት ጂቦ ውስጥ በአሁኑ ወቅት አንድ ሰው በቀን ውስጥ ከ3 ሊትር ያነሰ ውኃ ነው ያለው።»

Burkina Faso schlechte Wasserversorgung
ምስል Leo Correa/AP/picture alliance

ችግሩ አሁን ከጂቦ ከተማም ተሻግሯል። በውኃ አቅርቦቶች ጥቃት የተነሳ ወደ 300.000 የሚጠጉ ነዋሪዎች መጎዳታቸውንም ማሪን ኦሊቬሲ ይናገራሉ። በብዙ ቦታዎችም የመድኃኒት እና የመባልእት እጥረት አለ። ወትሮም የውኃ እጥረት በነበረበት በዚህ በረሃማ ስፍራ የውኃ አቅርቦት መሠረተ-አውታሮች መጠቃት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ካለፈው የካቲት ወር አንስቶ 32 ያህል የውኃ አቅርቦት ሥፍራዎች መውደማቸው ተመዝግቧል።  አሁን ጂቦ ከተማ ውስጥ በቂ ባይሆንም ኅብረተሰቡ ውኃ የሚቀርብለት በቦቴ ተሽከርካሪዎች ነው። ምንም እንኳን ለሰዉ የውኃ አቅርቦት ለማዳረስ ርብርብ ቢደረግም ቡርኪናፋሶ ውስጥ ከፍተና የሰብአዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን ባልደረባው ሚካኤል ማሊካ አስጠንቅቀዋል። የርዳታ ድርጅቶችም በውኃ እጥረቱ ግራ መጋባታቸውን አክለዋል።

«ጂቦ ውስጥ ኅብረተሰቡ በቀን የሚያስፈልገው የውኃ መጠን 500 ኩቢክ ሜትር ነው። እንዳለመታደል ኾኖ ድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን ማዳረስ የምንችለው 100 ኩቢክ ሜትር ብቻ ነው። እዚህ የተደቀነው አደጋ ለኅብረተሰቡ የንጹህ ውኃ አቅርቦት እጦት ነው። ያም ማለት፦ ምግብ ለማብሰል፣ ለጽዳት እና ለመጠጥ የሚኾን ውኃ እጦት ነው። ለድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድንም ለሥራው ውኃ በጣም አንገብጋቢ ነው። ለመዋቅራችን፣ ድጋፍ ለምናደርግላቸው የመድኃኒት ክፍሎች እና ሐኪም ቤቶች ውኃ እጅግ ያስፈልገናል።»

Burkina Faso schlechte Wasserversorgung
ምስል OLYMPIA DE MAISMONT/AFP/Getty Images

መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ቡርኪና ፋሶ ውስጥ ውኃን መሠረት ያደረገ ጦርነት በኅብረተሰቡ ዘንድ ሊቀሰቀስ ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል። አሸባሪዎች እና የታጠቁ ወንበዴዎች የውኃ ተቋማትን የጥቃት ዒላማቸው በማድረግ ችግር ውስጥ የወደቀውን የሀገሪቱን የፀጥታ ኹኔታ ጭራሽ በማባባሱ ላይ እንደተጠመዱ ይነገራል። ስለ አካባቢው ጥናት ያከናወኑ ባለሞያዎች ቡርኪና ፋሶን አሸባሪዎች ወደ ምዕራብ አፍሪቃ የወደብ ከተሞች ለማለፍ መሸጋገሪያ ሀገር አድርገው ይወስዷታል ይላሉ። የቡርኪና ፋሶ ጎረቤት በኾኑት ማሊ እና ኒጀር በርካታ ሚሊሺያዎች እና ታጣቂዎች ይርመሰመሳሉ። ከርሠ ምድሯ በወርቅ ክምችት እንደዳበረ የሚነገርላት ቡርኪናፋሶ ነዋሪዎቿ የዕለት መጠጥ ውኃ ተቸግረው ሀገሪቱ በተመድ መስፈርት ከዓለማችን የመጨረሻዋ ድሀ ሀገር ተብላ መሰየሟ በርካታ አፍሪቃውያንን የሚያስቆጭ ነው። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ/ዱንያ ሳዳቂ 

እሸቴ በቀለ