1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቀጠር ዓለም ዋንጫ ዝግጅት የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን ምን ይላሉ?

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ኅዳር 16 2015

የዓለም ዋንጫ አስተናጋጇ ቀጠር በውጭ ሀገራት ሰራተኞች ጉልበት ሰባት ስታድየሞች፣ አዲስ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የባቡርና የአስፋልት መንገዶችን ገንብታለች። በዚህም ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች ተካፍለዋል። በግንባታው ወቅት ቀጠር የበርካታ ሰራተኞችን መብት አላከበረችም በሚል ጠንካራ ትችት ተሰንዝሮባታል። በግንባታዉ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን ምን ይላሉ?

https://p.dw.com/p/4K2fC
Katar, Gastgeber der Weltmeisterschaft 2022
ምስል Koen van Weel/ANP/picture alliance

በቀጠር የኢትዮጵያውያን ሰራተኞች ተሞክሮ

የዘንድሮውን የዓለም ዋንጫ ውድድር አስተናጋጅ ሀገር ቀጠር የሰራተኞችን መብት ሳታከብር ከውጭ ሀገር የመጡ ሰራተኞችን ጉልበት በዝብዛለች በሚል በተለይ  በአውሮጳውያን ከፍተኛ ትችት ተሰንዝሮባታል። ቀጠር  የዘንድሮውን የዓለም ዋንጫ ውድድር እንድታዘጋጅ የተወሰነው እጎአ  በ2010 ነበር። ከዛን ጊዜ አንስቶ ሀገሪቱ አስተናጋጅነቷን በገንዘብ እንደገዛች፤ የሠራተኞችን እና የሠብዓዊ መብት አታከብርም በሚል ስሟ በተደጋጋሚ ተነስቷል። በዚህ በጀርመን የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ከመጀመሩ እና ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ከእግር ኳስ ስፖርታዊ ጉዳዮች ይልቅ ተሳታፊ  ብሔራዊ ቡድኖች እና ተጫዋቾቻቸው  ቀጠር ታደርሳለች ያሉትን የሰብአዊ መብት ጥሰትን በተለያየ መንገድ መግለፃቸዉን  የሚያወሱ ዘገቦች  ጎልተዉ ነበር።  አንዳንዶች ተጫዋቾቹ እና ስፖንሰር አድራጊዎች በቀጠር እና የአለም አቀፍ የእግር ኳስ ፌደረሽን ወይም ፊፋ ላይ ይበልጥ ጫና መፍጠር ይችሉ ነበር እያሉ ሲተቹ ሌሎች አውሮፓውያን «ድርብ ሞራላቸውን » ሊተው እና እግር ኳሱ ላይ ብቻ በማተኮር የሀገሪቱን ደንብ እና ባህል ሊያከብሩ ይገባል ሲሉ ይከራከራሉ። 
ጥበበ አለምፀሀይ ለአለም ዋንጫ ዝግጅት የስራ እድል አግኝቶ ከኢትዮጵያ ወደ ቀጠር የሄደው ከሰባት ዓመት በፊት ነው። እዛም የተለያዩ የግንባታ ማሽኖች ኦፕሬተር ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት በቀጠር ያለው ድባብ  የተለያየ ነው ይላል።«  እቲዲየም መግባት የሚችል ገብቶ ይመለከታል። የማይችል ደግሞ በቅርበት እንዲያይ በተለያዩ አካባቢዎች መመልከቻ ስክሪኖች ተዘጋጅተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ለህዝብ የተለያዩ መዝናኛ ቦታዎች ተዘጋጅተዋል። ለሚመጡት እንግዶች ትልቅ አቀባበል እየተደረገ ነው» ጥበበ ከኢትዮጵያ ከወሰደው የቆጵሮስ እና የግሪክ ድርጅት ጋር የነበረውን ውል ጨርሶ በአሁኑ ሰዓት ኢንፍራ ሮድ በተሰኘ ሀገር በቀል ድርጅት ተቀጥሮ እየሰራ እንደሆነ ገልፆልናል። ቀጠር የአለም ዋንጫን እንድታዘጋጅ ፊፋ እድሉን ከሰጣት ጊዜ አንስቶ የአውሮጳ መገናኛ ብዙኃን የሚያወጡትን ዘገባዎች ተከታትያለሁ የሚለው ጥበበ  ከሰብዓዊ መብት ጋር በተያያዘ የወጡት ዘገባዎች እና የግል ተሞክሮው የሚቃረኑ እንደሆኑ ነው የገለፀልን። 
« የሰብዓዊ መብት ጥሰት በግሌ አላየሁም። ነገር ግን አንዳንድ ወቀሳ የሚያቀርቡ ሰዎች አሉ ። አንዳንድ ድርጅቶች የሰራተኛ መብት አያያዛቸው ወረድ ያለ ነው። ነገር ግን  ሀገሪቷ ለቀን ሰራተኞችም ለሁሉም ያወጣችው ህግ አለ። ድርጅቶቹ በዛ ህግ መሠረት ይተዳደራሉ። ድርጅቶቹ ናቸው ተጠያቂ መብት ሳያከብሩ ሲቀር ክሱን ወደፍርድ ቤት መውሰድ ይችላል የፍርድ ሂደቱም አመርቂ ነው።»

ጥበበ አለምፀሀይ
ጥበበ አለምፀሀይ ምስል privat

ሌላዋ አስተያየቷን ያካፈለችን ኢትዮጵያዊት ሊና አደም ትባላለች። ሊና ኑሮዋን በዶሀ ካደረገች 10 ዓመታት ተቆጥረዋል። በቤት ሰራተኝነት ስራ ወደ ቀጠር እንደሄደች የገለፀችልን ሊና ሀገሪቷ ላይ ሌላም የፈለገችውን የስራ እድል እንዳገኘች ገልፃልናለች።  በአሁኑ ሰዓት በአንዱ የአለም ዋንጫ  ስታዲዮም ውስጥ የሚገኝ ከቀረጥ ነፃ ሱቅ ውስጥ ተቀጥራ ለእግር ኳስ ጎብኚዎች የተዘጋጁ እንደ ቲሸርት እና ኳስ እና ጌጣ ጌጥ የመሳሰሉ እቃዎችን ትሰራለች።  እስካሁን ለተለያዩ ድርጅቶች ተቀጥራ ትሰራ እንደነበር የገለፀችልን ሊና አሁንም ይሁን ከዚህ ቀደም ከሰራተኞች መብት ጋር በተያያዘ በግሏ ምንም አይነት ችግር ገጥሟት እንደማያውቅ ገልፃልናለች። « እኔ በህጋዊ መንገድ በደሞዝ ተስማምቼ የገባሁበት መስሪያ ቤት ነው።  እንደ ቪዛ አገዛዙ ስራው እና ደሞዙ ይለያያል።»

ተገኝ ዳና ልክ እንደ ጥበበ ለስራ ወደ ቀጠር የሄደው ከሰባት ዓመት በፊት ነው።  ይህንንም የስራ እድል ያገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ በመንገድ ስራ ተቀጥሮ ይሰራ በነበረ  አንድ የግሪክ ድርጅት አማካኝነት እንደሆነ ገልፆልናል። « ያ መሥሪያ ቤት እዚህ ስራ ስላሸነፈ ነው ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የወሰደን።  ወደ 200 ሰራተኞች እንሆናለን።

የተገኝስ ተሞክሮ ምን ይመስላል? 

«ሰው በተዋዋለው መሠረት ይከፍላሉ። ሌሎች ጥሰቶች እኔ አላየሁም። ስፖንሰር እና ፍሪ ቪዛ የሚባል ነገር አለ። አንዳንድ ሰዎች እዚህ ስፖንሰር የሚያደርጋቸው ከሌለ በፍሪ ቪዛ ይመጡ እና ይቸገራሉ። ብዙ ፓኪስታኒ ህንድ ሲሪላንካ እና ኔፓላውያን በፍሪ ቪዛ ይመጣሉ። በስፖንሰር የመጣ ግን ማንም አይቸገርም።» ተገኝ እንደሚለው ቀጠር ውስጥ ዝቅተኛ ከሚባለው የቀን ሥራ አንስቶ እስከ ስቴዲዮም ዲዛይን ማውጣት እና በፕሮፌሰርነት የዩንቨርስቲ መምህር ሆኖ እስከማገልገል በከፍተኛ ስራ የተሰማሩ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ቀጠር ውስጥ ይኖራሉ። ቁጥራቸውም እስከ 25 ሺ ይደርሳል ይላል።  እሱም ሆነ ሌሎች ኢትዮጵያውያን በኢኮኖሚ በጣም ተጠቃሚ እንደሆኑ ነው የነገረን። « የእነሱን ባህል ወግ እና ኃይማኖት ጠብቆ ለሰራ ሀገሪቱ በጣም ጥሩ ሀገር ናት። የአየር ንብረቱ ሞቃታማ መሆኑ ነው እንጂ ልክ አውሮፓ ማለት ናት። ምንም የሚጎል ነገር የለም። » ተገኝ ከአመጣው ድርጅት ጋር የነበረውን ውል ጨርሶ ለሌላ ድርጅት ተቀጥሮ እየሰራ ስለሆነ ስራው ቀጣይነት እንዳለው እና በዶሀ እንደሚቆይ ነግሮናል። በዓለም ዋንጫው ምክንያት ወደ ቀጠር የመጣው ጥበበም ቢሆን የስራ ፍቃዱን አራዝሞ በቀጠር ለመቆየት ወስኗል። 
ሊናም ብትሆን እንዲሁ። እግር ኳሱ ለበርካታ የሀገሯ እና የውጭ ዜጎች የስራ እድል እንደከፈተ የምትናገረው ሊና ከ 250 እስከ 500 የቀጠር ሪያል ወይም እስከ 7000 ብር ገደማ በቀን ቀጣሪ ድርጅቷ ከፍሏቸው የሚሰሩ ሰራተኞች እንዳሉ ገልፃልናለች። ቀጠር የሰራተኞች መብትን ብቻ ሳይሆን ፣ የሴቶችን መብት አታከብርም በሚል ትወቀሳለች። ሊና በሴቶች መብት ላይ የሚነሳውን ወቀሳ በከፊል ብትረዳም የሀገሪቷን ህግ ማክበርን ታስቀድማለች። « ቀጠር በሸሪያ የምትተዳደር ሀገር ናት። መኖር እና መስራት ስለምፈልግ የሀገሪቱን ህግ አከብራለሁ። መጣስ የሌለብኝን ነገር ለደህንነቴ ስል አልጥስም። » ትላለች። 
ሊና ተቀጥራ ከምትሰራው ስራ ውጪ የኢትዮጵያ ባህላዊ ልብሶችን ቀጠር ውስጥ በመሸጥ ትተዳደራለች። ሊናም ትሁን ተገኝ በዚህች ሀገር የስራ እድል በማግኘታቸው እና የአለም ዋንጫን በቅርበት ሲስተናገድ በመታዘባቸው ደስተኞች ናቸው። ከፈረንጆቹ  1998 ዓ ም አንስቶ የተደረጉ አለም ዋንጫዎችን ይከታተል እንደነበር የገለፀልን ተገኝ በተለይ ዘንድሮ እሱም አስተዋጽዎ ባበረከተበት ሐገር የአለም ዋንጫ ግጥሚያ  ሲደረግ በማየቱ የአለም ዋንጫውን ከምንም በላይ ልዩ ያደርገዋል።

ሊና አደም
ሊና አደምምስል privat

ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ